1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ የካቲት 25 2014

ኢያሱ ኃይሉም «በንጹሐን ደም የታጠቡ ሁሉ የእጃቸውን የሚያገኙበት ግዜ ደረሰ ፤ጌታ የተመሰገነ ይሁን» በማለት አስተያየታቸውን ደምድመዋል። ኑር ናስርም ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል።«የንጹሀን ደም ይጮሀል ሁሉም በሰራው ግፍና ወንጀል ለፍርድ የሚቀርብበት ቀን እሩቅ አይሆንም። ሁሉ ከፈጣሪ ፍርድ አያመልጥም።»የሚል።

https://p.dw.com/p/480VO
Äthiopien Addis Abeba Gedenken an Schlacht von Adwa
ምስል Solomon Muchie/DW

የየካቲት 25 ቀን 2014 ዓም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት


የዛሬው የማኅበራዊ መገናና ዘዴዎች ቅኝት ሰሞኑን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አነጋጋሪ ከነበሩ ጉዳዮች ውስጥ በሶስቱ ላይ ያተኩራል ለዝግጅቱ ኂሩት መለሰ  

የዘዛሬው ዝግጅታችን በማኅበራዊ መገናና ዘዴዎች፣ በአዲስ አበባ የአድዋ ድል አከባበር ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጸሙ ከባድ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን የሚያጣራ የተመድ መርማሪ ኮሚሽን አባላት ሹመት፤ እንዲሁም በዩክሬኑ ጦርነት ላይ  የተሰጡ አስተያየቶችን ያስቃኘናል።
126ኛዉ የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በተለይ በአዲስ አበባ በምኒልክ አደባባይና በአድዋ ድልድይ በተለያዩ መርኃ ግብሮች  ተከብሯል። የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከበዓሉ አስቀድሞ በዓሉ በአድዋ ድልድይ በአገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል  ሲል ባሰራጨው ደብዳቤ በዓሉ በሚኒልክ አደባባይ መከበር አለመከበሩን በግልጽ አለመጥቀሱ ተቃውሞ አስከትሎ ነበር። የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማሕበር «የማክበሪያ ቦታዉ ወደ ሌላ ቦታ መቀየሩ የድሉን መታሰቢያነት ዝቅ ያደርገዋል የሚል ስጋት አለን» የሚል መግለጫ አውጥቶ ነበር። ይሁንና ባህል ሚኒስቴር በዋዜማው አስተባብሎ በዓሉ በሁለቱም ቦታዎች እንደሚከበር አስታውቆ ነበር። የአድዋ ድል በዓል በአዲስ አበባ በሁለት ቦታ መከበሩ ግን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ብዙ አነጋግሯል።በዚህ ላይ ከተሰጡት አስተያየቶች ውስጥ ዘለፋዎችንና የግልሰቦችን ክብር የሚነኩ አስተያየቶችን ትተን በጨዋ አንደበት የቀረቡትን እንመለከታለን 
በድሩ ሁሴን በዓሉ ለምን በምኒልክ አደባባይ ብቻ አልተከበረም ከሚሉት መካከል ናቸው ምኒልክ ያልተዘከርበት፣ አድዋ. ጋሬውን ማንገስ. ያለፈርስ ማለት ነው ብለዋል።  «ያለ ቦታው ሁሉም ነገር ዉበት የለዉም የቦታ ለዉጥ ማድረግ ለምን ተፈለገ ዓድዋ መከበር ያለበት በ እምዬ ምኒልክ አደባባይ ብቻ ነው። ምኒልክ ዛሬም ንጉሥ ነው የሚሉት ደግሞ ተመስገን ገመቹ ናቸው። እስከ አሁን የአደዋ በአል ቀድሞ በኦፊሴል ከሚከበርበት የምኒሊክ አደባባይ ወደ አደዋ ድልድይ የተቀየረበት ዋና ምክንያት አልተገለፀም ። ይላል የአስፋው ፀጋዬ አስተያየት። የወማ ዳዋሳ አስተያየት ደግሞ ከቀደሙት ይለያል ቦታ ለምን ያጣላል የሚል ሃሳብ ነው የያዘው« ህዝብ ሁለ በቦታ ሲጣላ ይገርማል! በአድዋ ድልድይ ላይ የአድዋ በዓል ለምን ይከበራል? ራያ፣አላማጣ፣ ወልቃይት ጠገደ፣ሰቲት ሁመረ፣ወለጋ፣መተከል፣ አዲስ አበባ መሬት ሁሉ የእኛ ከእኛ ወጪ ወደ ውጪ የሚል....ሲሉ ተችተዋል። 
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የተፈጸሙ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ወንጀሎችን የሚመረምር ቡድንን ሰየመ። ምክር ቤቱ ለዚሁ ስራ ሦስት የሕግ ባለሙያዎችን የመርማሪ ኮሚሽኑ አባላት አድርጎ ሰይሟል። የቀድሞዋ የዓለማቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት ዋና ዓቃቤ ሕግ ጋምቢያዊቷ ፋቱ ቤንሱዳ፣ አሜሪካዊው በሚቺጋን የሕግ ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር ስቲቨን ራትነር እና ኬንያዊቷ ጠበቃና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ ናቸው በምክር ቤቱ የተሰየሙት። ጋምቢያዊቷ ፋቱ ቤንሱዳን በመርማሪ ኮሚሽኑ ሊቀመንበርነት ተሰይመዋል። በዚህ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት መግለጫ ላይ አስተያየት ከሰጡት አንዱ ደጀኔ ምኅረት ቅሬታማ ማሳሰቢያም አላቸው።« ቅሬታ አለኝ በኦሮሚያ እየተፈፀመ ያለው ግፍ አብሮ መጣራት አለበት»ብለዋል። ጥቁር ሰው በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረ አስተያየትም ከደጀኔ ሀሳብ ጋር ይመሳሰላል። ምርመራው በሁሉም የኢትዮጵያ ግዛት ይካሄድ ሲል ይጠይቃል። 
ሰብ ዶ ደብ ይስን በሚል የፌስቡክ ስም ፣ «እውነት እና ፍትሕ የጊዜ ጉዳይ እንጂ መውጣታቸው አይቀርም።» ሲል ፒ አር ኤም ኦ ባም አሁን ነው ጊዜው ሁሉም የእጁን ያገኛል ብለዋል። ኢያሱ ኃይሉም «በንጹሐን ደም የታጠቡ ሁሉ የእጃቸውን የሚያገኙበት ግዜ ደረሰ ፤ጌታ የተመሰገነ ይሁን» በማለት አስተያየታቸውን ደምድመዋል። ኑር ናስርም ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል።«የንጹሀን ደም ይጮሀል ሁሉም በሰራው ግፍና ወንጀል ለፍርድ የሚቀርብበት ቀን እሩቅ አይሆንም። ሁሉ ከፈጣሪ ፍርድ አያመልጥም።»የሚል። «አሜሪካ ጭር ሲል አትወድም ከትግራይ ወንድሞቻችን ጋር በሰላም መኖር ተገቢ ነው የሚለው ደግሞ የጉታ ቶላ አስተያየት ነው። የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በ2013 ዓ.ም ጥቅምት መጨረሻ  በትግራይ ተቀስቅሶ በአማራ እና አፍር ክልሎች በተዛመተዉና አሁንም በአፋር ክልል በቀጠለው ጦርነት የተፈጸሙ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎችን የሚያጣራና የሚመረምር ቡድንን ለማቋቋም የወሰነው ባለፈው ታሕሳስ ወር ነበር። ያኔ ኢትዮጵያ ውሳኔውን ተቃውማ ነበር። ከትንንት በስተያ የኢትዮጵያ የፍትህ ሚኒስትር ዶክተር ጌድኦን ጢሞቲዮስ የኢትዮጵያ መንግሥት ከመርማሪው ቡድን ጋር እንደሚተባበር ለምክር ቤቱ መግለጻቸው ተዘግቧል። 
በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አነጋጋሪ ከነበሩት ውስጥ ትናንት አንድ ሳምንት በደፈነው የዩክሬን ጦርነት ነው። ሩስያ ከአስር ቀናት በፊት የዩክሬንን ድንበር ጥሳ ባካሄደችው ወረራ እስካሁን ሀገሪቱን ለቆ የተሰደደው ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በልጧል።ዩክሬን ከ9ሺህ በላይ ሰዎች እንደተገደሉባት ስትገልጽ ሩስያ ደግሞ 500 ወታደሮቿ መሞታቸውን ተናግራለች።ከሁለቱም ወገን የተገለጸው የሟቾች ቁጥር ግን በገለልተኛ ወገን የተጣራ አይደለም። ከዚህ ሌላ በተለያዩ የዩክሬን ከተሞች የሚገኙ መሰረተ ልማቶች፣ የመኖሪያና የመስሪያ ቤቶች ህንጻዎች ወድመዋል። 
«ለዚህ ሁሉ የዩክሬይን ምስቅልቅልና ውድመት ተጠያቂው ኮሜድያኑ የዩክሬን መሪና አደፋፋሪው ምዕራቡ አለም ነው ።ሩስያ እልክ ውስጥ ገብታለች ሲሉ ግምታቸውን በፌስቡክ ያሰፈሩት የተናገሩት አሚን አወል ናቸው። ብርሃኑ ገዙ «ፑቲን ወደዚህ ጦርነት የገባው ምርጫ በማጣት ይመስላል። ዩክሬይን የምዕራባውያን ወጥመድ ሆናበታለች። እርሱም በኑክሊየር አፀፋ እመልሳለሁ ማለቱ ለማስጠንቀቅ ያህል ቢሆንም አደገኛ ነገር ነው። የግራ ቀኙ ነገር ሲታይ ዓለም ወደ ምጥ ጣር መጀመሪያ እየገባች እንዳለ ግልጽ ነው።»ሞሀመድ ሰዒድ ደግሞ ሰላማዊ መፍትሄ ይፈለግ ሲሉ መክረዋል። «ግርም እኮ ነው የሚሉኝ ምእራባውያን ግጭት አባብሰው ምስኪኖችን ለማስጨረስ ነውንዴ? ይልቅ ወደ ሰላም የሚመጡበትን መንገድ ዝቅ ብለውም ቢሆን መጠየቁ አይሻልም ለነገሩ ምናቸው ተነካና !።!ሲሉ  ዮ ራቢ የደህም ተቀራራቢ አስተያየት አላቸው። «በምድራችን ላይ ሠላም ይስፈን። እነደኔ ያለዉ ደሃ ከሠላም እንጂ ከጦርነት የሚያተርፈዉ የለም። የግድ አንዱን ጎራ ካልደገፋችሁ የተባልን ይመስል ሥራችንን ትተን ባለ ጉዳይ ስንመስል እነሱስ ቢሰሙ አይታዘቡንም?»ብለዋል። ጫንያለው ገብረ መድኅን «ነገሮችን ለማባባስ ከመሯሯጥ ወደ መፍትሄ መሄድ አይሻልም መሳርያ መግዢያ አበርክቶ መሳርያ ለመሸጥ መሯሯጥ ምን ይሉታል ሲሉ ትዝብታቸውን አካፍለዋል ። የጦርነቱ ቀስቃሽ አሜሪካና የኔቶ አባል ሀገራት ናቸውና 1997 በፊት ወደነበረው ድንበራቸው ይሂዱ ዪክሬንንም በዶንባስ ግዛት የምትጨቁናቸው ዜጎች መብታቸውን ታክብር ምዕራባውያንም ማዕቀብ የሚሉት የፈሪ ዱላቸው ያንሱ ሲሉ ጥሪ ያቀረቡት መኑ ከመአምላክ ናቸው። አውሮጳ ላይ ጦርነት እንዲካሄድ እያደረገች ያለችውን አሜሪካንን ተይ ይበሏት ሲሉ መክረው፣ አውሮጳውያንም በራሱ የሚተማመን ሀገር የለም እንዴ? የሚል ጥያቄ አንስተዋል። በርግጠኝነት መናገር የሚቻለው አሜሪካ ባትኖር የትም ሀገር ላይ ግጭት ሳንሰማ እንኖር ነበር። ያሉት ደግሞ መላኩ ታደሰ ናቸው።

Ukraine-Konflikt - Tschernihiw
ምስል Dmytro Kumaka/AP/dpa/picture alliance
Schweiz Genf | UN-Menschenrechtsrat | Außenminister Lawrow | Diplomaten haben Saal verlassen
ምስል KRISTOFFER JONSSON/REUTERS

«እኔ እደሚመስለኝ ችግሩን መፍታት የሚቻለው በሰላም በመነጋገር እንጂ ሩስያ ላይ ማእቀብ በመጣልን ሩስያን በማግለል አደለም የበለጠ ችግሩን ማባባስ ነው የችግሩ ቁልፍ ያለው ሩስያና ዩክሬን ጋ ብቻ ሳይሁን አሜሪካና አውሮጳም ነው ስለዚህ አውሮፓና አሜሪካ ቆም ብለው ማሰብና ችግሩን በብልሃትና በጥበብ በሰላም መፍታት ነው። አንዱን ሌላውን ማጥፋት ኪስራ እንጂ ጥቅም የለውም የሚሉት ግርማይ ተስፋይ በፌስቡክ ይህ ችግር አለምን ወደ ጥፋት የሚወስድ ነው፤ካለፈው ጦርነት መማር አለብን።ይህ ችግር የ አለም ህዝብም ህፃናት ልጆችም በሚሰሙት መጥፎ ዜና እየተጨነቁ ነው የአዓለም ኢኮኖሚም እያሽቆለቆለ ነው» በማለት ግጦርነቱን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም በዩክሬን የተከሰተውን ቀውስ ሁለቱም ወገኖች በሰላማዊ መንገድና በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቀረቡ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለሁለቱም ወገኖች በጻፉት ደብዳቤ «ሁለቱም ግጭትን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡም ጠይቀዋል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትም ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሌሎች አማራጮችን መጠቀም እንደሚገባቸውም ጥሪ አቅርበዋል። 

ኂሩት መለሰ 

እሸቴ በቀለ