1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብሪታንያና የአውሮጳ ኅብረት የንግድ ግንኙነት ድርድር

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 6 2013

የብሪታንያና የአውሮጳ ኅብረት የወደፊቱ የንግድ ግንኙነት ድርድር መጨረሻ ከወዲሁ ባይታወቅም ድርድሩ ያለ ስምምነት ከተጠናቀቀ ግን ጉዳቱ አስከፊ መሆኑ እንደማይቀር ነው ተደጋግሞ የሚሰማው።ድርድሩ ያለ ስምምነት ቢቋጭ ለሁለቱም ወገኖች አይጠቅምም።ሆኖም ብሪታንያ ይበልጥ ተጎጂ ልትሆን እንደምትችል ነው የሚገመተው።

https://p.dw.com/p/3mlSg
Boris Johnson und Ursula von der Leyen
ምስል Peter Summers/Getty Images

የብሪታንያና የአውሮጳ ኅብረት የንግድ ግንኙነት ድርድር

ብሪታንያ ከአውሮጳ ኅብረት ጠቅላ የምትወጣበት የሽግግር ጊዜ በጎርጎሮሳዊው ታኅሳስ 31፣ቀን 2020 ያበቃል።ከዚህ በኋላ ኅብረቱና ብሪታንያ የሚኖራቸው የንግድ ግንኙነት ላይ የሚካሄደው ወሳኝ ድርድር አልተቋጨም። ባለፈው እሁድ እልባት ያገኛል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ይኽው ድርድር አለማብቃቱ ብቻ ሳይሆን ያለ ስምምነት ሊጠናቀቅ ይችላል የሚለው  ስጋት እያነጋገረ ነው። ብሪታንያ የአውሮጳ የጋራው ገበያን ከተቀላቀለች 47 ዓመታት አልፈዋል።ይህን ያህል እድሜ ያስቆጠረው የንግድ ግንኙነት ብሪታንያ ኅብረቱን ለቃ ከወጣች በኋላ እንዴት ሊቀጥል እንደሚችል በአንድ ዓመቱ የሽግግር ጊዜ ሁለቱ ወገኖች ሲደራደሩበት ቆይተዋል። የዚህ ድርድር መጨረሻ ተብሎ የተቀመጠው ቀነ ገደብ ከትናንት በስተያ የነበረ ቢሆንም ሁለቱ ወገኖች ስምምነት ላይ መድረስ ባለመቻላቸው ድርድሩ እንዲቀጥል ተደርጓል። የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን እሁድ በሰጡት መግለጫ እንዳሳወቁት ተደራዳሪዎች ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ከተጨማሪ ጊዜ ጋር ፣ሃላፊነቱ ተሰጥቷቸዋል።
«ከብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ጋር ገንቢና ጠቃሚ የስልክ ውይይት አካሂደናል።መፍትሄ ያልተገኘላቸው ዋናኛዎቹ ጉዳዮች ላይ ተወያይተናል።ተደራዳሪዎቻችን በቅርብ ቀናት ሌት ተቀን ሲሰሩ ነበር።አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ የተካሄደው ድርድር አድካሚና ቀነ ገደቦችም የታለፈባቸው ነበር።ሁለታችንም በዚህ ወቅት ላይ ከታሰበው ተጨማሪ መንገድ መጓዙ ሃላፊነት የሚሰማው ውሳኔ መሆኑን አስበናል።ተደራዳሪዎቻችን ንግግሩን እንዲቀጥሉና በረፈደም ሰዓት ቢሆን ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ሃላፊነቱን ሰጥተናል።ድርድሩም እዚህ ብራሰልስ ይቀጥላል ።»
ፎን ዴር ላየን ድርድሩ እንደሚቀጥል ከማሳወቅ ውጭ እስከ መቼ የሚለውን ወይም ቀነ ገደቡን አልተናገሩም ።ሁለቱ ወገኖች ያልተስማሙባቸው ሦስት ጉዳዮች ናቸው። በእስካሁኑ ድርድርም በነዚህ ጉዳዮች ላይ ልዩነታቸውን ማጥበብ አለመቻላቸውን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።የብራሰልሱ ወኪላችን ገበያው ንጉሴ እንደሚለው ድርድሩ እልባት እንዲያገኝ ግፊቱ ቀጥሏል፤የተቻለው ሁሉ ጥረትም እየተደረገ ነው።ሆኖም የሁለቱ ወገኖች ንግድ እንዴት ይቀጥል የሚለው እንዲህ በቀላሉ የሚፈታ ጉዳይ አልመሰለም። 
የአውሮጳ ኅብረት የብሬግዚት ተደራዳሪ ሚሼል ባርንየ ከብሪታንያ ጋር የንግድ ስምምነት ላይ ለመድረስ ጊዜውም አልፈረደም ነው የሚሉት። በርሳቸው አስተያየት ለድርድሩ የተሰጠው ጊዜ ማጠሩ ነው ዋናው ችግር ።ያም ሆኖ ያለውን እድል ሁሉ አሟጠው መጠቀማቸው እንደማይቀር ነው ያስረዱት። 
«የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን እንዳሉት በዚህ አስቸጋሪ ድርድር  መቀጠል የኛ ሃላፊነት ነው።በአውሮጳ ኅብረት ታሪክ ከሶስተኛ አገር ጋር እንዲህ ያለ አስፈላጊ ስምምነት ላይ ተነጋግረን አናውቅም።በእቃዎች ንግድ፣በአገግሎት ዘርፍ ፣በአሳ ማስስገር በኃይል፣በትራንስፖርት በዜጎች ደኅንነት ላይ እንደዚህ ባለ አጭር ጊዜ ውስጥ ተደራድረን አናውቅም። የተደራደርነው 9 ወራት ብቻ ነው።ለነዚህ የቀደሙ ስምምነቶች በሙሉ ቢያንስ ቢያንስ አምስት ዓመት ያስፈልገን ነበር።ለዚህ ስምምነት የተገኘውን እድል በሙሉ እንጠቀማለን።አሁንም ልናደርገው የምንችል የኛ ሃላፊነት ነው።ጥሩና ፍትሃዊ ስምምነት ላይ መድረስ የኛ ሃላፊነት ነው።» 
የአውሮጳ ኅብረት አባል ሃገራትም ስምምነቱ እንዲሳካ ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት  እያሳሰቡ ነው።ማሳሰቢያውን ካቀረቡት መካከል  በዙር የሚደርሰው የኅብረቱ የወቅቱ ፕሬዝዳንት ጀርመን አንዷ ናት። 
«በርግጥ በኔ አመለካከት ውጤት ላይ ለመድረስ ሁሉንም ነገር መሞከር አለብን።ይህን በኅብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይም የኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ይህንኑ ተናግረዋል።እናም ውጤት ላይ ሊያደርስ የሚችል ማናቸውም ጥረት ከሁሉም በላይ ተቀባይነት አለው።»
ብሪታንያ ከአውሮጳ ኅብረት አባላነት ከተሰናበተች በኋላ የቀጠለው የአንድ ዓመት የሽግግር ጊዜ ከ16 ቀናት በኋላ ሲያበቃ የንግድ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ከወዲሁ ማሳሰቡ አልቀረም።ብሪታንያውያን  ከወዲሁ ስጋታቸውን እየገለጹ  ነው። እኚህ በብሪታንያ የፈረንሳይ አይብ ነጋዴ ወደፊት ሊደርስ የሚችለው የገበያ ችግር ከአሁኑ ያሳስባቸዋል።
«ከአሳሳቢዎቹ መካከል የምንከፍለው ግብር መጠን ነው።በአንዳንድ የአይብ ዓይነቶች ላይ እስከ 30 በመቶ ሊሆን ይችላል።ህዝቡ በተለይ ከኮቪድ በኋላ ይህን የመግዛት አቅም ይኖረዋል? ሃብታሙ አሁንም ሃብታም ነው።ደሃው ደግሞ ይበልጥ ደህይቷል። እናም ንግዱ እንዴት እንደሚሆን አናውቅም።(የብሪታንያ ገንዘብ) ፓውንድ ዋጋ ከቀነሰ በዩሮ ስለሆነ የምንገዛው በግብይቱ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርም ።አዎ ንግዳችንን ሊያዘጋን ይችላል።» 
እኚህ መምህር ደግሞ ስምምነት ላይ ተደረሰ አልተደረሰ ብሪታንያ ኅብረቱን ለቃ እስከወጣች ድረስ የሚመጣው ለውጥ የለም ይላሉ። 
«ውሉ ብቻውን ለኔ የሚያስገኘው ጥቅም የለም።ከቦታ ወደ ቦታ የመዘዋወር መብቴን አጥቻለሁ።ሁሉንም ነገር አጥቻለሁ ስለዚህ ከስምምነቱ የሚገኝ ትርፍ የለም።ምናልባት ለኤኮኖሚው በመጠኑ ይጠቅም ይሆናል። በአጠቃላይ ግን ለእኛ የሚያስገኝልን ጥቅም የለም። እኛ ወጥተናል»
የብሪታንያና የአውሮጳ ኅብረት የወደፊቱ የንግድ ግንኙነት ድርድር መጨረሻ ከወዲሁ ባይታወቅም ድርድሩ ያለ ስምምነት ከተጠናቀቀ ግን ጉዳቱ አስከፊ መሆኑ እንደማይቀር ነው ተደጋግሞ የሚሰማው።ድርድሩ ያለ ስምምነት ቢቋጭ ለሁለቱም ወገኖች አይጠቅምም።ሆኖም ብሪታንያ ይበልጥ ተጎጂ ልትሆን እንደምትችል ነው የሚገመተው።ገበያው
የአውሮጳ ኅብረትና ብሪታንያ በወደፊቱ የንግድ ግንኙነት ላይ መስማማት አለመቻላቸው የሚያስከትለውን ኪሳራ ማስቀረት የሚችሉበት ተስፋ ይኖር ይሆን?

Brexit | David Frost in Brüssel
ምስል picture-alliance/ASSOCIATED PRESS/F. Seco
Belgien EU-Gipfel Angela Merkel
ምስል John Thys/AP Photo/picture alliance
UK Michel Banier in London
ምስል Toby Melville/REUTERS

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ