1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ያላባራዉ የኢትዮጵያዉያን ሰቆቃ

ረቡዕ፣ መጋቢት 16 2012

በሞዛምቢክ በከባድ የጭነት ማጓጓዣ ሳጥን «ኮንቴነር» ዉስጥ 64 ኢትዮጵያዉያን ሞተዉ መገኘታቸዉ እያነጋገረ ነዉ። የኮርና ተኅዋሲ ስርጭትን ተከትሎ ሞዛምቢክ የሚያዋስንዋትን ሃገራት ድንበር ካሳወቀች እና ቁጥጥር ከጀመረ ጥቂት ጊዜያት በኋላ ሕገ-ወጥ ስደተኞቹ የተገኙት።  

https://p.dw.com/p/3a1T8
Mosambik Migration Dutzende Tote in Lkw-Container entdeckt
ምስል DW/A. Zacarias

ያላባራዉ የኢትዮጵያዉያን ሰቆቃ

 በሞዛምቢክ በቴቴ ግዛት እንዲቆም የተደረገዉ ከባድ የድረቅ ጭነት ማጓጓዣ በድንበር ጠባቂዎች እና በአካባቢዉ ላይ ፖሊሶች እንዲቆም የተደረገዉ በጥርጣሬ ነበር። ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ የሞዛምቢክ ብሔራዊ የስደተኞች ጉዳይ ቢሮ ቃል አቀባይ አሜሊያ ዲሬይቶ ሳጥን መሰሉ ከባድ የጭነት ማመላለሻ እንደቆመ ሹፊሩን ፖሊሶች ለመጠየቅ ወደ ተሽከርካሪዉ ጠጋ እንዳሉ ከኋላ የሚንኳኳ ነገር ሰሙ ፤ ነገሩ ጥርጣሪ ዉስጥ ስለከተታቸዉ ከባዱን የጭነት ተሽከርካሪ ለመፈተሽ ወሰኑ ብለዋል።  ይሁንና ሲልቪዮ አልቤርቶ የተባለዉ ሹፌሩ ከቁሳቁስ ሌላ ምንም እንዳልጫነ ቢናገርም የድንበር ተቆጣጣሪዎች እና ፖሊሶቹ ፍተሻቸዉን ቀጥለዉ ፤ በግዙፉ ተሽከርካሪ የእቃ መጫኛ ሳጥን «ኮንቴነር » ዉስጥ  64 ቱ ሕይወታቸዉ ያለፈ 14 ቱ ደግሞ በሕይወት ያሉ ወጣቶችን እንደተገኙ ተናግረዋል።  የሞዛምቢክ ብሔራዊ የስደተኞች ጉዳይ እንደገለፀዉ በጭነቱ መኪና ላይ የነበሩት በሙሉ ኢትዮጵያዉያን መሆናቸዉን ገልፆአል። የኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በጭነት ተሽከርካሪ ከማላዊ ወደ ሞዛምቢክ ሲጓዙ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያዉያን መሞታቸዉን አረጋግጫለሁ ማለቱ ተዘግቦአል።
« በማላዊ ከሊሎንግዌ ከሚባል ስፍራ እየመጣሁ ሳለ ነዉ አንድ ሰው ያስቆመኝ ከዝያም ግለሰቡ ወደ ሞቲዝ ሞዛምቢክ የሚሄዱ ሰዎች  አሉ ሲል  ነገረኝ። ሰዎቹ  ካሎውዌ  በተባለ ድንበር ላይ ነበሩ። ድንበር ላይ እንደደረስኩ፤ አንድ ሰዉ እዚህ አሁን አጠገቤ የቆመዉን ወጣት ወደ እኔ ጋ ላከዉ። ከዝያም ሰዎቹን ከሱ ጋር ሆነን አገኘናቸዉ፤ በምነዳዉ ተሽከርካሪ ተሽከርካሪ ኮንቴነር ዉስጥ አሳፈርናቸዉ»    

ሲልቪዮ በመጀመርያ 27 ሰዎችን ብቻ ነበር ለመጫን የተስማማዉ ። ለዚህ ደግሞ ሊቀበል የተስማማዉ በአንድ ሰዉ የሞዛምቢክ 30 ሺህ ሜታክልስ ነዉ ። ሲመነዘር ወደ 450 ኦይሮ ይሆናል።

Infografik Karte Mosambiks Provinzen Portugiesisch

የኮርና ተኅዋሲ ስርጭትን ተከትሎ ሞዛምቢክ የሚያዋስንዋትን ሃገራት ድንበር እንደምትዘጋ በሳምንቱ መጀመርያ ይፋ ካደረገች በኋላ የፀጥታ አካላት በሃገሪቱ ዙርያ ድንበሮች ላይ ቁጥጥር ማድረግ ከጀመሩ ጥቂት ጊዜያት ነበር።  በሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ወደ ደቡብ አፍሪቃ የተሻለ ኑሮን ፍለጋ ህልምን ሰንቀዉ ሲጓዙ የበሩት 64 ኢትዮጵያዉያን አስክሪን እና ከሞት የተረፉት 14ቱ ኢትዮጵያዉያን የተገኙትም ሞዛምቢክን ጨምሮ የዓለም ሃገራት ሁሉ ድንበራቸዉን ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንደጀመሩ ነዉ። የሞዛምቢክ የስደተኞች ጉዳይ ቢሮ ቃል አቀባይ አሜሊያ ዲሬይቶ በሞዛምቢክ እና ማላዊ መካከል የድንበር ዝዉዉር ቁጥጥር ባለመኖሩ ለሕገ-ወጥ ስደተኛ አዘዋዋሪዎች መጠቀምያ ሆንዋ ሲሉ ተናግረዋል።


በከባድ ጭነት ማመላለሻ ሳጥን «ኮንቴነር»  ዉስጥ የነበሩት 78 ወጣቶች 34 ዲግሪ ሴንቴግሬድ በነበረዉ የሞዛምቢክ አየር ሙቀት በተጨማሪ ድፍን በሆነ ሳጥን ዉስጥ በአየር እጠረት መሰቃየታቸዉ ተነግሮአል።  በሕይወት የተረፉት 14 ኢትዮጵያዉያን  የሕክምና ርዳታ እየተሰጣቸዉ ነዉ። ከዶቼቬለ አፍሪቃ ፕሮግራም ጋር ቃለ ምልልስ ያደረገዉ እና ከ 14ቱ ተራፊዎች መካከል ነዉ የተባለዉ አሪካሾ ቴሪቦ የተባለዉ ወጣት እንደተናገረዉ በጓደኛዬ ምክር የተሻለ ኑሮን ፍለጋ ነዉ  ሃገሪን ለቅቄ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለመጓዝ የወሰንኩት ብሏል። ማላዊ ከደረስን በኋላ በቀጣይ በሞዛምቢክ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለማቅናት ጉዞ የጀመርነዉ ከለሊቱ አራት ሰዓት ነበር፤ ከዛ,,,

«የጭነት ማመላለሻ እቓ መጫኛዉ ሳጥን ዉስጥ ገባን ሾፌሩም በሩን ዘጋ ። ከዝያ ምን እንደተፈጠረ አናዉቅም።  በተሽከርካሪዉ ላይ ባለዉ ሳጥን ዉስጥ የተሳፈረዉ ሁሉ ማለት ይቻላል ቀስ በቀስ እየሞተ ነበር። እነዚህ ሁሉ 64 ሰዎች በሕይወት ለመትረፍ በቂ ጊዜ አልነበራቸውም »

Mosambik Migration Dutzende Tote in Lkw-Container entdeckt - ÜBERLEBENDE
ምስል DW/A. Zacarias

ሞዛምቢክ ከጎረቤት ሃገር ሌሴቶና ዚምባቤ ብሎም እንደኢትዮጵያ ካሉ ራቅ ያሉት አፍሪቃ ሃገራት ዜጎች ወደ ደቡብ አፍሪቃ የሚሻገሩባት ሃገር ናት የሃገሪቱ ባለሥልጣናት  ጥብቅ የድንበር ቁጥጥር እንደሚካሄድ ተናግረዋል።  
የተለያዩ ሃገራትን አቋርጠዉ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ከሚያመሩ ኢትዮጵያዉያን መካከል አብዛኞቹ በየአፍሪቃ ሃገራቱ ወህኒዎች ያለ ተመልካች ታስረዉ ፤አልያም ሕይወታቸዉን አጥተዉ ፤ የአዉሬ ሲሳይ ሆነዉ ከዚህ መሰናክል ያለፉት በቪክቶሪያ ሐይቅ የዉኃ ሲሳይ ሆነዉ ከዚህ ሁሉ መሰናከል አልፈዉ ደቡብ አፍሪቃ የሚደርሱት በቁጥር ከሞቱት ከታሰሩት ጋር ሲነፃፀር እጅግ ጥቂት መሆናቸዉን ምሁራን ይናገራሉ። ደቡብ አፍሪቃም ከደረሱ በኃላ አብዛኞቹ በስቃይ ዉስጥ እንደሚኖሩ በየጊዜዉ የሚዘገብ ነዉ።

አዜብ ታደሰ