1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትአፍሪቃ

ዩኒቨርስቲ ገቢ አዲስ ተማሪዎች ጉዳይ ለምን ዘገየ?

ዓርብ፣ ግንቦት 20 2013

በዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ያነጋገርናቸው ተማሪዎች እንደገለፁልን ውጤት ከወጣ ከሁለት ወራት በኋላም እስካሁን ትምህርት አለመጀመራቸው ከፍተኛ ድብርት ውስጥ ከቷቸዋል። ጉዳዮ የሚመለከተው የሳይንስ እና ከፍተኛ የትምህርት ሚኒስቴርም ምላሽ ሰጥቶናል።

https://p.dw.com/p/3u5dy
Äthiopien Axum-Universität in der Region Tigray
ምስል DW/M. Hailesilassie

ትምህርት አለመጀመሩ ድብርት ውስጥ ከቷቸዋል

ኢትዮጵያ ውስጥ የ 2012 ዓ ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በፀጥታ እና የኮሮና ወረርሽኝ በመሳሰሉ ምክንያቶች በተያዘለት ጊዜ ሳይሰጥ መዘግየቱ ይታወሳል።  በመጨረሻም ተማሪዎቹ በ 2013 ዓ ም ፈተናውን ወስደው ውጤታቸውን አውቀዋል። ይህም ከሆነ ሁለት ወር ገደማ ሆነው። ይሁንና እስካሁን ተማሪዎቹ መቼ ወደ ዩኒቨርስቲ እንደሚገቡ አያውቁም። 
እንደ የኢትዮጵያ የሳይንስ እና ከፍተኛ የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ከሆነ ዘንድሮ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ከተፈተኑ 343ሽህ 832 ተማሪዎች መካከል 147 000 ያህሉ ወደ ከፍተኛ ተቋም የሚያስገባቸውን ውጤት አግኝተዋል። ይሁንና ተማሪዎቹ ውጤታቸውን ካወቁ ከሁለት ወራት በኋላም ትምህርት አልጀመሩም። ወጣት ፍፁም፣ ዳግማዊት እና ትንሣኤ ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። « ቀድሞውንም ሳንማር ብዙ ጊዜያችን ባክኗል» የሚለው ትንሣኤ አሁንም ጊዜው በከንቱ እየባከነ እንደሆነ ነው ባይ ነው። « ምንም እየሰራሁ አይደለም። እቤት ነው ያለሁት» የሚለው ትንሣኤ የድሬደዋ ልጅ ነው። ያለፉትን የትምህርት ዘመኖቹን መለስ ብሎ ሲቃኝ ብዙ ቁጭት አለበት። « በፊትም ትልቅ በደል ነበረብን። በሀገሪቱ የሰላም እጦት ምክንያት 12 ኛ ክፍሎች ሳንማር ብዙ ጊዜ አልፏል። 11ኛ ክፍልም እንዲሁ ረብሻ ነበር። » በመጨረሻም የኮሮና ወረርሽኝ ታክሎበት ብዙ ትምህርት እንዳመለጣቸው ትንሳኤ ይናገራል።
እንደዛም ሆኖ ትንሣኤ 523 ነጥብ በማግኘት ወደ ከፍተኛ ተቋም ማለፍ ችሏል። የዓመቱ ከፍተኛ ውጤት 669 ነው። ትንሣኤ የደረሰው የትምህርት ተቋም ሁለተኛ ምርጫው በነበረው ጎንደር ዮንቨርስቲ  ሲሆን መማር የሚፈልገው ግን በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ መሠረት ገና አልመረጠም። መማር የሚፈልገው ግን የኮምፒውተር ሳይንስ ነው።  

Äthiopien | Gonder & Wello University
ወጣት ትንሳሴ የደረሰው ጎንደር ዩኒቨርስቲ ነዉምስል Gonder & Wello University

ሌላዋ ተፈታኝ  ዳግማዊት ትባላለች። ወደፊት በአስተዳደር ወይም ማኔጅመንት ዘርፍ ብትማር ደስ ይላታል። « ውጤት ጥሩ ነበር። 420 ነው ያመጣሁት። የደረሰኝ ወልዲያ ዩኒቨርስቲ ነው»
ወልድያ ሄዶ መማር ለዳግማዊት 16ኛ ምርጫዋ ነበር። የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪ ናት። ሀዋሳ ወይም አዲስ አበባ ከተማ ደርሷት ቢሆን ትመርጣለች። ይሁንና በአሁኑ ሰዓት የሚያሳስባት የተመደበችበት ቦታ አይደለም። እሷም እንደ ትንሣኤ ከዚህ ቀደም በግጭት ምክንያት ትምህርት ሳትማር የቀረችበት ወቅት ነበር።  አሁንም ያለው ሁኔታ በጣም ያስጨንቃታል። « የስነ ልቦና ጉዳት ነው የደረሰብን። እቤት ውስጥ መቀመጥ በጣም ይደብራል» የምትለው ዳግማዊት ጊዜዋን የምታሳልፈው እቤት ውስጥ ስራ በማገዝ፣ መፅሀፍ በማንበብ እና ቤተ ክርስትያን በመሄድ ነው።
ሌላው ስጋቱን ያካፈለን ወጣት ፍፁም ይባላል። የሀዋሳ ከተማ ነዋሪው ፍፁም ከምርጫው በፊት ትምህርት ይጀመራል የሚል እምነት የለውም። « ከሁለት ሳምንት በፊት ጥሪ ተደረገልን። ከዛ ደግሞ በምርጫ ምክንያት ተብሎ ተዘዋወረ። እና ከምርጫው በኋላ ነው የሚሆነው።  ፍፁም ስራ ፈት መሆኑ በጣም ያበሳጨዋል። ፍፁምን ሌላም የሚያበሳጨው ነገር አለ። « 531 ነጥብ ሰው አምጥቶ ጥሩ ቦታ መመደብን ነው የሚጠብቀው። እኔ ግን 11ኛ ምርጫዬ ነው የደረሰኝ » በማለት በምደባው ደስተኛ እንዳልሆነ ይናገራል። 


የሳይንስ እና ከፍተኛ የትምህርት ሚኒስቴር ከሳምንት በፊት በፌስ ቡክ ገፁ ይፋ እንዳደረገው« ሁሉም ዩንቨርስቲዎች አዲስ ገቢ ተማሪዎችን እስከ ግንቦት 30/2013 ይቀበላሉ። ሰኔ 1 ፤ 2013 የአዲስ ገቢ ተማሪዎች ትምህርት ይጀመራል።» ይላል። በርግጥ ሰኔ አንድ ሁሉም አዲስ የዩንቨርስቲ ገቢ ተማሪዎች ትምህርት ይጀምሩ ይሆን? ይህስ ዮንቨርስቲው በግሉ የሚወስነው ነው ወይስ ወጥ የሆነ አሰራር አለ?  የሳይንስ እና ከፍተኛ የትምህርት ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ዳሬክተር የሆኑት ወይዘሮ አለምወርቅ ሕዝቅኤል « ምርጫውን ታሳቢ በማድረግ ከምርጫ በኋላ በአብዛኛው አዳዲስ ተማሪዎች ይገባሉ ብለን እናስባለን» ይላሉ። ትክክለኛ ጊዜውም ሊለያይ እንደሚችል እና ሁሉም ዮንቨርስቲዎች በአንድ ጊዜ ላይጠሩ እንደሚችሉ ያስረዳሉ። 
ሚኒስቴር መሥራያ ቤቱ የተለያዩ ከ 23 ሺ በላይ ቅሬታዎች እንደቀረቡለት የጠቀሱት ወይዘሮ አለምወርቅ የበርካታ ተማሪዎች ቅሬታ ምላሽ እንዳገኘ ወይም እንደተስተካከለ ይናገራሉ። ይሁንና የትምህርት ተቋም ምደባውን በሚመለከት የሁሉንም ተማሪዎች ፍላጎት ታሳቢ ማድረግ አለመቻሉን ነው ወይዘሮ አለምወርቅ ለ ዶይቸ ቬለ የገለፁት። ይህም ዩንቨርስቲዎች መቀበል ካላቸው አቅም አንፃር ነው።

Äthiopien Addis Ababa Forum der politischen Parteien
ምርጫው ለአዲስ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መዘግየት አንዱ ምክንያት ነውምስል Solomon Muche/DW


ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሠ