1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፕራይቬታይዜሽን ጉዳይ እሰጣገባዎች

ዓርብ፣ ሰኔ 14 2011

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ70ኛው የካቢኔ ውሳኔው "የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማቃናት እና ተከታታይነት ያለው ልማት ለማረጋገጥ" በሚያደርገው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ "ከመንግሥት መር ኢኮኖሚ ወደ ግሉ ዘርፍ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር" መወሰኑን አሳውቋል። ይህ ውሳኔ ለከፊሎች ጮቤ የሚያስረግጥ ዜና ሲሆን፥ ለከፊሎቹ ደግሞ ሐዘን የሚያስቀምጥ ሆኗል።

https://p.dw.com/p/3Kp4Z
180621 Kolumne BefeQadu Z Hailu

አምና ሥልጣን የተቆጣጠረው አመራር ከመጣ ወዲህ በተለይ ልኂቃኑን በእጅጉ የከፋፈለው ውሳኔ ይህ ውሳኔ ነው ቢባል የተሳሳተ አይሆንም።

‘ውሳኔ 70’ ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ?

እንደ እውነቱ ‘ውሳኔ 70’ እንደሚመጣ ይታወቅ ነበር። መንግሥት ኢኮኖሚውን ለግሉ ዘርፍ እንደሚከፍትና ግዙፍ የመንግሥት የንግድ ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታዎች እንደሚያዛውር ቀድሞ መናገሩ ይታወሳል። በተለይም ደግሞ ይህንኑ ለመከታተል የሚችሉ 21 አባላት ያሉት የፕራይቬታይዜሽን ምክር ቤት አቋቁሟል። ሆኖም ጉዳዩ እንዳዲስ አነጋጋሪ የሆነው ይህ ‘ውሳኔ 70’ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ድረ ገጽ ይፋ ከተደረገ በኋላ ነው።

በዚህ ውሳኔ አዲስ የተጨመረ ነገር የለም። ሆኖም "የለውጥ አመራሩ" ተደማጭነት እና ታማኝነት ያሽቆለቆለ/እያሽቆለቆለ በመሆኑ እና ብዙ ሰዎች ሰበብ እየፈለጉ ውሳኔዎችን መተቸት መጀመራቸው አንዱ የሰሞኑ ክርክር መንሥኤ ሲሆን፥ ሌላው ይህንኑ አጋጣሚ ተጠቅመው በፊትም የፕራይቬታይዜሽኑን ጉዳይ ሲቃወሙት የነበሩ ሰዎች እንዳዲስ አጀንዳቸውን ማራመድ በመቻላቸው ነው።

ሥጋቱ ምንድን ነው?

ሥጋቱን በርካታ ተቺዎች ደጋግመው ከሚጠቀሙባቸው ቃላት በመነሳት መገመት ይቻላል። እነዚህ ቃላት "የኒዮሊበራሊዝም ወረራ" እና "አገር ሽያጭ" የሚሉ ናቸው። በኢትዮጵያ ለግሉ ዘርፍ [ያውም በከፊል] ለሽያጭ ይቀርባሉ የተባሉት ድርጅቶች የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢትዮ ቴሌኮምን ይጨምራሉ። የተቺዎቹ ሥጋት በአጭሩ ሲጠቀለል እነዚህ ድርጅቶች ወደ ግል ሲዛወሩ የሚገዟቸው የውጭ አገር ኮርፖሬቶች ናቸው፤ ኮርፖሬቶቹ ደግሞ ትርፍ ተኮር ስለሆኑ ብዙኀኑን ድሃ አያገለግሉም። አልፎ ተርፎም የመንግሥትን እጅ በመጠምዘዝ አገሪቱን የኀያላን አገራት ወይም የኮርፖሬቶች መቀለጃ ያደርጋታል የሚለው ነው።

እንደ እውነቱ ከእነዚህኞቹ ሥጋቶች ውስጥ ገሚሱ ከብሔርተኝነት ወይም የውጭ ባለሀብት ጠልነት የመነጩ ይመስላሉ። ከዚህ ውጪ በተለይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ውጤታማ በመሆኑ ‘መሸጡ ለምን አስፈለገ?’ የሚሉ እና የ‘ፕራይቬታይዜሽን’ን አስፈላጊነት ከማኔጅመንት ችሎታ ጋር ብቻ የሚያያይዙት አሉ። የብዙዎቹ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ሥጋት ግን ድርጅቶቹን ወደ ግል ለማዘዋወር ያለው ጥድፊያ የነዚህ የመንግሥት ድርጅቶችን ዋጋ ባራከሰ እና ኢትዮጵያ የቁጥጥር ችሎታዋን ባላዳበረችበት ወቅት የሚደረግ በመሆኑ ከትርፉ ጉዳቱ ያመዝናል የሚል ነው።

በፖለቲካ ድርጅት ደረጃ፣ እስካሁን ውሳኔውን የተቃወመው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብቻ ሲሆን፥ በተለይ "ሊበራላይዜሽን ከፕራይቬታይዜሽን መቅደም አለበት" በሚል መከራከሪያ ነጻ የገበያ ፉክክር ሳይኖር በፊት ቀድሞ በብቸኝነት ገበያውን የተቆጣጠሩትን የመንግሥት ድርጅቶች ወደ ግል ማዛወር ‘የሞኖፖሊ’ አደጋ እንዳለው አመላክቷል።

እየሆነ ያለው ምንድን ነው?

የኢትዮጵያ መንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጥ እያመጣ ያለው ወዶ ሳይሆን ተገዶ ነው። ባለፉት ዐሥርት ዓመታት የተከማቸው ብድር መክፈል ከማይቻልበት ጣሪያ ላይ ደርሷል። በዚያ ላይ ብድሩን በንግድ ይመልሳሉ ተብለው የነበሩት የስኳር ፋብሪካዎች የግንባታ ገንዘባቸው በሙስና ባክኖ ቀርቷል። የባቡር ኮርፖሬሽኑም አትራፊነቱ እምብዛም ነው። በአንድ ወቅት "ገንዘብ ማተሚያ ማሽን" እና "የምትታለብ ላም" የሚል ቅፅል ሥም የተሰጠው ኢትዮቴሌኮም የራሱን ዕዳ እንኳን መክፈል አልቻለም። ስለዚህ የድርጅቶቹ ወደ ግል የመዛወር ወይም የግል ዘርፍ ንግድ ተኮር ኢኮኖሚ መገንባት ለኢትዮጵያ መንግሥት በውዴታ ሳይሆን በግዴታ የተገባበት ውሳኔ ነው።   በዚህ የዕዳ ይዞታ ምክንያት የውጭ ምንዛሬ እጥረትም አገሪቱን ለዘርፈ ብዙ ፈተና እየዳረጋት ነው። ፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃ በማጣት ምርታቸው እየተስተጓጎለ ነው። መድኀኒቶችን ሳይቀር ማስገባት ቸግሮ ብዙዎች እየማቀቁ ነው። ይሁንና የፕራይቬታይዜሽኑ ውሳኔ ተቺዎች ኢትዮጵያ ይህንን የባለዕዳነት ፈተና እንዴት መሻገር እንደምትችል አመላካች የሆነ ይኼ ነው የሚባል አማራጭ መንገዶችን ሲሰጡ አይታዩም።  

በመሠረቱ በሽያጩ ቅደም ተከተል መጀመሪያ ረድፍ ላይ ያለው ኢትዮቴሌኮም ነው። ኢትዮቴሌኮምን በተመለከተ ከ50% ጥቂት ዝቅ ያለ የባለቤትነቱን ድርሻ ለመግዛት ያሰፈሰፉ በርካታ ዓለማቀፍ የቴሌኮም ድርጅቶች በጉጉት እየጠበቁ ነው።

በረከት ወይስ መርገምት?

የውጭ ባለሀብቶች ድርጅቶቹን በባለቤትነት መያዛቸው እንደ መርገምት መታየቱ አግባብ አይደለም። ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ጎረቤቶች ቴሌኮም ድርጅቶቻቸው በውጭ ባለሀብቶች የተያዙ ቢሆኑም የሚያገኙት አገልግሎት እና አገራዊ ጥቅም ግን ከኢትዮጵያ የተሻለ ነው።

በኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ቀዳሚው ምሳሌ የቢራ ፋብሪካዎች ሽያጭ ነው። መንግሥት እጁን ከቢራ ንግድ ውስጥ ካወጣ ወዲህ የቢራ ፋብሪካዎቹ ባብዛኛው በውጭ ባለሀብቶች መያዛቸው እውነት ነው። ሆኖም ምርታቸው በበርካታ እጥፎች ጨምሮ የገበያውን ፍላጎት እያዳረሰ ነው። ፋብሪካዎቹ ተስፋፍተው ከቀድሞው ብዙ እጥፍ ለሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል። መንግሥትም ግዙፍ ታክስ ከዘርፉ እየሰበሰበ ነው። በንግድ ዓለም ከዚህ በላይ የሚፈለግ ነገር የለም።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ

ብዙዎቹ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ኢትዮጵያ ነጻ ገበያውን ከመቀላቀል ታመልጣለች ብለው አያምኑም። ነገር ግ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች ስላሉ ጊዜው አሁን አይደለም ብለው መከራከራቸውን ቀጥለዋል። የመጀመሪው ጉዳይ የቁጥጥር አቅም ነው። ብዙዎቹ ግዙፍ ኮርፖሬቶች ወደ አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ የሚሠሩትን መንገድ ለመቆጣጠር የሚያስችል ቢሮክራሲያዊ አቅም መገንባት ቸል መባል የሌለበት ጉዳይ መሆኑን አበክረው ይናገራሉ። ሌላኛው ጉዳይ የድርድር አቅም ነው። የንግድ ድርጅቶቹ  ወደ ግል ይዞታ ሲዘዋወሩ ዋጋቸውን እና ማኅበራዊ ዕሴታቸውን የሚመጥን ድርድር ማድረግ አስፈላጊ ቢሆንም በመንግሥት ዘንድ ይህ አቅም ገና አልተገነባም ብለው የሚሰጉ አሉ። ሦስተኛው የሠራተኞች መብቶች ጥበቃ ጉዳይ ነው። የውጭ ባለሀብቶችን ‘ርካሽ የሰው ኀይል አለኝ’ እያለች የምትጋብዘው ኢትዮጵያ፥ ለሠራተኞቹ መብቶች ጥበቃ ታደርጋለች ብሎ ማሰብ ይቸግራል።

መንግሥት እነዚህን ችግሮች መቅረፍ ከቻለ ብዙዎቹ ሥጋቶችም ይቀረፋሉ። ከዚህም በላይ በተለይም በዘርፉ ዕውቀት ያላቸውን እና የሚመለከታቸውን ሰዎች የሚያሳትፉ ተደጋጋሚ የውይይት መድረኮችን በማመቻቸት ሐቀኛ ውይይቶች የሚደረጉበትን መንገድ መጥረግ ይጠበቅበታል።

በፍቃዱ ኃይሉ