1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፑቲን ዕቅድ፣ዩክሬን ጦርነትና መዘዙ

ሰኞ፣ የካቲት 28 2014

ቮልድምየር ዜሌንስኪ ከፑቲን ጋር ያንድ ሐገር ልጆች ነበሩ።የሶቭየት ሕብረት።ፑቲን ስለላዉን ሲያቀለጣጥፉት ዜሌንስኪ እንደ አስራዎቹ ታዳጊ ወጣት በጨዋታ-ትምሕርቱ ሲባትል የሁለት ሐገራት ዜጎች ሆኑ።ፑቲን የሐገር መሪነቱን ሲለማመዱ፣ ወጣቱ ዜሌንስኪ ከቧልት፣ፊልም ምፀቱ ጋር ይታገል  ነበር።

https://p.dw.com/p/488d4
Bildkombo | Wladimir Putin und Wolodymyr Selenskyj
ምስል A. Gorshkov/SPUTNIK/AFP/Getty Images/Presidency of Ukraine/AA/picture alliance

ተመድ ስደተኛ ሲቆጥር፣ የሩሲያ ጦር ግድል-ድሉን ይዘረዝራል

 

ምዕራባዉያን መንግስታት በሩሲያ ላይ የሚጥሉት ማቅብ እየተበራከተ፣እየጠነከረ፣ እየከረረ ነዉ።ከነዳጅ አምራችና ሻጭ እስከ መኪና አምራቾች፣ ከባንኮች እስከ ክሬዲት ካርድ ተቋማት፣ ከወደብ አገልግሎት እስከ ሸቀጥ አመላላሽ ድርጅቶች፣ከፌስ ቡክ እስከ   ቴሌቪዢን ማሰራጪያ ጣቢያ የሚገኙ መገናኛ ዘዴዎች አንድም ከሩሲያ እየወጡ፣ ሁለቱም በሩሲያ እየተዘጉ ነዉ።የአዉሮጳ አሜሪካ ከተሞች ሩሲያን በሚያወግዙ፣ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲኒን በሚወነጅሉ ሰልፈኞች እየደመቁ ነዉ።የአዉሮጳ-አሜሪካ ፖለቲከኞች ዉግዘት ዛቻ፣ፉከራም አላባራም።ዘለንስኪም ይጮኻሉ፣ አንዱም ግን ዩክሬን ላይ የሚወርደዉን አንዲት ጥይት አላስቆመም።12ኛ ቀን።የፑቲን ስልት፣ጦርነቱና ጥፋቱ ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።
                               
ከሌኒን ረዘም ደግሞም ፈርጠም፣ ከስታሊን አጠር-ቀጠን ያሉ ናቸዉ።ልክ እንደስታሊን ኮስታራ።ቭላድሚር ቭላድሚሮቪች ፑቲን።ኮሚንዝም የምዱባን አለኝታ፣ የጭቁኖች መከታ፣ የግፉዓን መበልፀጊያ  ሥርዓት መሆኑ በሚሰበክ፣ በሚተረክበት ዘመን እንዳደገ ሩሲያዊ የሌኒን ፖለቲካዊ ቲወራ፣ የማርክስን ፍልስፍና፣ የኤንጊልስን ትንታኔ በቅጡ አንብበዋል።
በ1999 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የትልቂቱን ሐገር ትልቅ ሥልጣን ሲቆናጠጡ ግን ኮሚኒዚምን« ከዋናዉ ሥልጣኔ የራቀ፣ የዕድገትና የለዉጥ ተስፋ የሌለዉ ሥርዓት ነዉ» ማለታቸዉ ይጠቀሳል።

ግን ሰዉዬዉ ያሳስታሉ።የሚሉትን-የሚያደርጉ፣የመሰሉትን-የሚሆኑ ዓይነት አይደሉም።ባሕሪ፣ ዕድገት፣ ችሎታ፣ ሥራ ልምዳቸዉም-ብዙ የሚያስመስላቸዉ ብዙ ነዉ።አደን፣ ዋና፣ ሹፍርና፣ ተኩስ፣ ጂዶ ማን ችሏቸዉ።በዚያ ላይ ጥላቢስ ሰላይ፣የሰላዮች አለቃም ነበሩ። ፖለቲካዉንማ!!! እንደ ረዳት ከንቲባ አድፍጠዉ፣ እንደ ፓርቲ አደራጅ አዋዝተዉ፣በምክትል ጠቅላይ ሚንስትርነት አዝግመዉ ሲሻቸዉ ጠቅላይ ሚንስትር፣ ሲፍለጋቸዉ ፕሬዝደንት እየሆኑ-ከ25 ዓመት በላይ ዘወሩት።ቭላድሚር ፑቲን።በ2001 የያኔዉን የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት የጆርጅ ደብሊዉ ቡሽን ግልብ የፖለቲካ ዕዉቀት ለመረዳት ጊዜ አልወሰደባቸዉም።ቡሽ ዱራቸዉ ድረስ ጋበዟቸዉ።ሾተላዩ ጋዜጠኛ ጠየቀ።ፑቲን መለሱ። 
«ሩሲያን ልናምናት እንችላለን?-----ለዚሕ መልስ የለኝም።እኔም ራሴ ጥያቄዉን እጠይቅ ነበር።»

Ukraine | Zerstörung in der Region Zhytomyr
ምስል State Emergency Service of Ukraine/REUTERS

ለፖለቲካዉ ገራገሩ ቡሽ ግን ያስተማሪዉን ቀልብ ለመሳብ ከባልጀሮቹ እንደሚሻማ ተማሪ «እኔ ልመልስ» እያሉ መልሱን አንደቀደቁት።
                                 
«ጥያቄዉን ወድጄዋለሁ።ሰዉዬዉን አይኑን አይቻለሁ።በጣም ቀጥተኛና ታማኝ መሆኑን ተረድቻለሁ።በጣም ጥሩ ምክክር አድርገናል።የነብሱን ስሜት መረዳት ችያለሁ።ለሐገሩ በጣም ቁርጠኛ፣ የሐገሩን ጥቅም ለማስከበር የቆመ ነዉ።ላደረግነዉ ግልፅ ዉይይት በጣም አመሰግናለሁ።የዲፕሎማሲ መሸዋወድ አልነበረም።አንዱ ሌላዉን ለመጫን ያደረግነዉ ነገር የለም።ግልፅ ዉይይት ነበር።በጣም ገንቢ የሆነ ግንኙነት መጀመሪያ ነዉ።--ባላምነዉ ኖሮ ዱሬ ድረስ አልጋብዘዉም ነበር።»
ሩሲያዊዉ ዕዉቅ ጋጠኛ ሌዮኔድ ቤርሺድስኪ «ፑቲን ብሔረተኛ አይደሉም» ይላል። «ዘረኛም አይደሉም ግን ያሮጌዋ ሶቭየት ሕብረት አቀንቃኝ፣ ኢፔሪያሊስት እንጂ» ይላቸዋል።
ለቡሽ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ለወይዘሪት ኮንደሊሳ ራይስ ነገሩት የተባለዉ ግን ከሶቭየት ሕብረት መስራች ከቭላድሚር ኤሊየች ሌኒን መርሕ-ራቅ፣ የስታሊንን ቀረብ፣ የሩሲያ ኢፔሪያሊስትን መስራች የታላቁ ጴጥሮስን መርሕን ደነቅ የሚያደርጉ ይመስላሉ።
ፕዮቶር አሌክስየቭች ወይም ታላቁ ጴጥሮስ በ1700ዎቹ መጀመሪያ የዛሬዎቹን ዩክሬን፣ ቤሎሩስና የአካባቢያቸዉን ሐገራት የሚጠቀልለዉን የሩሲያን ታላቅ ግዛት የገነቡ ንጉስ ነገስት ናቸዉ።በዘመነ-ኮሙኒዝም ሌኒን ግራድ ተብሎ የነበረዉ የፑቲን የትዉልድ ከተማም በታላቁ ጴጥሮስ ስም ነዉ የተሰየመዉ።
በ2009 የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ባራክ ኦቦማ ሲያናግሯቸዉ ፑቲን ጠቅላይ ሚንስትር ነበሩ።«ፑቲን ሥራዎችን የሚሰሩት አንድ እግራቸዉን በአሮጌዉ ሥርዓት፣ ሌለኛዉን ባዲሱ አድርገዉ ነዉ» በማለት ተችተዋቸዉ ነበር ኦባማ።
ሰዉዬዉ ግን በ2014ና አሁን  ያደረጉትን እንደሚያደርጉ ኦባማ ስልጣን ከመያዛቸዉ ካንድ ዓመት በፊት በግልፅ ተናግረዉ ነበር።በ2008 የኔቶ አባል ሐገራትና የሩሲያ መሪዎች ካደረጉት ጉባኤ ጎን ለጎን ከፕሬዝደንት ጆርጅ ቡሽ ጋር ባደረጉት ዉይይት «ኔቶ ዩክሬንን አባሉ ለማድግ ከሞከረ፣  ሩሲያ ምስራቃዊ ዩክሬን በኃይል ከግዛትዋ ትጠቀልላች ብለዉ ነበር።»

በ2014 የዩክሬን መንግስት ተቃዋሚ ሰልፈኞችን የአሜሪካ ሴናተሮች፣ የብሪታንያ፣ የጀርመንና የፈረንሳይ ሚንስትሮች ኪየቭ ድረስ እየተጓዙ ደግፈዋል።በምዕራቦች ድጋፍ የተጠናከረዉ ተቃዉሞ ሰልፈኛ የቪክቶር ያኑኮቪችን መንግስት መንግሎ ሲጥል ፑቲን በ2008 የዛቱትን ገቢር አደረጉት።ክሪሚያንና ሳቫስቶፖልን ጠቀቀለሉ፣ ዶኔትስክና ሉሀንስክን ላይ ቶሎ የማይጠፋ እሳት ለኮሱ።
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ወታደሮች ባለፈዉ መስከረም ከዩክሬን ወታደሮች ጋር የጦር ልምምድ ማድረጋቸዉ ደግሞ ለፑቲን ከንቀት የከፋ መልዕክት ነበረዉ።ፑቲን በልምምዱ ማግስት ወደ ዩክሬን ያስጠጉትን ጦራቸዉን ወደ ኋላ እንዲስቡ ለማግባባት የተደረገዉ ጥረት ዲፕሎማን ከዛቻ፣ጫናን ከድርድር የቀየጠ በመሆኑ ለፍሬ አልበቃም።ፑቲን ባለፈዉ የካቲት 7 መጀመሪያ ለፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኦል ማክሮ አስጠንቅቀዉም ነበር።ጦርነት ከተጫረ አሸናፊና ተሸናፊ አይኖርም ብለዉ።
በ17ኛዉ ቀን ዩክሬን ላይ የሆነዉ ሆነ።የጥንታዊቱ አዉሮጳዊት ሐገር ታሪካዊ ሥፍራዎች፣ ከተሞች፣ኢንዱስትሪዎች፣ መኖሪያ ሕንፃዎች ይጋዩ ያዙ።ከሁሉም በላይ በላይ የዩክሬን ሩሲያን አንድነት ባይሆን-ጉርብትናን ኖሮበት የሚያዉቀዉ ዩክሬናዊ በቦምብ ሚሳዬል ይጠበስ-ይገደል፣ በበረዶ ቅዝቃዜ ይንዘፈዘፍ-ይሰደድ ገባ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከአፍቃኒስታን እስከ የመን፣ከቦስኒያ እስከ ኢራቅ፣ ከኮንጎ እስከ ደቡብ ሱዳን፣ ከሶሪያ እስከ ኢትዮጵያ እንዳደረገና እንደሚያደርገዉ ሁሉ ለዩክሬንም ርዳታ ይማፀናል።ስደተኛ ይቆጥራል።እስከ ትናንት የተሰደደዉ የዩክሬን ዜጋ ከ1.7 ሚሊዮን ይበልጣል።
ዓለም አቀፉ ድርጅት ስደተኛ ሲቆጥር፣ የሩሲያ ጦር ገድል ድሉን ይዘረዝራል።የሩሲያ ጦር ቃል አቀባይ ኢጎር ኮናሼንኮቭ ዛሬ።
 «በዘመቻዉ ባጠቃላይ 2396 የዩክሬን ወታደራዊ ተቋማት ተደምስሷል።ከነዚሕ መካከል 82 የዩክሬን ጦር ኃይል የዕዝ፣ የመቆጣጠሪያና የመገናኛ ማዕከላት፣119 S-300 መቶ፣ ቡክ M-1 እና ኦሳ የፀረ-አዉሮፕላን ሚሳዬሌች፣76 የሬዳር ጣቢያዎች፣827 ታንኮችና ሌሎች ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች፣ 84 ባለብዙ አፈሙዝ ሮኬት ማወንጨፊያዎች፣ 304 የመስክ መድፎችና ሞርታሮች፣603 ልዩ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች፣ 78 ሰዉ አልባ በራሪዎች ወድመዋል።»
 
ቮልድምየር ዜሌንስኪ ከፑቲን ጋር ያንድ ሐገር ልጆች ነበሩ።የሶቭየት ሕብረት።ፑቲን ስለላዉን ሲያቀለጣጥፉት ዜሌንስኪ እንደ አስራዎቹ ታዳጊ ወጣት በጨዋታ-ትምሕርቱ ሲባትል የሁለት ሐገራት ዜጎች ሆኑ።ፑቲን የሐገር መሪነቱን ሲለማመዱ፣ ወጣቱ ዜሌንስኪ ከቧልት፣ፊልም ምፀቱ ጋር ይታገል  ነበር።
ዜሌንስኪ እንደዘበት የገቡበት ፖለቲካ አድጦ እንዳይጥላቸዉ ከመጠንቀቅ ይልቅ ከኃይለኛ ባላንጣቸዉ ጋር መጋፈጣቸዉ ቢያንስ እስካሁን ለሚወዷት ሐገር እና ሕዝባቸዉ አልጠቀመም።
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት የዩክሬን የአየር ክልልን የሚጠብቁ ተቃጊ ጄቶች እንዲያዘምት ያቀረቡትን ጥያቄ ድርጅቱ ባለፈዉ ሳምንት ዉቅድ አድርጎታል።አምና ሰኔ ፑቲንን «ገዳይ» ያሏቸዉ የአሜሪካዉ ፕሬዝደንት ጆ ባይደንም ዘለንስኪን ይደግፉ እንጂ ጦር ማዝመቱን አልፈቀዱም።ዘለንስኪ ዛሬም ለሐገራቸዉ ይጮኻሉ።
«የወራሪዎቹ ጭካኔ፣ በሩሲያ ላይ የተጣለዉ ማዕቀብ በቂ እንዳልሆነ ለምዕራባዉያኑ ግልፅ ምልክት ነዉ።ምዕክንያቱም ወራሪዎቹ አልገባቸዉም።አልተሰማቸዉም።ዓለም ከምሩ  መቆሙን አላዩትም።ጦርነቱን ለማስቆም ቆርጦ መነሳቱን አላዩም።ከዚሕ እዉነት መሸሽ አይቻልም።ዩክሬን ዉስጥ ከሚደርሰዉ አዲስ ግድያ ማምለጥ አይቻልም።»
የሉትዌኒያ ፕሬዝደንትም የዘለንስኪን አባባል ይደግፋሉ።የቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት ትንሽ ሪፐብሊክ ሕዝብ ቁጥር የአዲስ አበባ ነዋሪን ግማሽ ቢያክል ነዉ።2.7 ሚሊዮን ነዉ።ግን የአሜሪካ መራሹ ጦር ተሻራኪ ድርጅት የኔቶ አባል ናት።ፕሬዝደንት ጊታናስ ናዉሴድ  ለዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊከን እንደነገሩት  ፑቲን በጦር ኃይል ካልተመከቱ 3ኛዉ የዓለም ጦርነት መነሳቱ አይቀርም።
«ፑቲን በኃይል ካላስቆሟቸዉ ዩክሬን ላይ አይቆሙም።ጀግኖች የዩክሬን ዜጎችን በሁሉም መንገድ መርዳት የኛ የሁላችንም የጋራ ኃላፊነት ነዉ።ሁሉንም መንገድ ስል፣ ከምሬ ነዉ።ሶስተኛዉን የዓለም ጦርነት ለማስቆም ሁሉንም አማራጭ መጠቀም አለብን ማለቴ ነዉ።ምርጫዉ የኛ ነዉ።»
 የዓለም ብቸኛ ልዕለ ኃያል ሐገር ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ምርጫዉን አልሸሸጓቸዉም።አንቶኒ ብሊከን።
                             
«ላነሱት ነጥብ፣ ትብብራችንን ማጠናከር ብቻ ሳይሆን፣ በኔቶ አማካይነት የጋራ ፀጥታችንን የምናስከብርበትን መንገድ ማጤን፣ አንዳድ ነጥቦች ላይ ዳግም ማጤን ከሚገባን ደረጃ ላይ ደርሰናል።ይሕ ሰራ መከናወን አለበት።አሁን ግን በጣም አስቸኳዩ ነገር የዩክሬን ወዳጆቻችን በዚሕ ወረራ እንዳይጎዱ መደገፍ ነዉ።ሩሲያ ይሕን የወረራ ጦርነቷን እንድታቆም ከፍተኛ ግፊት ማድረግ ነዉ።»
እስካሁን ብዙም ድምፅዋ ያልተሰማዉ ቻይና ከሩሲያ ጋር ያላት ወዳጅነት እንደማይናወጥ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሯ አስታዉቀዋል።በጦርነቱ ለተጎዳዉ የዩክሬን ሕዝብ  የቻይና ቀይ መስቀል ማሕበር ርዳታ እንደሚሰጥ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዋንግ ዪ አስታዉቀዋል።ዩክሬንን የሚያወድመዉን ጦርነት ለማስቆም ግን፣ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሩ አክለዉ እንዳሉት አብነቱ ሁለቱ ወገኖች እንዲደራደሩ ማቀራረብ እንጂ ጦርነቱን የሚያቀጣጥል ፉከራ-ቀረርቶ አይጥቀምም።
«ዉዝግቡን በሰላማዊ መንገድ ለምፍታት ሁለቱም ወገኖች ለንግግርና ድርድር  መገዛት አለባቸዉ።ለአካባቢዉ እና ለአዉሮጳ የረጅም ጊዜ መረጋጋት፣ ለፀጥታና ደሕንነት መከበር የተመጣጠነ፣ዉጤታማና ዘላቂ ሥልት መቀየስ አለባቸዉ።»
የሁለቱ ወገኖች ተወካዮች ዛሬ ለሶስተኛ ጊዜ መነጋገራቸዉ ተሰምቷል።የእስካሁኑም ሆነ የዛሬዉ ዉይይት በጦርነቱ ለተጎዳዉ ሕዝብ ሰብአዊ ርዳታ እንዲደርስ ከሚሉ ያጫጭር ጊዜ ርዕሶች ባለፍ ዘላቂ ተኩስ አቁምን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ አይደለም።የቻይናዉ ትልቅ ዲፕሎማት እንዳሉት ጦርነቱን የሚያጋግም እንጂ የሚያበርድ ድምፅም አይሰማም።

Brest Gespräche Ukraine Russland über Waffenstillstand
ምስል MAXIM GUCHEK/BELTA/AFP
Kosovo | Ukraine Protest in Pristina
ምስል Office of the President of Kosovo
Ukraine ukrainische Soldaten in Kiew
ምስል Sergei Supinsky/AFP

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ