1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«የፍትህ ሰቆቃ» ዶክመንትሪ ህጋዊና ሙያዊ ገፅታዉ

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 3 2011

በትናንትናዉ ዕለት በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን  «የፍትህ ሰቆቃ« በሚል ርዕስ የተላለፈዉ ዘጋቢ ፕሮግራም ብዙዎችን በማነጋገር ላይ ይገኛል። ፕሮግራሙ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ የሚያተኩር በመሆኑ ብዙ አሳዛኝና ለመስማት የሚከብዱ የግፍ ታሪኮች ተካተዉበታል።

https://p.dw.com/p/39ybr
Burundi, Symbolbild Folter
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Delay

«በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ ዘገባዎች ግለሰባዊ ጥፋተኝነት አያረጋግጡም»

በትናንትናዉ ዕለት በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን  «የፍትህ ሰቆቃ« በሚል ርዕስ የተላለፈዉ ዘጋቢ ፕሮግራም ብዙዎችን በማነጋገር ላይ ይገኛል። ፕሮግራሙ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ የሚያተኩር በመሆኑ ብዙ አሳዛኝና ለመስማት የሚከብዱ የግፍ ታሪኮች ተካተዉበታል።የታሪኩ ባለቤቶች ተፈፅሞብናል ብለዉ ባቀረቧቸዉ አሳዛኝ ድርጊቶች ልባቸዉ የተነካ፣ ከንፈር የመጠጡና ያዘኑ የመኖራቸዉን ያህል በዘጋቢ ፕሮግራሙ ላይ ሙያዊና ህጋዊ ገጽታዉን በማጣቀስ የተቹም አልጠፉም። ጉዳዩን በተመለከተ DW ያነጋገራቸዉ  በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና የኮሚንኬሽን መምህር  የሆኑት አቶ ዳግም አፈወርቅ  በዜጎች ላይ የደረሰዉ ግፍ አሳዛኝ መሆኑን ጠቅሰዉ ፤ይህንን ታሪክ የሰማንበትና የቀረበበት ሙያዊ መንገድ ግን ጥያቄ የሚያስነሳ ነዉ ብለዋል።

እንደ አቶ ዳግም ዘገባዉን ማነዉ ያዘጋጀዉ? መገናኛ ብዙሃኑስ እንዴት ተቀብለዉ አሰራጩት? የሚለዉም  የሚያነጋግር ነዉ።ፕሮግራሙን ጠቅላይ አቃቬ ህግ አዘጋጅቶታል ብለዉ እደሚገምቱ ገልፀዉ የራሳቸዉ ኤዲቶሪያል መመሪያ ያላቸዉ የመገናኛ ብዙሃን በሌላ መንግስታዊ መስሪያ ቤት የተሰሩ ዘገባዎችን ተቀብለዉ ማስተላለፋቸዉንም ከሙያ አንፃር ተችተዋል።

የግፍ ሰለቫዎቹን እዉነት ለማህበረሰቡ ማሳዎቅ መብትና የሚደገፍ ነዉ የሚሉት አቶ ዳግም ነገር ግን የመገናኛ ብዙሃኑ ይህን እዉነት ሚዛናዊና መካተት ያለባቸዉን አካላት በማካተት በጋዜጠኞች መሰራት ይኖርበት ነበር ብለዋል።ይህ ባለመሆኑም ዘጋቢ ፕሮግራሙ በተመረጡ ዕዉነቶች ላይ ብቻ በማተኮር በሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊጠየቁ የሚችሉ ሰዎችን ሳያካትት ቀርቷል ነዉ ያሉት።

Symbolbild Folter
ምስል picture alliance/dpa/Michelle Shephard

መገናኛ ብዙሃን ከአንድ አገር የዲሞክራሲ ተቋማት ዉስጥ ዋነኛዎቹ በመሆናቸዉም  የመንግስትና የመገናኛ ብዙሃን ግንኙነት ገደብ ተበጅቶለት ተቋማቱ ነፃ ዘገባዉም  ለጋዜጠኞች መተዉ አለበት ሲሉም ይሞግታሉ።

ዘጋቢ ፕሮግራሙ ከሙያ አንፃር ከሚነሳበት ትችት በተጨማሪ ከህግ አንፃርም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል የተባሉ አካላት ወደ ህግ በሚቀርቡበት ጌዜ በፍትህ ሂደቱ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል በሚል ጥያቄ የሚያነሱ አሉ። በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል  ተባባሪ ፕሮፌሰር  ደረጀ ዘለቀ ግን ጉዳዩ ህግን ከፖለቲካ ጋር የመደባለቅ አዝማሚያ ነዉ።

እነደ ረዳት ፕሮፌሰር ደረጀ የፍርድና የፍትህ ጉዳይ ግለሰባዊና  እያንዳንዱን ተግባር ከጥርጣሬ በላይ በሆነ መንገድ በማስረጃ ማረጋገጥን የሚጠይቅ በመሆኑ በመገናኛ ብዙሃን በሚተላለፉ ፕሮግራሞች ግለሰባዊ ጥፋተኝነትን አያረጋግጡም። ከዚያ ይልቅ ግን ተፈፀመ የተባለዉን ወንጀልና ግፍ እንዳይደገም ለህብረተሰቡ በማስተማሪያነት ማቅረቡ ከህግም ከሞራልም አንፃር ጠቃሚ ነዉ ሲሉ ገልፀዋል።

 

ሙሉ ዘገባዉን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነዉ ያድምጡ።

 

ፀሀይ ጫኔ

እሸቴ በቀለ