1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፌደራል መንግሥት ከህወሓት ጋር ይደረጋል ያለው ድርድር

ረቡዕ፣ ሰኔ 8 2014

በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ ሊደረግ የታቀደው ድርድር ሁሉንም ተፋላሚ ኃይሎች ያካተተ ሊሆን እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡ ስለቀጠለውና ምናልባትም በሰላም ሊቋጭ ይችላል ስለተባለው ጦርነት አስተያየታቸውን ያከሉት አንድ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያ ድርድሩ እንዲሳካ እውነት ላይ ሊመሰረት ይገባዋልም ይላሉ፡፡

https://p.dw.com/p/4Ckm4
Äthiopien Premierminister Abiy Ahmed im Parlament
ምስል Solomon Muche/DW

የፖለቲካ ተንታኝ አስተያየት

 

በሰሜን ኢትዮጵያ ከፍተኛ ውድመት እና ቀውስ ያስከተለው ጦርነት እንዲረግብ እና ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ ሊደረግ የታቀደው ድርድርና ውይይት ሁሉንም ተፋላሚ ኃይሎች ያካተተ ሊሆን እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ስለቀጠለውና ምናልባትም በሰላም ሊቋጭ ይችላል ስለተባለው ጦርነት አስተያየታቸውን ያከሉት አንድ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያ ድርድሩ እንዲሳካ እውነት ላይ ሊመሰረት ይገባዋልም ይላሉ፡፡

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ሴኔሳ ደምሴ እንደሚሉት በዓለም ታሪክ የየትኛውም ጦርነቶች መቋጫ ሰላማዊ የሚመጣው ድርድር ነው፡፡ «በድርድር ውስጥ ህዝብ የሚፈልገውና ለተፋላሚ ኃይላትም የሚበጀው፤ ተፋላሚዎቹ በሰጥቶ መቀበል መርህ የመጀመሪያ አማራጭ ብቻ ላይ ከመቸንከር አልፎ ሁለተኛ ምርጫቸውንም መመልከት ይኖርባቸዋል» ብለዋልም፡፡ የአደራዳሪ ሚናም የማይናቅ ነው ያሉት የፖለቲካል ሳይንስ ባለሙያው፤ በአፍሪካ ህብረት ተወክለው የድርድር ሂደቱን ለማሳካት ከሚጥሩት የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሌሴንጎን ኦባሳንጆ በተጨማሪ ተፋላሚ ኃይላት የድርድር ኮሚቴን ከማዋቀር ጀምሮ የድርድሩ ተሳታፊ መሆን ይኖርባቸዋል ሲሉም አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡

በዚሁ ጉዳይ አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላው ፖለቲከኛ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ትዴፓ ምክትል ሊቀመንበር አቶ መስፍን ተስፋዬ የሚደረገውም ሆነ ሊደረግ የታቀደው ድርድር ግልጽነት ሊኖረው እንደሚገባ ነው አስተያየታቸውን የሰጡት፡፡ አቶ መስፍን «ድርድሩ ግልጽነት ይጎድለዋል፡፡ ተደራዳሪዎቹ በይፋ ኮሚቴ አዋቅረው ቅድሜ ሁኔታዎቻቸውን ማስቀመት ይኖርባቸዋል» ባይ ናቸው፡፡

 የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በሚደረገው ድርድር የትግራይ ሠራዊትን ትጥቅ ማስፈታት ለድርድር አይቀርብም ሲሉ፤ የድርጅቱ ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው በድርድሩ የትኛውም የቀድሞ የትግራይ ግዛት ከትግራይ ውጪ አይሆንም ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ከሰሞኑ  ለዓመታት ምዕራብ ትግራይ በሚል ሲተዳደር የነበረው የወልቃይት መሬት ለድርድር እንደማይረብ ተናግረዋል፡፡ የሆኖ ሆኖ የፌዴራል መንግሥት ከህወሓት ጋር በስውር ተወያይቷል መባሉን ትናንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ  አጥብቀው የተቃወሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ የድርድር ሂደቱን የሚያሳልጥ ኮሚቴ መቋቋሙን ግን በይፋ ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለምክር ቤት መንግሥታቸው ጦርነቱን በሰላም ለማብቃት ፍላጎት እንዳለው ካሳወቁ በኋላ በህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ተፈርሞ የተሰራጨው ደብዳቤም በኬንያ መንግሥት አሸማጋይነት በሚካሄድ ድርድር ላይ ለመሳተፍ የህወሓትን ዝግጁነት ገልጿል።

ስዩም ጌቱ 

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር