1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፈጠራ ህልሙን ለማሳካት የሚታትረው ወጣት

ረቡዕ፣ ኅዳር 8 2014

ወጣት ዮሴፍ ጌታው ይባላል።ተወልዶ ያደገው ሰሜን ሸዋ ዞን በረኸት ገጠር ቀበሌ ሲሆን፤ በሙያው መካኒክ ነው። ከልጅነት ዕድሜው ጀምሮ የተበላሹ የኤለክትሪክ ዕቃዎችን መጠጋገ ያሚያዘወትረው ዮሴፍ፤ በግሉ ባደረገው ጥረት የብረታ ብረት ብየዳ  ስራ በመልመድ አወሮፕላንን ጨምሮ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል።

https://p.dw.com/p/436X9
Äthiopien | Junger Erfinder | Yosef Getaw
ምስል Yosef Getaw

አወሮፕላንን ጨምሮ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን ሰርቷል


በኢትዮጵያ በርካታ ወጣቶች የዕለት ተዕለት ህይወትን ሊያሻሽሉ እና የሀገርን ኢኮኖሚ ሊያሳድጉ የሚችሉ  የፈጠራ ስራዎችን ሲያቀርቡ ይታያል። ሆኖም ግን ፈጠራዎቻቸውን ወደ ተግባር እና ወደ ገንዘብ መቀየር ቀላል አይደለም። የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጀት የፈጠራ ስራዎቹን ወደ ተግባር ለመቀየር ጥረት ከሚያደርግ  ወጣት ጋር ቆይታ አድርጓል ።
ወጣት ዮሴፍ ጌታው ይባላል።ተወልዶ ያደገው ሰሜን ሸዋ ዞን በረኸት ገጠር ቀበሌ ነው።በ20ዎቹ መጀመሪያ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ይህ ወጣት፤ ምንም እንኳ  በትምህርት የተደገፈ ባይሆንም  በሙያው መካኒክ ነው። ከልጅነት ዕድሜው ጀምሮ ከትምህርቱ ጎን ለጎን  የተበላሹ የኤለክትሪክ ዕቃዎችን መጠጋገን ያዘወትር እንደነበር የሚገልፀው  ዮሴፍ፤ በግሉ ባደረገው ጥረት የብረታ ብረት ብየዳ  ስራ በመልመድ ይህንን ችሎታውን ተጠቅሞ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል።
በዚህ ሁኔታ ወደ መካኒክነት ስራ የገባው ወጣቱ  ራሱ የሚጠቀምባትን በአይነቱ የተለዬ ሞተር ሳይክል በመስራት ነበር የፈጠራ ስራውን የጀመረው።
ቆይቶም ለግንባታ ስራ የሚያገለግሉ የተለያዩ ሞዴል ተሽከርካሪዎችን እንዲሁም  ከሶስት ዓመት በፊት ደግሞ ሞዴል  አውሮፕላን መስራቱን ገልጿል።ቀስ በቀስም ይህንን ሞዴል አውሮፕላን በማሻሻል መሬትን ለቆ የተወሰነ ከፍታ መብረር እንዲችል ማድረጉን ያስረዳል።
«በመጀመሪያ ትንሽ ሞዴል አውሮፕላን ነበር የሰራሁት አስታውሳለሁ።ከዚያ ሙያየን ተጠቅሜ መስራት እንደምችል ገባኝ ።ከዚያ ሞዴሎቹን ከፍ እያደረኳቸው ሄድኩና በትልቁ ሰው የሚጭን አውሮፕላን መስራት እንደምችል ራሴን አሳምኜ ከዚያ ወደ ትልልቅ አውሮፕላን ገባሁ።ብዙ ነበር የሞከርኩት። ቪዲዮ ላይ ያለው ቢያንስ ለአምስተኛ ጊዜ ነው።ከዚያ በፊት ብዙ የሞከርኳቸው አሉ።» ካለ በኋላ «አውሮፕላኗን ራሴ ነኝ ያበረርኳት።ወደ አራት ሜትር ያህል ከፍታ ነበር የተነሳችው።ነገር ግን ብዙ ስዓት አልቆየሁም አየር ላይ። ቢያንስ ሶስት ደቂቃ ምናምን ነው የበረረችው።»በማለት የበረራ ሙከራውን ገልጿል።በገንዘብና በቁሳቁስ እጥረት ሌላ ተጨማሪ ሙከራ ለማድረግ አለመቻሉንም ተናግሯል።
ወጣቱ ወደ አውሮፕላን ፈጠራ  የተሳበው ከትውልድ ቀየው በቅርብ ርቀት በምትገኘው አረርቲ ከተማ  ይመለከታቸው ከነበሩ ሳይንስ ቀመስ ፊልሞች መሆኑንም ይገልፃል። ለዚህ ይረዳው ዘንድም  በተለይ «ፍላይ ቦይ» የተሰኘውን የላያት ሳሚ ፊልም ደጋግሞ ተመልክቷል።

Äthiopien | Junger Erfinder | Yosef Getaw
ምስል Yosef Getaw
Äthiopien | Junger Erfinder | Yosef Getaw
ምስል Yosef Getaw

«የዚያኔ ኢንተርኔት አልጠቀምም ነበር።ፊልም ላይ «ኖርማል» አውሮፕላን አየሁ።እኔ ከክፍለሀገር ነው ወደ ከተማ የመጣሁት የገጠር ልጅ ነኝ።ፊልም ላይ አውሮፕላን መኪና ሳይ በጣም ነበር ደስ የሚለኝ።እና የብየዳ ስራ ከቻልኩ በኋላ የአሁኑን ሞዴል አውሮፕላን የሰራሁት መጀመሪያ ከዚያ  አንፃር ነው።,«ፍላይ ቦይ» የሚለው የጦርነት ፊልም ነው ።እና እሱን ፊልም አውሮፕላኖች ስለነበሩት በተደጋጋሚ አየው ነበር።»ብሏል። 
ይሁን እንጅ ወጣቱ እንደሚለው የአውሮፕላን ስራውን የበለጠ ለማሻሻል የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን በቀላሉ ማግኘት ባለመቻሉ ስራውን መቀጠል አልቻለም። በመሆኑም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  የአውሮፕላን ስራውን ገታ አድርጎ  ለፈጠራ ስራዎቹ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን ለመግዛት የሚያስችል ጥሪት ለመቋጠር ፊቱን ገንዘብ ወደሚያስገኝ  የፈጠራ  ስራ ማዞሩን ገልጿል።በቅርቡም  በኮምፒዩተር የሚደረግን የመኪና ውድድር ጨዋታ መቆጣጠሪያ ወይም «ጌም ኮንትሮል»ሰርቷል።
ዮሴፍ እንደሚለው ይህ ፈጠራ  መኪና መንዳት ለሚለማመዱ ሰዎች  ጭምር የሚያገለግል ሲሆን፤ ይህንን የፈጠራ ስራውን ወደ ገበያ በማስገባት ገንዘብ እንዲያመጣ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ነው።
በሌላ በኩል ተወልዶ ባደገባት የገጠር ቀበሌ በግብርና ስራ የሚተዳደሩት ቤተሰቦቹ  በዘርፍ የሚያጋጥማቸው  ችግር እንዲሁም አሁን በሚኖርባት አረርቲ ከተማ የሚታየው  የኤለክትሪክ ችግር ከፍተኛ መሆኑን የሚናገረው ወጣት ዮሴፍ፤ ችግር የፈጠራ ስራ መነሻ ነውና የኤለክትሪክ ሀይል ተደራሽነትን እንዲሁም የግብርናውን ዘርፍ  የሚያሻሽሉ  የፈጠራ ሀሳቦች እንዳሉትም አጫውቶናል።
የፈጠራ ስራዎቹን የሚሰራው ከአካባቢው ከሚገኙ ርካሽና የወዳደቁ ነገሮችን በመጠቀም ሲሆን፤ዮሴፍ እንደሚለው ሰው ዓልቫ አውሮፕላን ለመስራት ሞክሮ የሚሰራበትን ቁሳቁስ በቅርብ ማግኘት ባለመቻሉ ለጊዜው አቋርጦታል። በአንድ ወቅትም ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር በመሆን ጨረቃ ላይ የሚነዳ ሰይክል ለመስራት የፈጠራ ንድፈ ሀሳብ በመቅረፅ በየአመቱ በሚዘጋጀው የናሳ የሮቦት ውድድር ላይ ለመሳተፍ ሞክሮ በቪዛ ችግር ሳይሳተፍ መቅረቱን ገልጿል።
ወጣቱ እነዚህን የመሳሰሉ ብዙ የፈጠራ ሀሳቦች  ቢኖሩትም ኑሮውን ለመደጎም ከሚሰራው የመካኒክነት ስራ የሚያገኛትን ትንሽ ገንዘብ ለቁሳቁስ መግዣ በመጠቀም በትርፍ ጊዜው አቅሙ የፈቀደለትን ብቻ ነው እየሰራ ያለው።
ለወደፊቱ  ግን አሁን ያለበት ሁኔታ ተቀይሮ የፈጠራ ስራዎቹን ወደገንዘብ በመለወጥ እና የገንዘብ አቅሙን በማጠናከር ሀገርንና ወገንን የመጥቀም እንዲሁም፤ የራሱ ትልቅ የምርምር ድርጅት የማቋቋም ህልም አለው።

Äthiopien | Junger Erfinder | Yosef Getaw
ምስል Yosef Getaw
Äthiopien | Junger Erfinder | Yosef Getaw
ምስል Yosef Getaw
Äthiopien | Junger Erfinder | Yosef Getaw
ምስል Yosef Getaw

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።


ሂሩት መለሰ
ፀሀይ ጫኔ