1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፈጠራ ባለሙያዎችን ማን ይደግፍ?

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 26 2014

በኢትዮጵያ በርካታ ወጣቶች ሀገርን ሊያሳድጉ የሚችሉ የፈጠራ ስራዎችን ሲሰሩ ይታያል።በዚያው ልክ በገንዘብ እጥረት የተነሳ ስራዎቻቸውን ወደ ምርት እና አገልግሎት መቀየር ያልቻሉ ብዙዎች መሆናቸው ይነገራል።

https://p.dw.com/p/4Amnq
Logo Äthiopien Ministerium für Innovation und Technologie

«የችግሩ ምንጭ የሀገሪቱ የፋይናንስ ስርዓት ነው»


ፈጠራ እና ቴክኖሎጅን የማሻሻል ስራ ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ወሳኝ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በማደግ ላይ ያሉ  ሀገራት  ጤናን፣ትምህርትን፣ መሰረተ ልማቶችን ፣የአመራረት ዘዴን እንዲሁም የዕለት ተዕለት ህይወትን በማሻሻል ድህነትን ለመቅረፍ  የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው።
አዳዲስ የቴክኖሎጅ ፈጠራዎች ለሀገር እድገት ካላቸው ጠቀሜታ በመነሳትም መንግስታት በየሀገሮቻቸው ለሚገኙ የፈጠራ ባለሙያዎች  ትኩረት በመስጠት ቀጥተኛ  የገንዘብ ድጋፍ፣ የቀረጥ ማበረታቻዎች፣ የአእምሮአዊ ንብረት ጥበቃ በማድረግ እና በዩኒቨርሲቲዎች እና በግሉ ዘርፍ መካከል የትብብር ግንኙነቶችን በመፍጠር የስልጠና ድጋፍ ሲያደርጉ ይታያል።
ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ግን በርካታ ወጣቶች ሀገርን ሊያሳድጉ የሚችሉ የፈጠራ ስራዎችን ሲሰሩ ቢታይም፤  የፈጠራ ስራዎቻቸው ወደ ምርት እና አገልግሎት ለመቀየር የገንዘብ እጥረት  ከፍተኛ ማነቆ መሆኑ ከዚህ ቀደም በዚህ ዝግጅት የፈጠራ ስራዎቻቸውን ባስተዋወቁ  ወጣቶች ተደጋግሞ ተነስቷል።ለአብነት ያህል በዚህ ዝግጅት የፈጠራ ስራዎቹን ያቀረበው እና በገንዘብ ድጋፍ ማጣት ስራዎቹን ወደ ምርት መቀየር ያልቻለውን ወጣት በረከተአብ ምህረተአብን መጥቀስ ይቻላል።  
ይህንን የወጣቶቹን ችግር  መሰረት አድርገን ያነጋገረናቸው በኢትዮጵያ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚንስቴር የኢኖቬሽን ልማት እና ምርምር ዘርፍ ዳይሬክተር ጄነራል የሆኑት አቶ ሰላምይሁን አደፍርስ ችግሩን እሳቸውም በተደጋጋሚ የሰሙት እና በተጨባጭ ያለ ችግር መሆኑን ገልፀው፤ ችግሩ የሚመነጨው ከሀገሪቱ የፋይናንስ ስርዓት መሆኑን ይገልፃሉ። 
በዚህ የተነሳ የፈጠራ ባለሙያዎች በውድድር እንደ ዓለም ባንክ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት መርሃ ግብር ከመሳሰሉ ድርጅቶች ከሚገኙ ሽልማቶች  እንዲሁም ከመንግስት አልፎ አልፎ ከሚገኝ አነስተኛ የገንዘብ ድጋፍ በዘለለ የፈጠራ ባለሙያዎችን በቀጥታ በገንዘብ መደገፍ እንዲሁም ብድር መስጠት ሳይቻል ቆይቷል ይላሉ።ይህንን በመገንዘብም ችግሩን የሚፈታ አዋጅ በመዘጋጄት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት አዳዲስ  የቴክኖሎጂ  ፍጠራዎች በሽታን፣ ድህነትን እና ረሃብን  ለመዋጋት አዳዲስ መፍትሄዎችን በማምጣት ትልቅ እድሎችን የሚፈጥሩ በመሆናቸው በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት በፈጠራ ላይ ጥገኛ ናቸው።በሌላ በኩል ፈጠራ ቁጥሩ እየጨመረ ለመጣው ወጣት አዳዲስ የስራ ዕድሎችን ለመፍጠርም ያግዛል። ያም ሆኖ ፈጠራ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያስገኝ ክህሎትን በሚያሳድጉ ስልጠናዎች መታጀብ አለበት።ከዚህ አንፃር የፈጠራ ባለሙያዎችን በስልጠና ለመደገፍ  ምን እየተሰራ ነው?  ለሀላፊው ያነሳንላቸው ሌላው ጥያቄ ነበር።ሃላፊው ሲመልሱ በተቻለ መጠን መስሪያቤታቸው በተለያየ መንገድ ለፈጠራ ባለሙያዎች የአቅም መደገፍ ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 
በመንግስት ከሚነሳው በቀጥታ የገንዘብ ደጋፍ አና የብድር አቅርቦት ችግር ባሻገር የግል ባለሀብቶችም ቢሆኑ አዋጭነቱን በመስጋት በፈጠራ ስራ ላይ ደፍረው መዋዕለ ንዋይ ሲያፈሱ አይታይም።አዋጁ ይህንንም የሚመለስ መሆኑን ሃላፊው ግልጸዋል።
በአጠቃላይ ፈጠራ በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ያለውን ተፅዕኖ ለማሳደግ ፖሊሲዎችና አዋጆችን  ከማውጣት ባለፈ የፈጠራ ባለሙያዎችን ከባለሀብቶች ጋር የሚያገናኝ  ድልድይ በመፍጠር፣ፈጠራን ወደ ምርት ለማስገባት ብድር በመፍቀድ፣ በአነስተኛ እና ጥቃቅን ኢንደስትሪዎች እንዲንዲሳተፉ  በማድረግ የፈጠራ ባለሙያዎችን  በተግባር መደገፍ እና ለሀገር በቀል ፈጠራዎች የተሻለ መደላድል መፍጠር በፈጠራ ኢኮኖሚን ለማሳደግ ከሚፈልግ መንግስት የሚጠበቅ  ነው።በአፍሪቃ በፈጠራ ስራ በ1ኛ ደረጃ የምትጠቀሰው ሞሪሸስ  እንዲሁም ጎረቤት ሀገር ኬንያን የመሳሰሉ ሀገራት ልምዶች የሚያሳዩትም ይህንኑ ነው እና።

Äthiopien, Habtamu Abafogi
ምስል Privat
Äthiopischer Erfinder Bereketab Mihiretab
ምስል Privat

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።


ፀሀይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ