1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፀጥታና ደኅንነት ጉዳይ በጨፌ ኦሮሚያ ጉባኤ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 13 2014

የኦሮሚያ ክልልን እጅግ በብርቱ ፈትኖታል የተባለው የፀጥታ ችግር በጨፌ ኦሮሚያ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ 1ኛ ዓመት 6ኛ የሥራ ዘመን ዋና ጥያቄ ኾኖ ተነሳ። ጉባኤው በትናንትናው እለት እና ዛሬ በአዳማ/ናዝሬት ከተማ ጨፌ አዳራሽ ሲካሄድ ቆይቷል። ክልሉን በተለይ ባለፉት ስድስት ወራት ፈትነው የቆዩት የሰላምና ፀጥታ እንከኖች ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል።

https://p.dw.com/p/48q06
Äthiopien | Chaffee Oromia Konferenz
ምስል Seyoum Hailu/DW

«መንግስት ርምጃ የሚወስድበት መንገድ ያዝ ለቀቅ የሚል ነው» ከተሳታፊዎች አንዱ

የኦሮሚያ ክልልን እጅግ በብርቱ ፈትኖታል የተባለው የፀጥታ ችግር በጨፌ ኦሮሚያ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ አንደኛ ዓመት ስድስተኛ የሥራ ዘመን ዋና ጥያቄ ኾኖ ተነሳ። ጉባኤው በትናንትናው እለት እና ዛሬ በአዳማ/ናዝሬት ከተማ ጨፌ አዳራሽ ሲካሄድ ቆይቷል። የክልሉ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ባለፉት ስድስት ወራት ክልሉን ፈትኖት የቆየ ስላሉት የሰላምና ፀጥታ እንከኖች ማብራሪያ ሰጥተዋል። የጨፌ አባላቱ በበኩላቸው ለአቶ ሽመልስ አስተዳደር ባቀረቡት ጥያቄ የሰላምና ፀጥታ ችግሩን ቀዳሚ ትኩረት በመስጠት አምርረው ብርቱ ጥያቄዎችን አንስተዋል። ዛሬም ጉባኤውን ሲያካሂድ የዋለው ጨፌ ኦሮሚያ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ በማጽደቅ እና ሹመቶችን በመስጠት ከሰዓት በኋላ ተጠናቋል።

ትናንት በተጀመረው የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ጨፌ ኦሮሚያ በመጀመሪያው ምዕራፍ የክልሉ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ያቀረቡትን የባለፉት ስድስት ወራት የመንግስት ሥራ ክንውን ነው ያደመጠው። ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዚሁ ሪፖርታቸው ትኩረት ሰጥተው ካብራሩት አንደኛው ክልሉን ባለፉት ስድስት ወራት ፈትኖት የቆየው የሰላምና ፀጥታ እንከኖች ይገኛል። በዚህ ረገድ ክልሉን ያጋጠመው የፀጥታ ችግር አሳፋሪ ነው ያሉት አቶ ሽመልስ ፈተናውን ለመቋቋም ግን አመርቂ ያሉት ውጤት መመዝገቡን ነው ያመለከቱት። የፀጥታ መዋቅሩን በትጥቅ ማጠናከር እና መዋቅሩን መሸፈን ከዚህ ውስጥ ተጠቃሽ ነውም ብለዋል። አክለውም በሪፖርታቸው ከትግራይ ክልል ውጭ ከሁሉም የአገሪቱ 9 ክልሎች ጋር የሚዋሰነውን የኦሮሚያ ክልል ከአጎራባች ክልሎች ሕዝቦች ጋር በሰላም መኖር እንዲቻል ሰፊ ያሉት ሥራ መሠራቱንም ጠቁመዋል። በተጠቀሰው የሥራ ጊዜ በግብርና፣ ትምህርትና ጤናን የመሳሰሉ የአገልግሎት ዘርፍ እድገት ላይም ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ ውጤትም ማስመዝገቡን ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው አካተዋል። 

Äthiopien | Chaffee Oromia Konferenz
ምስል Seyoum Hailu/DW

ከሪፖርቱ በኋላም የጨፌው አባላት ለአቶ ሽመልስ አስተዳደር ባቀረቡት ጥያቄ የሰላምና ፀጥታ ችግሩን ቀዳሚ ትኩረት ሰጥተው አምርረው አንስተዋል። «በሪፖርቱ እንደ ክልሉ ያሉብን እንከኖች የተነኩም አይመስለኝም። የኦሮሞ ሕዝብ ሕይወቱን ሲሰጥባቸው የነበሩ በርካታ ጥያቄዎች ነበሩ። የአዲስ አበባ ጉዳይ ከዚህ ውስጥ ተጠቃሽ ነው። ከመልማት ጥያቄ ጋርም ተያይዞ እኔ ከመጣሁበት ምዕራብ አርሲ ዞን ሲራሮ ወረዳ አንድ ጀሪካን ውኃ ኅብረተሰቡ 100 ብር እየገዛ ነው እየጠጣ ያለው። በየጊዜው የፕሮጀክቶች እቅድ ይወጣሉ ሲተገበሩ አናይም። የሚሠሩ ፕሮጀክቶች ጥራትም ጥያቄ የሚነሳበት ነው። የክልሉ መንግስት ወረድ ብሎ በማየት የሐሰት ሪፖርትን ማስወገድ አለበት። ሕዝብ የመረጠን እኮ ውኃ ለመጠጣት በሰላም ተኝቶ ለማደር ነበር። እያልኩ ያለሁት ሕዝቡ አሁን ተኝቶ እያደረ አይደለም ነው።»

«እንደ ዞናችን ያለንበት ችግር አሰቃቂ ነው፡፡ መውጫ መንገድ እኮ የለንም። ዞን ከወረዳዎች ወረዳ ከወረዳ መገናኘት ፈተና ከሆነ ሰነባብቷል። ይሄን አስከፊ የፀጥታ ችግር የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እንዴት ነው የሚመለከተው። በተለየም የፀጥታ መዋቅር አመራሩን እንዴት ይመለከተዋል የምለውን ለማንሳት እወዳለሁ። በርግጥ እንደለውጥ አመራር ይህ መንግስት ከውስጥ እና ከውጪ ብርቱ ፈተናን ተሻግሮ እዚህ መድረሱን እረዳለሁ። ኦነግ ሸኔ የመንግስት የፀጥታ ኃይልን ይገዳደራል የሚል እምነት የለንም። ችግሩ መንግስት ርምጃ የሚወስድበት መንገድ ያዝ ለቀቅ የሚል ነው። ይሄ ደግሞ እፎይታ ይሰጣቸዋል። ከነጌለ ወደ ደሎ የሚመጣው መንገድ በታጣቂው ተቆርጧል። ሕዝብ ይዘረፋል የተዘረፈ ደግሞ ከዚህ ዞን አይወጣም። አንድ ምሳሌ ላንሳ። የሕወሓትን ወረራ በአማራ እና በአፋር ሲገታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኮ ምሽግ ሲገባ ጦሩን ከአፍሪካ አሊያም ከአውሮፓ አይደለም ያመጣው። ሄዶ ውስጥ ያለውን ችግር አስተካክሎ ነው በሁለት ሳምንት ሰላም የመለሰው። እኛ ጋ ፀጥታ አመራር ላይ ማስተካከያ ለምን ጠፋ፤ ሦስት ዓመታት በሙሉ።»

Äthiopien | Chaffee Oromia Konferenz
ምስል Seyoum Hailu/DW

«የመንግስት ፀጥታ ኃይል ቀን ውሎ ማታ ሲወጣ ሌሊቱን በተራው ሕዝቡ በታጣቂዎች ሲደበደብ ያድራል። ሕይወት እኮ ቀዳሚው ነገር ነው። ሕይወቱን ነው ሕዝባችን እያጣ ያለው። ክቡር ፕሬዝዳንታችን ልክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንዳደረጉ ሁሉ ወጥተው ይህን ዞናችንን ከፀጥታ ስጋት ሊያፀዱልን ይገባል። እኛም ከጎንዎ እንቆማለን። የወከለን ሕዝብ እያለቀ ስለሆነ ከጎንዎ ያሉትን አስተካክለው አብረን እንነሳ ነው የምንልዎት። የጉጂ ህዝብም ከጎንዎ ይቆማል። በፊት በፊት ሴት ነበር የሚጠልፉ ይባላል። አሁን ግን ወንድ እየጠለፉ ሚሊዮኖች ጠይቃሉ። ይሄ ፈፅሞ ከባህላችን ጋር የሚጋጭ ሰምተንም የማናውቅ ሰቅጣጭ ነገር ነው። ብሩን እዚህ አዲስ አበባ እየመጡ ቤት እየገዙበት ነውም ይባላል። ተቀበሉዋቸው ስትሉን ነበር የተቀበልናቸው። አሁን በቃን። ከመሃላችን ይውጡ። እኛ የምንለው አገራችን በሌቦች አይፍረስ ነው። መንግስት ርምጃ ይውሰድ።»  

ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የክልሉ ፀጥታ አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሻፊ ሁሴን ርምጃዎቹ የዘገዩበትን ምክንያት በመግለጽ ነው ማብራሪያቸውን የጀመሩት፡፡ 
«ይህ ችግር ለምን ዘገየ የምለውን በተለያየ መንገድ ተመልክተናል። አንደኛ ይህን ኃይል ጠላትነቱን አውቀን የምንዋጋበት መንገድ በራሱ ልዩነት አለው። ለምሳሌ ከምዕራብ ቄሌም ወለጋን ብንወስድ የዚህ ኃይል ጭካኔ እዚያ ይጠነክራል። ይሁንና የአከባቢ አመራር የወሰደው ርምጃ ተምሳሌት ያለው ነው። ኢሉባቦር፣ ጅማ፣ ባሌ እና ሀራርጌም እንደዚሁ። ሌሎቹ ጋ ይሄ ቆራጥነት እንደሌለ ገምግመናል። የፀጥታ መዋቅራችን ላይም የሚነሳ ትያቄ አለ። እውነት ለመናገር የፀጥታ መዋቅራችን ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት 2-3 ዓመታት መራር መስዋዕትነት እከፈለ ነው። ግን ደግሞ ማስተካከያ ሲወሰድ ነበር ይወሰዳልም። በቅርቡ እንኳን በሰሜን እና ምዕረብ ሸዋ፣ በምስራቅ ወለጋ በተወሰደ ርምጃ ተስፋ ሰጪ ውጤት ተገኝቷል። በየደረጃው ያለን ሁላችንም ከተባበርን ለክልላችን መፍትሄ ይመጣል።» 

Äthiopien | Chaffee Oromia Konferenz
ምስል Seyoum Hailu/DW

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው የፀጥታ ችግሩ ትኩረት አለመነፈጉንና አሁን ላይ ለሽምቅ ውጊያ ምላሽ መስጠት በሚቻልበት መንገድ ላይ ክልሉ ከፌዴራል መንግስት ጋር እየሰራ ነው ብለዋል። «ከ2010 በፊት ያልነበረ የሸነ ትጥቅ አሁን ከየት መጣ።፡ የኦሮሞ ሕዝብ በሚሊየን ሲፈናቀል የት ነበሩ። ለተከበረው የጨፌ አባላት ማለት የምፈልገው ይህን ያደረገው የጠላቶቻችን ቅንጅት ነው። በዚህ ውስጥ ነገሩ የሕዝብ ትግል መስሏቸው የተሳተፉን አሁንም እንቀበላቸዋለን። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አሁንም ቢሆን ለየትኛውም ሰላማዊ መንገድ በሩ ክፍት ነው። በግልጽ መናገር የምፈልገው የጦር አመራርን ለማውጣት ጊዜ የሚወስድ ተግባር መሆኑ ፈትኖናል። የፀጥታ ኃይላችን ለከፈለው መስዋዕትነትም ዕውቅና መስጠት ያስፈልጋል። አሁንም ጠመንጃ ብቻ ሳይሆን ለችግሮቻችን መፍትሄው ፖሊካዊ ነው ብለን እናምናለን። በመሆኑ ወርደን ከሕዝብ ጋር እንሠራለን። ሸማቂን ደግሞ መዋጋት የሚቻለሁ የሚጠቀምበትን ስፍራ ማጥበብ ከዚያም ማጥፋት ነው።፡ እቅዶች አሉን በወራት ውስጥ ለውጥ እንደምናምጣ እንተማመናለን። የፌዴራል መንግስት ፀጥታ ኃይል በዚህ ላይ ልምድም ስላለው አሁን አቅጣጫ ተቀምጦ ወደ ተግባር ይገባል በቤታችን ያለውን ኩርፊያ እንደምንፈታ አምናለሁ።»

ጨፌው ከፀጥታ ችግሩ በተጨማሪ የኑሮ ውድነት፣ የመሰረተ ልማቶች ዝርጋታ፣ ሕገወጥ ግንባታ እና ሌብነት እንዲሁም ስራ አጥነት እና ሌሎችም ጉዳዮችን አንስቶ መክሮበታል። ድርቅ ያስከተለው የርሃብ ስጋትን ጨምሮ 4.8 ሚሊየን ሕዝብን በክልሉ ለርዳታ ዳርጓል የተባሉ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ፈተናዎችም ለውይይቱ ቀርቧል።

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ