1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፀጥታ ጉዳይ በኦሮሚያ ክልል

ሰኞ፣ የካቲት 16 2012

በኦሮሚያ ክልል አባ ቶርቤ የሚባልና «ጽሑፍ ያለው ወረቀት እየበተነ  አስጠንቅቆ  ሲያበቃ ቀጠሮ ሰጥቶ የሚገድል» የተባለ አካል የክልሉን ሰላም እያወከ መሆኑን የክልሉ የኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

https://p.dw.com/p/3YKGn
Karte von Äthiopien
ምስል AP GraphicsBank/DW

«በአምቦ የቦምብ ጥቃት፣ በቡራዩ ግድያ»

በኦሮሚያ ክልል አባ ቶርቤ የሚባልና «ጽሑፍ ያለው ወረቀት እየበተነ  አስጠንቅቆ  ሲያበቃ ቀጠሮ ሰጥቶ የሚገድል» የተባለ አካል የክልሉን ሰላም እያወከ መሆኑን የክልሉ የኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ። የቢሮ ኃላፊው አቶ ጌታቸው ባልቻ ለዶቼ ቬለ (DW) ትናንት በአምቦ ለመንግሥት ድጋፍ የወጡ ሰዎችን እንቅስቃሴ ለማስቆም  ያሰበ  ግን ያልተሳካ ያሉት የቦንብ ጥቃት ተሰንዝሮ 29 ሰዎች መጎዳታቸውን ገልፀዋል። ከተጎጂዎቹ  አንዱ ብቻ አሁንም በህክምና ላይ እንደሚገኝ ቀሪዎቹ ግን ወደ ቤታቸው መመለሳቸውንም ተናግረዋል። በጉዳዩ በአካል ተሳትፈዋል በሚል እጃቸው እንዳለበት የተጠረጠሩ ስድስት ሰዎች እጅ ከፈንጅ የተያዙ ሲሆን ክትትሉ ቀጥሏል ብለዋል። ራሱን በድርጅትም ይሁን በቡድን ደረጃ እንዲህ ነኝ ብሎ የሚጠራ አካል ባይኖርም ግድያ እየፈጸመ ፣ ዜጎችን እያፈናቀለ ፣ ጉዳት እያደረሰ ያለው «አባ ቶርቤ» የሚባል አካል እንደሆነም ገልጸዋል። ባለፈው ዓርብ የተገደሉትን የቡራዩ ከተማ ፓሊስ አዛዥ በተመለከተም ክትትሉ ተጠናክሮ መቀጠሉን፣ ሕዝቡን የማረጋጋትና አጥፊዎቹን ወደ ሕግ የማቅረብ ሥራም  በተጠናከረ  ሁኔታ  እየተከናወነ  መሆኑን ለዶቼ ቬለ ዘርዝረዋል። ከጉዳዩ ጋር በተያያዘም 18 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ይፋ አድርገዋል። መከላከያ ሠራዊት በተለይም በምዕራብ የክልሉ ክፍል ከክልሉ የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ጸጥታ የማስከበር ሥራ እየሠሩ መሆኑንም አመልክተዋል። በሞያሌ ተመሳሳይ ጥቃት በጸጥታ አካላት ላይ ተፈጽሟል ስለሚባለው ፤ ኃላፊው እስካሁን የጠራ መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል። 

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ