1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጨለማዉ ዋሻ ማዶ ብርሐን

ሰኞ፣ ኅዳር 28 2013

የዓለም ሐብታም፣ ቱጃር፣ ኃይል መንግስታት ዩናይትድ ስቴትስና የቻይና የሚያደርጉት ሽኩቻ ዓመታት ያስቆጠረ፣ በርዕዮተ ዓለም ልዩነት፣ በንግድ ተባለጥ፣ ዓለምን በጣሙን ሩቅ ምስራቅን በላይነት በመቆጣጠር ሰበብ የሚጦዝ ሊሆን ይችላል።የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭት ዉዝግብ ሽኩቻዉን ለማናር ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን የዋሽግተንም የቤጂንግም መሪዎች አልካዱትም።

https://p.dw.com/p/3mMIv
New York Merkel Video Botschaft  UN-Onlinekonferenz zu Frauenrechten
ምስል UN

የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭት፣ ዉዝግቡና ተስፋዉ


አሜሪካኖች፣ ያን ገዳይ ተሕዋሲ በ1920ዎቹ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ዶሮ ላይ አገኙት።ብሪታንያዎች ለሰዉም ገዳይነቱን አረጋገጡ። «ኮሮና» አሉትም።አሜሪካኖች ዶሮ ላይ ባገኙት በመቶኛ ዓመቱ ከቻይና ተሰራጨ።ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ሰዉ ፈጀ፤ 54 ሚሊዮን ለከፈ።ሕዝብን አስጨነቀ፣ ስራ-ኑሮን አሳከረ።ሐኪሞችን፣ ሳይቲስቶችን፣ ፖለቲከኞችን አራወጠ፣ አጨቃጨቀ፤ ወታደሮችን አስዘመተ፣ አጋጨም፤ ጋዜጠኛን አስጮኸ።ብዙ ኩባንዮችን ሲያከስር ጥቂቱን አነሰረ።ሩሲያዎች፣ አሜሪካኖችና ጀርመኖች ያገኙት ክትባት ግን ሰሞኑን ለሰዎች ይሰጥ ጀምሯል።ዓለም ከጨለማዉ ዋሻ ማዶ ብርሐን እያየ ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።
የጥናት ድርሳናት እንደሚጠቁሙት በ1920ዎቹ ሰሜን አሜሪካ ዉስጥ የቤት እንስሳትን በተለይም ዶሮን የፈጀዉ በሽታ የመተንፈሻ አካልን ከሚያቆስል ተሕዋሲ  እንደሚመጣ አሜሪካዉያን ተመራማሪዎች በ1931 አስታዉቀዉ ነበር።አሜሪካዉያኑ ሳይቲስቶቹ ኢንፌክሺየስ ብሮንካይቲስ ቫይረስ (IBV) ያሉት ተሕዋሲ ወይም ተመሳሳዩ ሰዉንም እንደሚያጠቃ የብሪታንያ ሳይቲስቶች ቀደም፣ አሜሪካኖች ከተል ብለዉ ግን ሁለቱም በ1960ዎቹ ማብቂያ አረጋገጡ።የብሪታንያ ሳይቲስቲስቶች ገዳዩን ተሕዋሲ «ኮሮና» ብለዉ በላቲናዊ ስም የሰየሙትም በዚያዉ ዘመን ነበር።
የተሕዋሲዉን ዓይነት፣ባሕሪና እንስሳና ሰዎችን ሲያጠቃ አንዱ ከሌላዉ የሚኖረዉን ልዩነት፣በመከፋፈል፣ በማጥናት ስያሜዉን በመስጠቱ ሒደት የስኮቲሿ (ብሪታንያዋ) ሳይቲስት ጁን አልሜይዳ ከፍተኛዉን አስተዋፅኦ ማድረጋቸዉ በየመጣጥፉ ይጠቀሳል።በ2017 የዩናይትድ ስቴትስን የፕሬዝደትነት ስልጣን የያዙት ቱጃሩ ነጋዴ ዶናልድ ትራምፕ ግን የሐገራቸዉም፣ የእናታቸዉ ሐገር ሳይቲስቶች ያደረጉትን የምርምር ዉጤት፣ የሰጡትን ስም፣ዓለም የተቀበለዉንም እዉነት እንቢኝ ብለዉ ገዳዩን ተሕዋሲ «የቻይና» እንዳሉት ዓመት አስቆጠሩ።
                                       
«በቻይና ተሕዋሲ ላይ በከፈትነዉ ዉጊያ የተወሰዱ አንዳድ ርምጃዎችን በመግለጥ እጀምራለሁ።»መጋቢት 2020።ትራምፕ ተሕዋሲዉን «የቻይና» ለማለታቸዉ የሚሰጡት ምክንያት ከቻይና  በመሠራጨቱ ነዉ የሚል ነዉ።
ተሕዋሲዉ ኮሮና፣ ኮቪድ ተባለም ወይም ትራምፕ እንዳሉት «የቻይና» በዩናይትድ ስቴትስ ያደረሰዉ ቀዉስ፣ የትራምፕ አስተዳደርን ወዝዉዞ ፣ ገዝግዞ፣ ፕሬዝደንት ትራምፕ ባለፈዉ ሕዳር በተደረገዉ ምርጫ  በተቀናቃኛቸዉ እንዲሸነፉ ካደረጉ ትላልቅ ምክንያቶች ትልቁ ሆኗል።
ሁለቱ የዓለም ሐብታም፣ ቱጃር፣ ኃይል መንግስታት ዩናይትድ ስቴትስና የቻይና የሚያደርጉት ሽኩቻ ዓመታት ያስቆጠረ፣ በርዕዮተ ዓለም ልዩነት፣ በንግድ ተባለጥ፣ ዓለምን በጣሙን ሩቅ ምስራቅን በላይነት በመቆጣጠር ሰበብ የሚጦዝ ሊሆን ይችላል።የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭት ዉዝግብ ሽኩቻዉን ለማናር ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን የዋሽግተንም የቤጂንግም መሪዎች አልካዱትም።
የዓለም ቱጃር ኃያላን መንግስታትን ሽኩቻ ያናረዉ ተሕዋሲ፣ በዓለም ከፍተኛ ጥንቃቄና ጥበቃ የሚደረግላቸዉን ግለሰብ፣ ከነ ቤተሰብ፣ ባለስልጣኖቻቸዉ ለሆስፒታል አልጋ ዳርጓል። ለምርጫ ሽንፈት አጋልጧልም።
ኮቪድ19 ከገደለ፣ ካሳመመዉ ሕዝብ፣ ከምጣኔ ሐብት ድቀት ኪሳራዉ በላይ መዘዙ ኃያላኑን ከዉዝግብ ሽኩቻ እስከ መዋጮ ንፍገት፣ከመሪዎች የጤና ቀዉስ እስከ ምርጫ ሽንፈት ሲያደርስ፣ ኢትዮጵያን ደግሞ ከምርጫ መራዘም ዉዝግብ እስከ ዉጊያ ለናረ ጠብ ምክንያት ባይሆን ሰበብ ሆኗል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለፈዉ ሳምንት ሐሙስና ዐርብ በኮሮና ተሕዋሲ ስርጭትና መፍትሔዉ ላይ ለመከረዉ ልዩ ጠቅላላ ጉባኤ እንዳስታወቀዉ ኮቪድ 19፣ በድርጅቱ የ75 ዓመት ታሪክ ዉስጥ ታላቁ የጤና ቀዉስ ብቻ ዓይደለም፣ የሰብአዊ፣ የማሕበረ-ምጣኔ ሐብታዊ፣ የፀጥታና የሰብአዊ መብት ቀዉስ ጭምር እንጂ።
የጠቅላላ ጉባኤዉ ፕሬዝደንት ፎልካን ቦስኪር «የዘመናችን ዓለም ታላቅ ፈተና» ያሉትን መቅሰፍት ለማስወገድ ዓለም በጋራ እንቆም ተማፅነዋል።«ይሕ አዳራሽ መንግሥታት አንድ ላይ የሚሰበሰቡበት ነዉ።የሚተባበሩበት ነዉ።ጠቅላላ ጉባኤዉ የሰዉ ልጆች ድምፅ፣ ፍላጎትና ሕሊና ነዉ።ዓለም፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም ዛሬ  ያጋጠማትን የዘመኑን ታላቅ ፈተና ለማስወገድ ተጨባጭ እርምጃ ይወስዳል ብሎ እየጠበቀ ነዉ።»
ፕሬዝደንቱ «ይሕ» ያሉት የግዙፉ ድርጅት ሰፊ አዳራሽ ግን ፈንጠር ፈንጠር ብለዉ ከተቀመጡ ጥቂት ሰዎች በስተቀር ባዶ ነበር።ለጉባኤዉ 53 ርዕሳነ-ብሔራት፣ 39 መራሕያነ-መንግስታትና 38 ሚንስትሮች  መልዕክት አስተላልፈዋል።አብዛኞቹ መልዕክቱን ያስተላለፉት ካያሉበት ነዉ።
በተለይ የበለፀጉት ሐገራት መሪዎችና ተወካዮች ገዳዩን ተሕዋሲ የሚከላከለዉን ክትባት ለድሆቹ ሐገራት ሕዝብ ጭምር እንዲደርስ ለመርዳት ቃል ገብተዋል።ይሁንና በጎ ቃል የተቆረቆረበት፣ ልዩ ጉባኤ፣ ባዶዉ አዳራሽም ጭምር ዘንድሮም እንደ አምናዉ የዉዝግብ ሽኩቻ መድረክ ከመሆን አላመለጠም።
ሮይተርስ ዜና አገልግሎት «ስማቸዉን መናገር ያልፈለጉ» ብሎ የጠቀሳቸዉ አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ባለስልጣን ጉባኤዉን «የዘገየ» እና «የቻይናን ፕሮፓጋንዳ ለማስተጋባት» ያለመ በማለት አጣጥለዉ ነቅፈዉታል።ለጉባኤዉ በቪዲዮ መልዕክት ያስተላለፉት የዩናይትድ ስቴትስሱ የጤና የሕብረተሰብ አገልግሎት ሚንስትር አሌክስ አዛርም ስማቸዉን እንደሸሸጉት ባልደረባቸዉ ፊት ለፊት ባያፈርጡትም እንደ ዲፕሎማሲዉ ወግ በግድምድሞሽ አገላለጥ ቻይናን መወረፋቸዉ አልቀረም።ሚንስትሩ የዘንድሮዉን የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭት «የስፔን ጉንፋን» ይባል ከነበረዉ ከ1918ቱ የኢንፌሌንዛ መቅሰፍት ጋር ያመሳስሉታል።ቻይናን ለመተቸት ምክንያት ያደረጉት ግን በዘመን ሒደት የመጠቀዉን የመረጃ ዕድገት፣ፍጥነትና አጠቃቀሙን ነዉ።
                                             
*«በ1918 እንደሆነዉ ሁሉ፣ ተሕዋሲዉ በድፍን ዓለም እሲከሰራጭ ድረስ በቂ መረጃ አልተሰጠም ነበር።ዛሬ ለዚሕ ምክንያት ሊቀርብበት አይችልም።በ1918 ዘመናይ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች አልነበሩንም።መረጃዎችን ለማጋራት ዉጤታማ ዓለም አቀፍ ሥርዓት አልነበረንም።ዓለም አቀፍ የጤና ደንቦች አልነበሩንም።ቁልፉ ጉዳይ ተሕዋሲዉ መጀመሪያ የተገኘበት ቦታ አይደለም።ጥያቄዉ መረጃ በጊዜና በግልፅ ለሌች መሰጠቱ ነዉ።በሚያሳዝን ሁኔታ አስፈላጊዉ መረጃ አልተሰጠም።ይሕ ኃላፊነትን የዘነጋ እርምጃ በመላዉ ዓለም ከባድ ጥፋት አድርሷል።»
ስማቸዉ ያልተጠቀሰዉ የዩናይትድ ስቴትስ ባለስጣን ጉባኤዉን «የቻይና ፕሮፓጋንዳ መድረክ» ማለታቸዉን  በተባበሩት መንግስታት የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ አጣጥሎ ነቅፎታል።ቃል አቀባዩ ሮይተር ዜና ወኪል እንደጠቀሰዉ «ጉዳዩን ፖለቲካዊ ማድረግ የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ፍላጎት አይደለም።»
ለጉባኤዉ ንግግር ያደረጉት የቻይና ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዋንግ ይም የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በቻይና መንግስት ላይ ለሰነዘሩት ወቀሳ የሰጡት መልስ የለም።
የዋሽግተን-ቤጂንጎች የፖለቲካ-ዲፕሎማሲ ዉዝግብ ቀጠለም ቆመ ዉዝግቡን ለማናር  ምክንያት የሆነዉ የኮሮና ተሕዋሲ ዘንድሮ ከዓመት በኋላ በሰዉ ልጅ ድል ከሚሆንበት የመጨረሻዉ መጀመሪያ ላይ የደረሰ መስሏል።
የሩሲያ ሳይቲስቶች ከብዙዉ ዓለም ቀድመዉ ግን ከብዙዉ ተነጥለዉ ያገኙት ክትባት ካለፈዉ ቅዳሜ ጀምሮ ለሐገሪቱ ዜጎች እየተሰጠ ነዉ።ተሕዋሲዉን ከዓለም ቀድመዉ ያገኙት አሜሪካኖች፤ ከጀርመኖች ጋር ሆነዉ የሰሩት ክትባት ደግሞ ተሕዋሲዉ የሰዉም መሆኑን ለተረጋገጠበት፣ ዛሬ በሚታወቀዉ ስም ለተሰየመበት ሐገር ለብሪታንያ ሕዝብ ቢዘገይ በዚሕ ሳምንት እንዲሰጥ ተወስኗል።
ተሕዋሲዉ የዛሬ መቶ ዓመት ግድም መጀመሪያ የታወቀባት፣ተሕዋሲዉ በሚያመጣዉ በሽታ ከዓለም ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ሕዝብ የገደለ፣ ያሳመመባት፣ ብዙ ተቀባይነት ያገኘዉ ክትባት ከጀርመን ጋር በመተባበር የተሰራባት ዩናይትድ ስቴትስና ጀርመንን ጨምሮ የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራትም ክትባቱን ለየሕዝባቸዉ ለመስጠት እየተዘጋጁ ነዉ።
የጀርመኗ መራሒተ መንግስት ወይዘሮ አንጌላ ሜርክል በመግቢያችን ላነሳዉ ጥያቄ አወንታዊ መልስ አላቸዉ።አዎ ይላሉ ሜርክል ከጨለማዉ ዋሻ ጫፍ የብርሐን ጭላንጭል ይታያል።
«ዘንድሮ በወረርሺኙ ምክንያት ከፍተኛ አስቸጋሪ ሁኔታ ቢያጋጥመንም፣ ከዋሻዉ መጨረሻ ጫፍ ብርሐን አለ።ከዚሕ የተደረሰዉ በአብዛኛዉ ACT በተባለዉ የኮቪድ 19ን ለመከላከል በተመሰረተዉ ትብብር አማካይነት ነዉ።ለዚሕ ትብብር ምስጋና ይግባዉና መመርመሪያ፣ ማከሚያና ክትባትና መሳሪያ ለመስራትና ለማከፋፈል የሚረዳ መድረክ ተዘጋጅቷል።ይሁንና ይሕ መድረክ ይበልጥ ዉጤታማ እንዲሆን ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ያሻዋል።ገንዘብን ስራ ላይ ማዋሉ ጠቃሚ ነዉ።በተለይ ከACT መሠረታዊ ዓላማዎች አንዱን ስናይ በጣም ጠቃሚነቱ በግልፅ ይታያል።ክትባትን ማምረት።በዚሕ ግንባር ከፍተኛ እመርታ ታይቷል። ተስፋ የማድረጋችን ምክንያትም ይህ ነዉ።»
ተስፋ ጥሩ ነዉ።ተስፋ እናድርግ።

Data visualization - COVID-19 vaccine tracker - Research Teams - Update 2.12.2020
Russland | Coronavirus: Impfstoff
ምስል Vitaly Nevar/TASS/dpa/picture alliance
Indonesien | Lieferung Coronavirus Impfstoff Sinovac Biotech
ምስል Presidential Palace/REUTERS

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ