1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስአፍሪቃ

የጦጣ ፈንጣጣ ተሐዋሲ ወረርሽኝ ስጋት ምን ያህል ?

ረቡዕ፣ ግንቦት 17 2014

የጤና ባለሞያዎች በሽታው እንዴት ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍ ገና ግራ እንዳጋባቸው ነው። በእርግጥ የጦጣ ፈንጣጣ በሽታ ለምድራችን አዲስ አይደለም። አፍሪቃውያን በተለይም አንዳንድ የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት በሽታውን ተለማምደውት እየኖሩ ባሉበት በዚህ ጊዜ የጦጣ ፈንጣጣ ወረርሽኝ እንዴት እንደ አዲስ የዓለም ስጋት ሆኖ ብቅ አለ?

https://p.dw.com/p/4Bnvu
Infektion mit "Monkeypox Virus" Affenpocken - 1971
ምስል Gemeinfrei/CDC's Public Health Image Library

የጦጣ ፈንጣጣ ሌላው የዓለማችን የወረርሽኝ ስጋት

ዓለም ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ገና አላገገመችም፤ በየሀገሩ አሁንም ሰዎች በተሐዋሲው እየተለከፉ ነው። በተዋሐሲው የሚሞተው የሰው ቁጥርም እንዲሁ ቀላል አይደለም። በወረርሽኙ ሳቢያ በመላው ዓለም የተከሰተው የኤኮኖሚ ድቀት ሊያገግም ገና ዓመታትን መውሰዱ አይቀርም፤ ለዚያውም ሰላም ካለ። ነገር ግን ይህቺው ያልታደለችው ዓለም ከኮሮና ወረርሽኝ እና የሩስያ ዩክሬን ጦርነት ከደቀኑት ስጋት ሳትላቀቅ ሌላ ፤ ምናልባትም ሌላ አስፈሪ ስጋት ተደቅኖባታል። አዲስ የወረርሽኝ በሽታ ስጋት ፤ የጦጣ ፈንጣጣ። ጤና ይስጥልን አድማጮቻችን በዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዝግጅታችን በብሪታኒያ ተከስቶ ወደ ሌሎች የዓለማችን ሃገራት እየተዛመተ ስለሚገኘው እና ምናልባትም በዓይነቱ አስፈሪ ስለሆነው የጦጣ ፈንጣጣ በሽታ ወረርሽኝ አይነት እና ያሳደረውን ስጋት እንመለከታለን ፤ መልካም ቆይታ ።

የጤና ባለሞያዎች በሽታው እንዴት ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍ ገና ግራ እንዳጋባቸው ነው። በእርግጥ የጦጣ ፈንጣጣ በሽታ ለምድራችን አዲስ አይደለም። አፍሪቃውያን በተለይም አንዳንድ የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት በሽታውን ተለማምደውት እየኖሩ ባሉበት በዚህ ጊዜ የጦጣ ፈንጣጣ ወረርሽኝ እንዴት እንደ አዲስ የዓለም ስጋት ሆኖ ብቅ አለ? ገና ከወረርሽኝ ላላገገመችው ዓለምስ ምን አይነት አንድምታ ይዞ ይመጣ ይሆን? እስቲ በመጠኑ ስለ በሽታው አመጣጥ ታሪካዊ ዳራ እንመልከት።  የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው የጦጣ ፈንጣጣ ተሐዋሲ በጦጣዎች ላይ መገኘቱ በምርመራ ለመጀመርያ ጊዜ የተረጋገጠው በጎርጎርሳዊው 1958 ዴንማርክ ውስጥ ነው። ሞንኪ ፖክስ ወይም የጦጣ ፈንጣጣ የሚለውን ስያሜ ያገኘውም ተሐዋሲው ከጦጣዎች በተወሰደ ናሙና ከመገኘቱ ጋር ተያይዞ ነው። ተሐዋሲው በሰዎች ላይ በምርመራ የተረጋገጠው ደግሞ በጎርጎርሳዊው 1970 በኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ  በአንድ ሕጻን ላይ በምርመራ ከተረጋገጠ በኋላ ነበር። በሽታው በሰዎች ላይ መረጋገጡ ግማሽ ክፍል ዘመን ተሻግሮታል። በሽታው ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው ሰውነት ላይ በሚገኝ የቁስል ንክኪ፣ ሌሎች የሰውነት ፈሳሾች ንክኪ፣ከመተንፈሻ አካላት የሚወጡ ፈሳሾች እንዲሁ በህመምተኛው ሰው በተበከሉ አልባሳት ንክኪ አማካንነት እንደሆነ መረጃው ያመለክታል። የጦጣ ፈንጣጣ ተሐዋሲ ከሰው ወደ ሰው ከተላለፈ በኋላ ከ6 እስከ 13 ቀናት የህመም ምልክት ሊያሳይ ይችላል። ፕሮፌሰር ያሬድ ወንድምኩን በዩንይትድ ስቴትስ ቨርጂኒያ የውስጥ ደዌ ሀኪም ናቸው የጦጣ ፈንጣጣ በሽታ እንደ ኮሮና በሽታ በዓለማችን ላይ ከፍ ያለ ስጋት ያመጣል ብለው አያምንኑም ። ምክንያቱም ይላሉ ፕሮፌሰር ያሬድ።

Illustration Affenpocken Test
ምስል Dado Ruvic/REUTERS
Zentralafrikanische Republik Patienten mit Affenpocken
ምስል CHARLES BOUESSEL/AFP
Symptome Affenpocken
ምስል Brian W.J. Mahy/CDC/REUTERS

በሰዎች ላይ የተከሰተው የፈንጣጣ  በሽታ ከምድር ላይ ከጠፋ ሦስት አስርት አመታትን ተሻግሯል። የሰው ልጆች በምርምር ውጤት ካገኙት የበሽታ መከላከያ ክትባቶች ውስጥም በህመም ወቅትም ሆነ ህመሙ ካለፈ በኋላ አስቀያሚ አሻራውን በሰዎች ፊት ላይ ጥሎ የሚያልፈውን ደዌ እስከ መጨረሻው ተሰናብተውት ነበር። ምናልባትም አሁን በጦጣዎች ላይ የተገኘው ይኽ ተሐዋሲ አሁን በአዲስ መልኩ ሌላ ስጋት ሆኖ መጥቷል። ፕሮፌሰር ያሬድ እንደሚሉት ለሰዎች ፈንጣጣ ከዓመታት በፊት የመከላከያ ክትባቱን የተከተቡ ሰዎች በሽታውን የመከላከል አቅም ሊኖራቸው ቢችልም ከጊዜ ብዛት ያንን አቅም ሊያጡ የሚችሉበት ዕድል ሊኖር ይችላል።  ነገር ግን በቅርቡ ክትባቱን የተከተቡ ሰዎች ክትባቱ አሁንም ከፍተኛ የመከላከል አቅም እንዳለው ያረጋገጠ ውጤት ማስገኘቱን በመግለጽ በሽታው ለዓለማችን ስጋት ሊሆን የማይችልበትን ዕድል አስረግጠው ይናገራሉ።

Kongo | Ausschlag bei einem Affenpocken Patienten
ምስል Brian W.J. Mahy/CDC/REUTERS

ዩናይትድ ስቴትስ ፣ ካናዳ ፣ ብሪታኒያ ፤ ጀርመን  እንዲሁም ከአፍሪቃ ሞሮኮን ጨምሮ ይህ ዝግጅት እስከተሰናዳበት ሰዓት ድረስ 21 የዓለማችን ሃገራት ከ100 በላይ የጦጣ ፈንጣጣ ተጠቂዎች መገኘታቸውን ይፋ አድርገዋል። ተሐዋሲው ከአፍሪቃ ውጭ በ16 ሃገራት ውስጥ መከሰቱ ነው የተረጋገጠው። ምንም እንኳ በየሀገሩ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ በሽታው መገኘቱ በምርመራ ቢረጋገጥም ወደ የተለያዩ ሃገራት በቀላሉ እየተዛመተ ስለመሆኑ ግን እነዚሁ አህጉር ተሻጋሪ የምርመራ ዘገባዎች ያመለካታሉ።

Symptome Affenpocken
ምስል CDC/Getty Images

ከአውሮጳ የበሽታዎች መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል የተሐዋሲውን ሌላ የመተላለፊያ መንገድ በተመለከተ የተገኘው መረጃ፤ የግብረ ስጋ ግንኙነትም ሌላኛው የተሐዋሲው መተላለፊያ መንገድ መሆኑን ያሳያል።

አንድ ሰው በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ፈፅሞ ከሆነ ፣ አንሶላ እና ሌሎች አልባሳትን ተጋርቶ ከሆነ አሊያም የበሽታው መከላከያ የህክምና ቁሳቁሶችን በጋራ ተጠቅሞ ከሆነ ለበሽታው ሊያጋልጠው እንደሚችል ከምርምር ማዕከሉ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

Illustration Pockenvirus
ምስል Science Photo Library/IMAGO

 በጥቂት ቀናት ውስጥ በርካታ የዓለማችን ሃገራትን ያዳረሰው የጦጣ ፈንጣጣ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በፊት በቁጥጥር ስር ሊውል እንደሚገባ የሚናገሩት የውስጥ ደዌ ህክምና ባለሙያው ፕሮፌሰር ያሬድ ወንድምኩን እንደሚሉት ተሐዋሲውን ለመከላከል ከ0 የሚጀመር ሥራ ባለመኖሩ በአጭር ያሉትን አማራጮች እንዲህ ይገልጻሉ።

በተሐዋሲው የተጠቁ ታማሚዎች በበሽታው ከተያዙ በኋላ ለማገገም ከሁለት እስከ አራት ሳምንታት እንደሚወስድባቸው የህክምና መረጃዎች ያመለክታሉ። በተሐዋሲው የተጠቁ ሰዎች ከፍተኛ የሰውነት ሙቀት ይኖራቸዋል፤ ማሳከክ፤ በሰውነት ቆዳ ላይ ውሃ የሚቋጥር እብጠትም ይታይባቸዋል። ይህንኑ በመረዳት በፍጥነት ወደ ህክምና ተቋም መሄድ እንደሚገባም ይመከራል።

በሌላ በኩል የጦጣ ፈንጣጣ በሽታ ለወትሮ ከሚታወቅባቸው አንዳንድ የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ውጭ ተዛምቶ  መገኘቱ የተለያዩ መላምቶችን ሳያስነሳ አልቀረም ። ምክንያቱም ደግሞ ተሐዋሲው ይገኝባቸዋል ተብለው ወደ ሚጠረጠሩ የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት የጉዞ ታሪክ በሌላቸው ሰዎች ላይ ጭምር መታየቱ ነው። የሆነ ሆኖ ሃገራት የተሓዋሲውን ስርጭት ለመግታት ከአሁኑ የቤት ሥራዎቻቸውን እያከናወኑ መሆኑን ይናገራሉ። ቀደም ሲል ከምድር ላይ እንደጠፋ የሚገመተው የሰዎች የፈንጣጣ  በሽታ ከዚሁ ከጦጣ ፈንጣጣ በሽታ ጋር ተዛማጅ በመሆኑ እና የሰዎች የፈንጣጣ ተሐዋሲ መከላከያ ክትባት የጦጣ ፈንጣጣ ተሀዋሲን 85 ከመቶ የመከላከል አቅም እንዳለው በመረጋገጡ ሃገራት ክትባቱን ከወዲሁ ማከማቸት መጀመራቸው ተመላክቷል። እንደ  ኢትዮጵያ ባሉ እና ቀደም ሲል በፈንጣጣ በሽታ ብርቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሃገራት ያ ተመሳሳይ ታሪክ እንዳይደገም ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ይመከራል። 

ታምራት ዲንሳ

ሸዋዬ ለገሰ