1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጦርነት ዘመን ኤኮኖሚ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 24 2014

በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉበት፣ በሚሊዮኖች የተፈናቀሉበት እና ዛሬ ዕኩለ-ሌሊቱን አንድ ዓመት የሚሞላው ጦርነት አገሪቱ በዓመታት ልፋት ያጠራቀመችውን ጥሪት ጭምር እያወደመ ነው። በጦርነቱ ዳፋ ኢትዮጵያ በአጎዋ በኩል ለአሜሪካ የገበያ የነበራትን ዕድል ከጥር ወር ጀምሮ ስታጣ ባለወረቶችንም እያሸሸ ነው

https://p.dw.com/p/42Xo0
Äthiopien I Krieg in Tigray beschädigt die Fabrik von Zenith Gebs Eshet Ethiopia Ltd in Shire
ምስል Biniam Gebrezgi/Zenith Gebs Eshet Ethiopia Ltd

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የጦርነት ዘመን ኤኮኖሚ

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የዕድገት እና ዕድል ድንጋጌ (African Growth and Opportunity Act) በኩል ሸቀጦቿን ለአሜሪካ ገበያ የማቅረብ ዕድሏን ከታኅሣሥ 23 ቀን፣ 2014 ጀምሮ ታጣለች። የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ትናንት ማክሰኞ ለአገራቸው ምክር ቤት በጻፉት ደብዳቤ «ዓለም አቀፍ ዕውቅና በተሰጣቸው የሰብአዊ መብቶች ብርቱ ጥሰት ምክንያት» ኢትዮጵያ በአጎዋ ድንጋጌ የነበራትን ዕድል ማጣቷን ይፋ አድርገዋል።

ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ጊኒ እና ማሊ ተመሳሳይ እጣ-ፈንታ የገጠማቸው ሲሆን፤ የአሜሪካ የንግድ ተወካይ ካትሪን ታይ "የአገራቱ መንግሥታት የአጎዋን ድንጋጌ በመጣስ በወሰዱት ርምጃ ምክንያት" ከመርሐ-ግብሩ ውጪ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

በጎርጎሮሳዊው 2020 ዓ.ም 237 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ሸቀጦች ያለ ቀረጥ በአጎዋ በኩል ለአሜሪካ ገበያ ላቀረበችው ኢትዮጵያ ውሳኔው የመርዶ ያክል ነው። መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ባደረገው አሜሪካ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት የሚያገለግሉት የምጣኔ ሐብት ባለሙያው ዶክተር ውበት ካሳ "በዋናነት የሚጎዳው በጨርቃ ጨርቅ እና በተዛማጅ ዘርፎች ውስጥ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎችን ነው። ኢትዮጵያ በቅርቡ ከፍ ያለ የውጭ ኢንቨስትመንት እያስመዘገበች ያለበት ዘርፍ ነው። በተለይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በዋነኝነት የተሳተፉበት ለውጭ ዕቃን በማምረት ላይ ስለሆነ እነዚህ ዘርፎች ተጽዕኖ ያርፍባቸዋል" ሲሉ ተናግረዋል።

በጨርቃ ጨርቅ እና ተዛማጅ ማምረቻዎች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ተቀጣሪዎቻቸውን ሥራ እንደሚያሳጣ የገለጹት ዶክተር ውበት "በአገሪቱ የዕድገት፣ የሥራ ፈጠራ ዕቅድ እና የድህነት ቅነሳ መርሐ-ግብር ላይ በአሉታዊ መንገድ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። የውጭ ምንዛሪ የማግኘት አቅምንም ሊቀንስ ይችላል" በማለት አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ አሜሪካ ርምጃውን እንድትቀለብስ ጥያቄ አቅርቧል። የአሜሪካ ውሳኔ "በፍጹም ችግሩን አያቃልልም" ያለው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ርምጃው ከግጭቱ ምንም ግንኙነት የሌላቸው ከ200 ሺሕ በላይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች በተለይም ሴቶችን እንደሚጎዳ ገልጿል።

የአሜሪካ የንግድ ተወካይ ካትሪን ታይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሦስቱ አገሮች ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን የንግድ ግንኙነት እንደገና ለመጀመር ለአጎዋ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን ለማሟላት አስፈላጊ የሆኑ ርምጃዎችን መውሰድን እንደሚጠበቅባቸው ትናንት ማክሰኞ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። ካትሪን ታይ ኢትዮጵያ፣ ማሊ እና ጊኒ በአጎዋ በኩል ሸቀጦቻቸውን በአሜሪካ ገበያ የማቅረብ ዕድላቸውን ለመመለስ ማድረግ የሚጠበቁባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ለሶስቱም አገሮች እንደሚያሳውቁ ቃል ገብተዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አገሪቱን ያሳጣት በአጎዋ በኩል የነበራትን ዕድል ብቻ ግን አይደለም። በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉበት፣ በሚሊዮኖች የተፈናቀሉበት እና ዛሬ ዕኩለ-ሌሊቱን አንድ ዓመት የሚሞላው ጦርነት አገሪቱ በዓመታት ልፋት ያጠራቀመችውን ጥሪት ጭምር እያወደመ ነው። 

የኢትዮጵያን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉ የፖለቲካ እና የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ጦርነቱ ያስከተለውን ኪሳራ አሁን በሚገኝበት ደረጃ በቁጥር መናገር ቢቸግራቸውም ብርቱ ኤኮኖሚያዊ ጉዳት ማስከተሉ ግን አልጠፋቸውም። መቀመጫውን በለንደን ባደረገው ካፒታል ኤኮኖሚክስ የተባለ ተቋም የምጣኔ ሐብት ተንታኝ የሆኑት ቪራግ ፎሪዥ "ባለወረቶች በኢትዮጵያ የዕድገት አካሔድ ደስተኞች አይደሉም። ይኸ ዋጋው እጅግ በሰፋው የኢትዮጵያ ቦንድ ግብይት ተንጸባርቋል። የኢትዮጵያ ቦንድ እየተሸጠ ያለው ጫና ውስጥ ከገቡት ጎራ ነው።  የአገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ እጅጉን ተዳክሟል። የዋጋ ግሽበት ከ30 በመቶ በላይ ነው። በተለይ በፋይናንስ ገበያው የታየው ነገር ኢትዮጵያ የነበራትን ቀዳሚነት ማጣቷን የሚያሳይ ይመስለኛል" ሲሉ ጫናውን ይገልጻሉ።

በጥቅምት ወር መጀመሪያ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት በሚቀጥለው አመት የሚኖራቸውን ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት ሲተነብይ የኢትዮጵያን ሳያካትት ቀርቷል። ለዚህም ተቋሙ በቀጥታ የአንድ ዓመቱን ጦርነት ባይጠቅስም "በወደፊት ኤኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ረገድ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የእርግጠኝነት ማጣት" አንዱ ገፊ ምክንያት እንደሆነ ይፋ አድርጓል።

ከዚያ ቀደም ብሎ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ጠቀም ያለ ገንዘብ ከምትበደርባቸው አንዱ የሆነው እና የተራዘመ የብድር አቅርቦት (Extended Credit Facility) የተባለው ማዕቀፍ ጊዜው ሳይጠናቀቅ ተቋርጧል። ከተፈቀደላት 1.7 ቢሊዮን ዶላር ብድር ውስጥ ወደ 200 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ብቻ የወሰደችው ኢትዮጵያ ማዕቀፉ እንዲራዘም አሊያም መተኪያ እንዲበጅለት ጥያቄ አቅርባለች። ይኸ በአንጻሩ ኢትዮጵያ ባለባት የውጭ ዕዳ ላይ የአከፋፈል ሽግሽግ ለማድረግ የጀመረችው ሒደት ሳይጠናቀቅ ምላሽ ሊያገኝ እንደማይችል የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ቃል አቀባይ ጄሪ ራይስ ጥቆማ ሰጥተዋል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የብድር ማዕቀፍ "እንዲቀጥል" ኢትዮጵያ ጠየቀች

የኢትዮጵያ መንግሥት ዕዳ ከአጠቃላይ አገራዊ የምርት መጠን አኳያ ያለው ምጣኔ 50 በመቶ ገደማ መሆኑን ጠቅሰው "ይኸ በቀጠናውም ይሁን በማደግ ላይ ከሚገኙ የዓለም ገበያዎች አኳያ እጅግ ከፍተኛ የሚባል አይደለም" የሚሉት ቪራግ ፎሪዥ  "ኢትዮጵያ ያንን ዕዳ የመክፈል አቅሟ ላይ የሚነሳው ጥያቄ" አሳሳቢ እንደሆነ ያስረዳሉ።

"ጦርነት እየተካሔደ ከፍተኛ አጠቃላይ አገራዊ የምርት መጠን (GDP) ዕድገት ይኖራል፤ ወይም ኢትዮጵያ በፍነጥት ታድጋለች ብሎ ማሰብ አይቻልም። የመገበያያው ገንዘብ የተረጋጋ ይሆናል የሚለው ሐሳብም በግጭቱ ምክንያት ጥያቄ ውስጥ ወድቋል። የመገበያያ ገንዘብ መዳከም ደግሞ የመንግሥት ዕዳ ከአገሪቱ አጠቃላይ አገራዊ የምርት መጠን አኳያ ያለው ምጣኔ እንዲጨምር ያደርጋል። ስለዚህ ግጭቱ ይኸን የዕዳ ጫና እና ኢትዮጵያ የተበደረችውን ገንዘብ የመክፈል አቅሟ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል" ሲሉ የኤኮኖሚ ባለሙያዋ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ትናንት ማክሰኞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግ ሙሉ በሙሉ ትኩረቱን ከሰሜን ወደ ደቡብ በሚንደረደረው ጦርነት ላይ አድርጓል። የአማራ ክልል ከፌድራሉ መንግሥት ቀደም ብሎ "ማንኛውም የመንግስት ተቋም መደበኛ አገልግሎቱን አቋርጦ በጀቱን ጨምሮ ሁሉንም ነገር" ከትግራይ ኃይሎች ጋር በሚደረገው ውጊያ ላይ እንዲውል ወስኖ ነበር። በትግራይ የንግድ እና የኤኮኖሚ ዘርፎችን ጨምሮ የክልሉ እንቅስቃሴዎች ከተቋረጡ ወራት ተቆጥረዋል። ዛሬ አንድ ዓመት የሞላው የኢትዮጵያ ጦርነት ባለወረቶችን ማራቁን የሚናገሩት የኤኮኖሚ ባለሙያዋ ቪራግ "የኢትዮጵያ የወጪ እና የገቢ ንግድ ሚዛን እጅግ ደካማ ነው። ይኸ ጉድለት በዋናነት የሚሞላው በውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ ንዋይ ነበር" ብለዋል።

ግጭቱ በተባባሰባቸው ወራት የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ ንዋይ እየቀነሰ መሔዱን የሚናገሩት የኤኮኖሚ ባለሙያዋ "በኢትዮጵያ መንግሥት የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር የቴሌኮም ፈቃድ ለሽያጭ ሲቀርብ አንድ ግዙፍ የቴሌኮም ግልጋሎት አቅራቢ ከጨረታው ጥሎ ወጥቷል። ኩባንያው ለውሳኔው በምክንያትነት ካቀረባቸው ጉዳዮች መካከል `በአገሪቱ የሚታየው ግጭት እና ኹከት በቢዝነስ ከባቢው የእርግጠኝነት ማጣት ፈጥሯል´ የሚል ይገኝበታል። ስለዚህ የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ ንዋይ እያፈገፈገ መሆኑን የሚያሳዩ የተወሰኑ ምልክቶች አሉ። የግጭቱ የበለጠ መባባስ የከፋ የርስ በርስ ጦርነት በሚካሔድበት አገር በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ያለውን ፍላጎት መቀዛቀዝ የበለጠ እንመለከታለን ብዬ አስባለሁ" በማለት ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጦርነቱ ከጅማሮው በአጭሩ እንዲቀጭ ኋላም በድርድር እና በተኩስ አቁም እንዲያበቃ ያደረገው ግፊት እስካሁን ፍሬ አላፈራም። ኢትዮጵያ የገባችበት ቀውስ መቼ እና እንዴት መፍትሔ እንደሚበጅለት ባለመታወቁ ኤኮኖሚያዊ ኪሳራውን ለማስላትም ለባለሞያዎቹ ጊዜው ገና ነው። ቪራግ ፎሪዥ "[በጎርጎሮሳዊው] ከ2015 እስከ 2016 የነበረው ከፍተኛ ተቃውሞ የአገሪቱን ዕድገት በ2.5 በመቶ ቀንሷል። በ1998 የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጦርነት በወቅቱ ከነበረው ድርቅ ጋር ተደምሮ ኤኮኖሚውን አኮማትሮ የአገሪቱ አጠቃላይ የምርት መጠን (GDP) ከ4 በመቶ በላይ እንዲቀንስ አድርጎታል" ሲሉ ብርቱ ፖለቲካዊ ቀውስ እና ጦርነት ሊያሳድር ለሚችለው ቀውስ ማነጻጸሪያ አቅርበዋል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ