1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥቅምት 2 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥቅምት 2 2013

የአዐሥር ሺህ ሜትር የአውሮጳ ክብረወሰን በትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድ ሯጭ ተሰብሯል።  በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የዓለም ክብረወሰን ላይ ተደርሷል።

https://p.dw.com/p/3jp3e
Formel 1 | Grand Prix Nürburgring | Vettel
ምስል Joe Portlock/Getty Images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ለ18 ዓመታት በብሪታኒያዊቷ አትሌት ተይዞ የቆየውን በዐሥር ሺህ ሜትር ርቀት የአውሮጳ ክብረወሰን አትሌት ሲፋን ሐሰን መስበር ችላለች። ትውልደ ኢትዮጵያዊት ኔዘርላንዳዊት አትሌት ሲፋን ሐሰን ክብረወሰኑን ያሻሻለችው በ25 ሰከንዶች ነው። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ሌዊስ ሐሚልተን ከሚሻኤል ሹማኸር ክብረወሰን ጋር ተስተካክሏል። በሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ ራፋኤል ናዳል ድል ተቀዳጅቷል። የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከሰሞኑ ባደረጋቸው የወዳጅነት እና የሊግ ውድድሮች የድሮ ብርታቱ አልተስተዋለም።

አትሌቲክስ

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድ ሯጭ ሲፋን ሐሰን ሔንጌሎ ውስጥ በተደረገው የዐሥር ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር የአውሮጳ ክብረ ወሰን ሰብራለች። በብሪታንያዊቷ ሯጭ ፓውላ ራድክሊፍ ከ18 ዓመታት በፊት ተይዞ የቆየውን ክብረ ወሰን ሲፋን በ25 ሰከንድ አሻሽላ ለመስበር ችላለች። ከ25 ዙሩ ሽቅድምድም ግማሽ ያኽሉን ለብቻዋ ነበር የሮጠችው ማለት ይቻላል። ክብረ ወሰኑ የዛሬ 18 ዓመት በፓውላ ራድክሊፍ ሲሰበር ሙይንሽን ውስጥ የሮጠችበት ጊዜ (30:01.09)   ነበር።  አትሌት ሲፋን ሐሰን 29:36.67 ሮጣ ክብረ ወሰን ስትሰብር በዚህ የውድድር ዘርፍ አራተኛዋ ፈጣን ሯጭ አስብሏታል። በርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን አኹንም ድረስ የሚገኘው በኢትዮጵያዊቷ ሯጭ አልማዝ አያና ስር ነው። አልማዝ ከአራት ዓመታት በፊት በሪዮ ዴ ጄኔሮ ኦሎምፒክ 29:17.45 ሮጣ ያስመዘገበችው ድል ከሲፋን የአውሮጳ ክብረ ወሰን በ19 ሰከንዶች የሚበልጥ ነው።

Leichtathletik-WM Doha 2019 Frauen Finale 1500 Meter Sifan Hassan
ምስል Reuters/D. Martinez

የመኪና ሽቅድምድ

ብሪታንያዊው የፎርሙላ አንድ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን ጸጉሩ እስኪነጣ ድረስ ክብረወሰን ማደኑን እንደማይተው ዐሳውቋል። ጀርመን ውስጥ በተከናወነው የፎርሙላ አንድ የኑይርበርግሪንግ ግራንድ ፕሪ ሽቅድምድም የዓለም ክብረወሰን ላይ በደረሰበት ወቅት ነው ሌዊስ ይኽን የተናገረው። የ35 ዓመቱ የመርሴዲስ አሽከርካሪ በትናንትና ድሉ፦ ጀርመናዊው ሚሻኤል ሹማኸር ይዞት የቆየው የ91 ጊዜያት የፎርሙላ አንድ አሸናፊነት ክብረወሰን ላይ መድረስ ችሏል።   

በትናንቱ ውድድር የሬድ ቡሉ አሽከርካሪ ማክስ ፈርሽታፐን ኹለተኛ፣ የሬኖ አሽከርካሪ ዳኒኤል ሪካርዶ ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል። ሌዊስ ሐሚልተን ለድል በበቃበት በትናንትናው እለት የሚሻኤል ሹማኸር ልጅ የ21 ዓመቱ ሚክ ሹማኸር የአባቱን የአደጋ መከላከያ ቀይ የብረት ቆብ በስጦታ መልክ አበርክቶለታል።

«በአጠቃላይ ቤተሰባቸን ስም እንኳን ደስ ያለህ፤ ለድንቅ ብቃትህ»ም ብሎታል ሚክ ሹማኸር። ቆቡን ለሌዊስ ሐሚልተን የውድድሩ ቦታ ይዘው የመጡትት የሚሻኤል ሹማኸር ተጠሪ የ55 ዓመቷ ሣቢኔ ኬኽም ናቸው።

Formel 1 | Grand Prix Nürburgring | Hamilton
ምስል Bryn Lennon/Reuters

በትናንቱ ሽቅድምድ በኮሮና ምክንያት ብዙ ታዳሚ አልነበረም። 13 ሺህ ተመልካች ነበር የታደመው። ሌዊስ ሐሚልተን ለድል ሲበቃ እና በክብረ ወሰን ከሹማኸር ጋር ሲስተካከል ታዳሚው ከመቀመጫው ተነስቶ ነው አድናቆቱን የገለጠለት። ሚሻኤል ሹማኸር በአደጋ ምክንያት ራሱን ከሳተ በርካታ ጊዜያት በመቆጠሩ ስጦታው ልዩ ስሜትም ፈጥሯል በታዳሚው ዘንድ።

የሚክ ሹማኸር ተስፋ

ቢልድ የተሰኘው በጀርመን ሰፊ አንባቢ ያለው ጋዜጣ እንደዘገበው ሌዊስ ሐሚልተን በስጦታው እጅግ ተደስቷል። «ምን ማለት እንዳለብኝ ዐላውቅም። እጅግ በጣም ነው ክብር የተሰማኝ» ሲል ሌዊስ ስጦታውን ላበረከተለት ሚክ መደሰቱን ገልጦለታል።

የዘንድሮ 11ኛው ዙር ውድድር ትናንት የከናወበት ኑይርበርግሪንግ ከተማ የ51 ዓመቱ ሚሻኤል ሹማኸር የዛሬ 25 ዓመት ለድል የበቃበት ነው።

የሚሻኤል ሹማኸር ልጅ ሚክ ሹማኸር የፎርሙላ 2 ተወዳዳሪ ነው። በሰበሰበው 191 ነጥብም አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል በአኹኑ ወቅት። ካሉም ኢሎት በ169 ነጥብ ኹለተኛ ነው። ሚክ ሹማኸር ወደፊት ወደ ፎርሙላ አንድ የማደግ ዕድሉ ሰፊ እንደኾነ ተዘግቧል።

Der neue Ferrari-F2004 wird in Maranello vorgestellt
ምስል AP

በፌራሪ እና አል ሮሜዎ መወዳደሪያዎች የፎርሙላ አንድ ሙከራ አድርጎ ለውድርሩ ብቃት እንዳለውም አስመስክሯል። በአልፋ ሮሜዎ ዐርብ እለት ነበር እንዲለማመድ የተፈቀደለት። ከዚያ በፊት አባቱ የዛሬ 16 ዓመት ለ7ኛ እና ለመጨረሻ ጊዜ አሸነፊ በኾነባት (F2004) ፌራሪ ነበር ለልምምድ ብቅ ያለው።

የፎርሙላ 3 ተወዳዳሪ ከነበረበት ጊዜ አንስቶም ግቡ የፎርሙላ አንድ ላይ ተወዳድሮ ድል ማድረግ እንደኾን በተደጋጋሚ ገልጧል። ሚሻኤል ሹማኸርን በፌራሪ ይተካል የተባለለት ጀርመናዊው ሰባስቲያን ፌትል ብዙም አልተሳካለትም። ምናልባት ወጣቱ ሚክ ሹማኸር ይሳካለት ይኾናል።

የሜዳ ቴኒስ

በሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ ኖቫክ ጄኮቪችን የረታው የዓለም ኮከቡ ስፔናዊ ራፋኤል ናዳል ከዋነኛ ተቀናቃኙ ሮጄር ፌዴሬር ጋር መስተካከል ችሏል። ራፋኤል ናዳል 13ኛ የፈረንሳይ ውድድር ድሉን ትናንት ሲያስመዘግብ 6 ለ0፣ 6 ለ2 እና 7 ለ5 ነበር ማሸነፍ የቻለው። በዚህም መሠረት ከሮጄር ፌዴሬር የ20 ጊዜያት ድል ጋር ተስተካክሏል። የፈረንሳይ የሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ ለወትሮው የሚካኼደው ግንቦት ወር ላይ ነበር። ነገር ግን በኮሮና ተሐዋሲ ስርጭት የተነሳ ውድድሩ ሊገፋ ችሏል።

Tennis Roland Garros - Finale | Rafael Nadal gewinnt
ምስል Christian Hartmann/Reuters

በተመሳሳይ የሴቶች ውድድር የ19 ዓመቷ ወጣት ፖላንዳዊቷ ኢጋ ስዊያቴክ ተጋጣሚዋ ሶፊያ ኬኒን 6ለ 4 እና 6 ለ1 ማሸነፍ ችላለች። በዚህም መሰረት ፖላንዳዊቷ ወጣት በእንዲህ አይነቱ ግዙፍ የሜዳ ቴኒስ ለድል ስትበቃ የመጀመሪያዋ መኾን ችላለች። በዓለም አቀፍ ውድድር ቁጥር 54 ላይ የምትገኘው ይኽች ተወዳዳሪ ለዚህ አይነቱ ድል መብቃቷ በርካታዎችን አስደምሟል።

እግር ኳስ

የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ሰሞኑን የወዳጅነት እና የኔሽን ሊግ ውድድሮችን አድርጎ ያሳየው እንቅስቃሴ እና ውጤት ከዚህ በፊት የነበረው ብቃቱ ላይ ያለ አያስመስለውም። የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ዮአኺም ሎይቭ ተጨዋቾቻቸው በረቡዕ ግጥሚያ የተሻለ ብቃት እንዲያሳዩ አሳስበዋል። ጀርመን ረቡዕ ከስዊዘርላንድ ጋር የኔሽን ሊግ ግጥሚያ አላት። በመጀመሪያ የኔሽን ሊግ ግጥሚያ ወደ ዩክሬይን ያቀናው ቡድን ዩክሬንን 2 ለ1 ማሸነፍ የቻለው ከብዙ ትግል በኋላ ነበር። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን በአማካዩ ቶኒ ክሮስ እና ዮሱዋ ኪሚሽ ግቦች ለድል ቢበቃም የዩክሬን ተጨዋቾች ኳስ በማስጣል እና በማጨናገፍ ቡድኑን ማስጨነቅ ተሳክቶላቸዋል።

Fußball | Nations League | Deutschland - Spanien
ምስል picture-alliance/dpa/C. Charisius

አሰልጣኙ ዛሬ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፦ «በደንብ ቀልብ እንዲሰበሰብ እፈልጋለሁ፤ ድፍረት እና ጥንቅቅ ያሉ ኳሶችን ማየት እሻለሁ» ብለዋል። ቡድናቸው በትክክለኛው ሰአት ወደ ፊት የመፈትለክ ውሳኔ እንዲታይበትም ፍላጎታቸውን ገልጠዋል። በተዘዋዋሪ ከዚህ ቀደም የታዩ የተጨዋቾች ስኅተቶችን ስም ሳይጠሩ ወርፈዋል። ኾኖም ከቱርክ ጋር በነበረው የወዳጅነት ግጥሚያ ሦስት ጊዜ ቡድናቸው እየመራ ሦስት እኩል ከመውጣቱ አንጻር የዩክሬኑ የጠበበ ድልን «ጠቃሚ ውጤት» ነው ብለውታል። ቡድናቸው የማሸነፍ ፍላጎት እንዳለው ያመላክታልም ሲሉ አክለዋል።

ከአሰልጣኙ ጋር ዛሬ ለቃለ መጠይቅ የታደመው ሌዮን ጎሬትስካ የቡድኑ አባላት ከዩክሬን ጋር ሲጫወቱ ከነበረው የተሻለ እንዲያሳዩ ይፈልጋል። «ያለቦታቸው የሚላኩ ድንገተና ኮሶች ሲሻገሩ ነበር። ቴክኒካዊ ችግርም ነበረባቸው። በደንብ ያለቀለት ኳሶችን ብናቀብል ኖሮ በሰፋ ልዩነት ባሸነፍን ነበር» ሲል በቡድኑ ያለፈ ግጥሚያ ደስተኛ አለመኾኑን ዐሳውቋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ