1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥቅምት 16 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥቅምት 16 2013

በእንግሊዝ ፕሬሚየ ርሊግ መሪው ኤቨርተን በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ነጥብ መጣሉ ሊቨርፑል በነጥብ እንዲስተካከለው ዕድል ከፍቷል። በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየር ሙይንሽን አይንትራኅት ፍራንክፉርትን በሰፋ የግብ ልዩነት አሸንፏል። በላሊጋው ሁለቱ ኃያላን ቡድኖች ተጋጥመው ባርሴሎና በሪያል ማድሪድ ሽንፈት ገጥሞታል።  

https://p.dw.com/p/3kSpZ
Fussball I Chelsea v Liverpool
ምስል Jason Cairnduff/AFP/Getty Images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ከሁለት ሳምንት ቆይታ በኋላ ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ግጥሚያውን በደርሶ መልስ የሚያከናውነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የወዳጅነት ጨዋታዎቹን ተሸንፏል። ጨዋታዎቹን ስታዲየም ውስጥ ገብቶ ከተከታተለ የእግር ኳስ ስፖርት ጋዜጠኛ ጋር ቡድኑ ሊያሻሽል ስለሚገባቸው ነጥቦች ቃለ መጠይቅ አድርገናል። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ሌዊስ ሐሚልተን በጀርመናዊው ሚሻኤል ሹማኸር ተይዞ የቆየውን ክብረ ወሰን መስበር ችሏል። በእንግሊዝ ፕሬሚየ ርሊግ መሪው ኤቨርተን በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ነጥብ መጣሉ ሊቨርፑል በነጥብ እንዲስተካከለው ዕድል ከፍቷል። በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየር ሙይንሽን አይንትራኅት ፍራንክፉርትን በሰፋ የግብ ልዩነት አሸንፏል። በላሊጋው ሁለቱ ኃያላን ቡድኖች ተጋጥመው ባርሴሎና በሪያል ማድሪድ ሽንፈት ገጥሞታል። 

ወደ እንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፤ የጀርመን ቡንደስሊጋ እና የስፔን ላሊጋ የእግር ኳስ ግጥሚያ ውጤቶች ከማለፋችን አስቀድሞ ስለ ኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አጠር ያለ ቃለመጠይቅ እናሰማችሁ። ከዛምቢያ ጋር ለወዳጅነት ተጋጥሞ ትናንት 3 ለ1 የተሸነፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አቋም እና የጨዋታ እንቅስቃሴን ስታዲየም ገብቶ የተከታተለው የእግር ኳስ ጋዜጠኛው ዖምና ታደለ እንዲህ ቃኝቶታል።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ዛሬ ማታ ቶትንሃም ከበርንሌይ እንዲሁም ዌስት ብሮሚች ከብራይቶን ጋር ይጋጠማሉ። ዌስት ብሮሚች እና በርንሌይ 17ኛ እና 18ኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኙት። ተጋጣሚዎቹ ቶትንሃም እና ብራይቶን ደግሞ 11ኛ እና 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

Fussball I Chelsea v Liverpool
ምስል Matt Dunham/Getty Images

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተደረጉ ግጥሚያዎች የደረጃ ሰንጠረዡ መሪ ኤቨርተን በሳውዝሐምፕተን 2 ለ0 በመሸነፉ ለሊቨርፑል መልካም አጋጣሚ ኾኗል። ሊቨርፑል ቅዳሜ ዕለት ሼፊልድ ዩናይትድን 2 ለ1 ድል በማድረጉ ከኤቨርተን ጋር እኩል 13 ነጥብ ይዞ በግብ ክፍያ ብቻ ተበልጦ ኹለተኛ ደረጃ ላይ መስፈር ችሏል። በቅዳሜው ጨዋታ ሳውዝ ሐምፕተን ኤቨርተን በጨዋታ በልጦ ነበር ያሸነፈው። በእርግጥ የኤቨርተኑ ሉቃስ ዲግኔ በ72ኛው ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ ከሜዳ ቢሰናበትበትም ማለት ነው። በአንጻሩ ወሳኝ ተከላካዩ ቫን ጂያክን በጉዳት ማሰለፍ ያልቻለው ሊቨርፑል ካለፈው ግጥሚያ አንጻር በተከላካይ መስመሩ በኩል የተሻለ እንቅስቃሴ ማሳየት ችሏል።

በቀጣይ ግጥሚያ ኤቨርተን ከኒውካስል ጋር እንዲሁም ሊቨርፑል ከዌስት ሐም ጋር የሚያደርጓቸው ግጥሚያዎች የደረጃ ሰንጠረዡ መሪ በውል እንዲለይ ያስችላሉ። አስቶን ቪላ 12 ነጥብ ይዞ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ላይስተር ሲቲ በተመሳሳይ 12 እንዲሁም ሊድስ ዩናይትድ በ10 ነጥብ ሦስተኛ እና አራተኛ ኾነው ይከተላሉ። ቸልሲ እና አርሰናል 9 ነጥብ ይዘው ደረጃቸው 9ኛ እbና 10ኛ ነው። 8 ነጥብ ያለው ማንቸስተር ሲቲ 13ኛ እንዲሁም ማንቸስተር ዩናይትድ በ7 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ናቸው።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያውዎች ባየር ሙይንሽን እንደለመደው በግብ ተንበሽብሿል። ተጋጣሚው አይንትራኅት ፍራንክፉርትን 5 ለ0 አሰናብቶ በደረጃ ሰንጠረዡ 12 ነጥብ መሰብሰብ ችሏል።  ከመሪው ላይፕሲሽ በአንድ ነጥብ ቢለይም በርካታ የግብ ክፍያዎች ግን አሉት። መሪው ላይፕሲሽ ቅዳሜ ዕለት ሔርታ ቤርሊንን 2 ለ 1 ድል አድርጓል። በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቦሩስያ ዶርትሙንድም ከላይፕሲሽ በአንድ ነጥብ ብቻ ተበልጦ ከባየር ሙይንሽን ጋር ተመሳሳይ 12 ነጥብ መሰብሰብ ችሏል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ትናንት መከረኛው ሻልከን 3 ለ0 አሰናብቷል።

Deutschland Bundesliga - Werder Bremen v TSG 1899 Hoffenheim
ምስል Carmen Jaspersen/dpa/picture-alliance

በሲግናል ኢዱና ፕርክ ስታዲየም በተከናወነው ግጥሚያ ሻልከ እስከ 55ኛው ደቂቃ ድረስ ግብ ሳይቆጠርበት መዝለቅ ችሎ ነበር። ኾኖም አመሉ አለው ብሎት በ55ኛው፤ 61ኛው እና 78ኛው ደቂቃዎች ላይ፦ በተከላካዩ ማኑዌል አካንጂ፣ ኧርሊንግ ሃላንድ እና ማትስ ሑመል ግቦች አንገቱን ደፍቶ ወጥቷል። በሻልከ እና ቦሩስያ ዶርትሙንድ መካከል የነበረው ግጥሚያ በአንድ አካባቢ ቡድኖች መካከል የሚደረግ ደርቢ ግጥሚያ ስለነበር በርካቶች በጉጉት ጠብቀውት ነበር። በቅዳሜው ግጥሚያ የኧርሊንግ ሃላንድ እና የጄደን ሳንቾ ቅንጅት ድንቅ ነበር።

ላሊጋ

በስፔን ላሊጋ የእግር ኳስ ውድድር ቅዳሜ ዕለት ሽንፈት የገጠመው ባርሴሎና ወደታች ሲያሽቆለቊል አሸናፊው ሪያል ማድሪድ በደረጃ ሰንጠረዡ ኹለተኛነቱን አስጠብቋል። ባርሴሎናን 3 ለ1 ድል በማድረጉም ሪያል ማድሪድ ከመሪው ሪያል ሲሲዬዳድ የሚበለጠው በአንድ ነጥብ ብቻ ነው። 13 ነጥብ አለው። 14 ነጥብ ያለው ሪያል ሶሲዬዳድ የግብ ክፍያ ግን በርካታ ነው። ግራናዳ በ13 ነጥብ 3ኛ፣ ቪላሪያል በ12 ነጥብ 4ኛ እንዲሁም አትሌቲኮ ማድሪድ 11 ነጥብ ይዞ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ባርሴሎና 7 ነጥብ ብቻ ሰብስቦ 12ኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው።  ሴቪያ፣ ቫሌንሺያ እና አላቬስ እንደ ባርሴሎና ተመሳሳይ 7 ነጥብ ይዘው ከ13ኛ እስከ 15ኛ ደረጃ ተደርድረዋል።

የመኪና ሽቅድምድም

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ብሪታኒያዊው ሌዊስ ሐሚልተን በጀርመናዊው አሽከርካሪ ሚሻኤል ሹማኸር ላለፉት 14 ዓመታት ተይዞ የቆየውን ክብረ ወሰን መስበር ቻለ።  ሌዊስ ሀሚልተን ክብረወሰኑን የሰበረው በፖርቹጋል ግራንድ ፕሪ ሽቅድምድም ከሌላኛው የመርሴዲስ አሽከርካሪ የቡድን አባሉ በ25 ሰከንድ ቀድሞ ድል ካደረገ በኋላ ነው። የትናንትና ድሉ ሲደመር ሌዊስ ሀሚልተን በአጠቃላይ የፎርሙላ አንድ ሽቅድምድም 92 ጊዜያት በማሸነፍ ብቃቱን አስመስክሯል።

Formel 1 |  Lewis Hamilton gewinnt großen Preis von Portugal
ምስል Jose Sena Goulao/Reuters

የራስ ቅሉ ላይ በደረሰበት አደጋ ራሱን ስቶ የሚገኘው ሚሻኤል ሹማኸር ለ91 ጊዜያት የፎርሙላ አንድ አሸናፊ በመኾን ክብረወሰኑን ይዞ ቆይቶ ነበር። አኹን ሌዊስ ሐሚልተን የቀረው በዓለም የመኪና ሽቅድምድም ፍጻሜ እንደ ሚሻኤል ሹማኸር ለሰባት ጊዜያት ለማሸነፍ አንድ የውድድር ዘመን አሸናፊ መኾን ነው። ለ19 ዓመታት የፎርሙላ አንድ ተፎካካሪ የነበረው ሚሻኤል ሹማኸር በዓለም የመኪና ሽቅድምድም ፍጻሜ 7 ጊዜያት አሸንፏል።  ሌዊስ ሐሚልተን በበኩሉ እስካሁን ለ6 ጊዜያት ማሸነፍ ችሏል። በአጠቃላይ የፎርሙላ አንድ ውድድር ግን ለ14 ዓመታት የተወዳደረው ሌዊስ ሐሚልተን ትናንት ክብረወሰኑን ሰብሯል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ