1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥር 8 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥር 8 2015

ሊዮኔል ሜሲን ለማስመጣት የሳዑዲ ዐረቢያው ቡድን እጅግ በርካታ ገንዘብ አዘጋጅቷል፤ ሜሲ ወደ አል ሒላል ቡድን የሚያቀና ከሆነ ከክርስቲያኖ ሮናልዶም በላይ እንደሚከፈለው ነው ሰሞኑን የተዘገበው። በተለያዩ የአትሌቲክስ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን ድል ቀንቷቸዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አርሰናል የከፍታውን ሊቨርፑል የቁልቁለቱን ጎዳና ተያይዘውታል።

https://p.dw.com/p/4MGsq
WM 2022 - Argentinien - FInale Messi Bischt
ምስል Tom Weller/dpa/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

አርጀንቲናዊው የኳስ ጠቢብ ሊዮኔል ሜሲን ለማስመጣት የሳዑዲ ዐረቢያው ቡድን እጅግ በርካታ ገንዘብ አዘጋጅቷል። ሊዮኔል ሜሲ ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ የአል ሒላል ቡድን የሚያቀና ከሆነ ከክርስቲያኖ ሮናልዶም በላይ እንደሚከፈለው ነው ሰሞኑን የተዘገበው። በተለያዩ የአትሌቲክስ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን ድል ቀንቷቸዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አርሰናል የከፍታውን ሊቨርፑል ደግሞ የቁልቁለቱን ጎዳና ተያይዘውታል። 

አትሌቲክስ፦

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት የዐለም ዘርፍ የኋላው ስፔን ውስጥ በተደረገ የጎዳና ሩጫ ፉክክር የራሷን የዐለም ክብረወሰን ለጥቂት በአምስት ሰከንዶች ልዩነት ሳትሰብር ቀረች። በ15ኛው የቫለንሺያ የ10 ኪሎ ሜትር ርቀት የሩጫ ውድድር የዐለም ዘርፍ ያሸነፈችው 29 ደቂቃ ከ19 ሰከንድ ሮጣ በማጠናቀቅ ነው። ኬንያውያቱ ጄስካ ቼላንጋት እና ኤስተር ቢሩንዱ ቦሩራ ከ42 እና 56 ሰከንዶች በኋላ ተከታትለው በመግባት ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

1o ሺህ ሯጮች በታደሙበት የትናንቱ የቫለንሺያ የ10 ኪሎ ሜትር ፉክክር በወንዶች ኬንያውያን ሙሉ ለሙሉ የበላይ ሆነው አጠናቀዋል። ዌልዶን ኪፕኪሩይ ላንጋት 10 ሺህ ሜትሩን በአንደኛነት ለማጠናቀቅ የወሰደበት ጊዜ 26 ደቂቃ ከ55 ሰከንድ ነው። ቻርልስ ላንጋት በ2 ሰከንድ ልዩነት የሁለተኛ ደረጃ አግኝቷል። ዳንኤል ቱማካ ኮሴን ከአራት ሰከንዶች በኋላ ቻርልስን ተከትሎ በመግባት የሦስተኛ ደረጃውንም ለኬንያ አድርጓል። ኢትዮጵያውያን ወንድ አትሌቶች ባልተሳተፉበት በዚህ ፉክክር ለጀርመን ተሰልፎ የሚሮጠው ትውልደ ኢትዮጵያዊ አትሌት አማናል ጴጥሮስ 18ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

Olympia 2008 Äthiopien Gold für Tirunesh Dibaba 10000 m Lauf
አንጋፋዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በ2008 በኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባገኘችበት ወቅት፤ ፎቶ ከማኅደርምስል picture-alliance/ dpa

ዩናይትድ ስቴትስ ሒውስተን ውስጥ በተከናወኑ የግማሽ ማራቶን ሩጫ ፉክክሮች በወንድም በሴትም ኢትዮጵያውያን ድል ተቀዳጅተዋል። በወንዶች ፉክክር አትሌት ልዑል ገብረ ሥላሴ ዐለም 1 ሰአት ከ34 ሰከንዶች በመሮጥ የአንደኛነት ደረጃን አግኝቷል። የኬንያው ሯጭ ዌስሌይ ኪፕቶ በልዑል ለጥቂት በ1 ሰከንድ ተበልጦ የሁለተኛ ደረጃን ይዟል። ሞሮኮዊያዊው አትሌት ሞሐመድ ኤል አራቢ በ1 ሰአት ከ58 ደቂቃ በመሮጥ ሦስተኛ ሆኗል።

በሴቶች ተመሳሳይ የግማሽ ማራቶን ሩጫም ድሉ የኢትዮጵያ ሆኗል። አትሌት ሕይወት ገብረ ማሪያም ርቀቱን በ1 ሰአት ከ6 ደቂቃ ከ28 ሰከንድ በማጠናቀቅ በአንደኛነት አሸንፋለች። የዩናይትድ ስቴትሷ ራጭ ኤሚሊ ሲሶን እንዲሁም የብሪታንያዋ አትሌት ጄሲካ ዋርነር-ጁድ የሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን አግኝተዋል። ከአራት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሩጫ ፉክክር የተመለሰችው አንጋፋዋ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ 16ኛ ደረጃን አግኝታለች። ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜም 1 ሰአት ከ11 ደቂቃ ከ35 ሰከንድ ነው። ሌላኛዋ የዲባባ ልጅ ተስፋ የተጣለባት አትሌት አና ዲባባ 1 ሰአት ከ09 ደቂቃ ከ22 ሰከንድ በመሮጥ የ4ኛ ደረጃን አግኝታለች።

እግር ኳስ

ለሀገር ውስጥ ቡድኖች ብቻ የሚሰለፉ ተጨዋቾች በሚሳተፉበት የአፍሪቃ ሃገራት ሻምፒዮን (CHAN) ውድድር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁለተኛ የምድብ ጨዋታውን ነገ በስታድ ደ ባራኪ ስታዲየም ያከናውናል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጋጣሚ የአልጄሪያ ቡድን ነው። ቅዳሜ ደግሞ የምድቡ ሦስተኛ ግጥሚያውን ከሊቢያ ጋር ያደርጋል። ሊቢያ ከአልጄሪያ ጋር በነበረው የመጀመሪያ ጨዋታው ብርቱ ተፎካካሪ ሆኖ እጅግ በጠበበ የግብ ልዩነት ነው የተሸነፈው።

CHAN qualification game in Mekele Äthiopien
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በአፍሪቃ ሃገራት ሻምፒዮን (CHAN) ፎቶ፦ ከማኅደርምስል DW/M. Haileselassie

እስካሁን በነበሩ ውጤቶች የመጀመርያ ጨዋታውን ከሞዛምቢክ ጋር ጥር 6 ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በኔልሰን ማንዴላ ስታዲየም ያከናወነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያለምንም ግብ ተለያይቷል። በጨዋታው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአንድም ሦስቴ ግብ ሊሆኑ የሚችሉ አጋጣሚዎችን አግኝቶ በሞዛምቢኩ ግብ ጠባቂ ብርታት እንዲሁም ዒላማን በመሳት መክነዋል። ከሞዛምቢክ ጋር ኢትዮጵያ ነጥብ በተጋራችበት ጨዋታ ጋቶች ፓኖም የውድድሩ ኮከብ ሆኗል። ከኢትዮጵያ ቡድን ጋር በአንድ ምድብ የተደለደለችው አልጄሪያ ዐርብ ዕለት በስታድ ደ ባራኪ ስታዲየም ሊቢያን 1 ለ0 አሸንፋለች። በዚህም መሠረት «የበረሃ ቀበሮዎች» በሚል ቅጽል የሚትታወቀው አልጄሪያ ምድቡን በ3 ነጥብ ትመራለች። ኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ በተመሳሳይ ነጥብ ያለምንም ግብ ሁለተኛ ደረጃ ይዘዋል። ሊቢያ በ0 ነጥብ የምድቡ መጨረሻ ላይ ነች።  ለመሆኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቻን ውድድር አቋሙ ምን ይመስላል? ተፎካካሪ ቡድኖቹስ? የእግር ኳስ ተንታኝ እና «ከሜዳ ውጪ» የተሰኘውን ጨምሮ የተለያዩ ለኅትመት የበቁ መጽሐፍትን አዘጋጅ ዘርዓይ እያሱ ውድድሮቹን ተመልክቷል።

በዚህ ውድድር ለሁለት ጊዜያት ዋንጫ ማንሳት የቻለው የሞሮኮ ቡድን ከአልጄሪያ ጋር በገባው ፖለቲካዊ ውዝግብ የተነሳ ከውድድሩ ራሱን አሰናብቷል። የሞሮኮ ቡድን ከራባት ከተማ ውድድሩ ሊካሄድበት ወደነበረበት ኮንስታንቲን ከተማ በቀጥታ ካልበረርኩ ሲል ያቀረበውን ጥያቄ አልጀሪያ ውድቅ በማድረምጓ በውድድሩ ሳይሳተፍ ቀርቷል። አልጀሪያ እና ሞሮኮ ከዓመት ከመንፈቅ በፊት በዲፕሎማሲ ውዝግብ የተነሳ የአየር ክልላቸውን ዘግተው ከአንዱ አገር ወደሌላኛው የቀጥታ በረራ ማድረግ አይቻልም። የአትላስ አናብስቱ የሞሮኮ ቡድን በውድድሩ ላይ ባለመገኘቱ የካፍ ቅጣት ይጠብቀዋል። ሞሮኮ በውድድሩ ባለመሳተፉም ተጋጣሚው ሱዳን በፎርፌ አሸናፊ መሆን ችሏል። ሞሮኮ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚሰለፉ ተጨዋቾች ያሉበት የቻንም ሆነ ሌላኛው ብሔራዊ ቡድኗን አፍሪቃ ውስጥ የሚስተካከል የለም። ባለፈው ዐርብ ጥር 5 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የጀመረው የቻን ውድድር ከሦስት ሳምንታት ፉክክር በኋላ ቅዳሜ ጥር 27 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ይጠናቀቃል።

 Marokko Fußballnationalmannschaft
የሞሮኮ የእግር ኳስ ቡድን በአፍሪቃ ሃገራት ሻምፒዮን (CHAN) ፎቶ፦ ከማኅደርምስል picture-alliance/AA/J. Morchihi

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አርሰናልን የሚያቆመው አልተገኘም። አርሰናል ትናንት ከቶትንሀም ጋር ባደረገው ግጥሚያ 2 ለ0 አሸንፏል። የዘንድሮ ፉክክር ዋነኛ ተቀናቃኙ ማንቸስተር ሲቲ በማንቸስተር ዩናይትድ የ2 ለ1 ሽንፈት መግጠሙም ለአርሰናል ሌላ ፌሽታ ነበር። ቅዳሜ ማንቸስተር ዩናይትድ በኦልድ ትራፎርድ ስታዲየም ሜዳው ያስተናገደው የከተማው ቡድን ማንቸስተር ሲቲን ያሸነፈው በኳስ ይዞታ እጅግ በከፍተኛ ልዩነት ተበልጦም ነበር። ነጥብ የጣለው ማንቸስተር ሲቲ 39 ነጥብ ይዞ በደረጃ ሰንጠረዡ 2ኛ ላይ ይገኛል። መሪው አርሰናል በ47 ነጥብ በአንደኛነት ተኮፍሷል።  ሦስተኛ ደረጃ ላይ ያለው ኒውካስል 19ኛ ማንቸስተር ዩናይትድ 18 ጨዋታ አከናውነው እኩል 38 ነጥብ ይዘው በግብ ልዩነት ይበላለጣሉ። 19ኛ ጨዋታውን ያጠናቀቀው ቶትንሀም በ33 ነጥብ የ4ኛ ደረጃን ይዟል። ከወዲሁ 20ኛ ጨዋታዎችን አከናውኖ 31 ነጥብ የሰበሰበው ፉልሀም 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ብራይተን እና ብሬንትፎርድ ሊቨርፑልን በልጠው 8ኛ እና 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ተደጋጋሚ ሽንፈትን ያስተናገደው የዬርገን ክሎፕ ሊቨርፑል ቅዳሜ ዕለትም በብራይተን የ3 ለ0 ሽንፈት ገጥሞት ወደ 9ኛ ደረጃ ተንሸራቷል። በ28 ነጥቡም ተወስኗል። ዌስትሀም ዩናይትድ፤ ኤቨርተን እና ሳውዝሀምፕተን ከ18ኛ እስከ 20ኛ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ተደርድረዋል።

Argentinien | Empfang der Fußballnationalmannschaft in Buenos Aires
የአል-ሒላል ቡድን ሊዮኔል ሜሲን ለማስፈረም በርካታ ሚሊone አዘጋጅቷል፤ ፎቶ ከማኅደርምስል Martin Villar/REUTERS

በሳዑዲ ዐረቢያ ሊግ በተደጋጋሚ ዋንጫ በመውሰድ ክብረ ወሰን የያዘው የአል-ሒላል ቡድን ሊዮኔል ሜሲን ለማስፈረም በእየ ጨዋታ ዘመኑ የሚከፈል የ280 ሚሊዮን ዩሮ ክፍያ አቅርቦለታል። ከክፍያው የተወሰነው ሳዑዲ ዐረቢያ በ2030 ከግብጽ እና ግሪክ ጋር በጋራ የዐለም ዋንጫ ውድድርን ለማዘጋጀት ለጀመረችው ዘመቻ የሚውል ነው ተብሏል። ቀደም ሲል የአል-ሒላል ዋነኛ ተቀናቃኝ ቡድን አል-ናስር ክርስቲያኖ ሮናልዶን በከፍተኛ ክፍያ ማስፈረሙ ይታወቃል። ከፓሪስ ሳንጃርሞ ጋር የፈረመው ውል ከጥቂት ወራት በኋላ የሚጠናቀቀው ሊዮኔል ሜሲ ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ቡድን የሚያቀና ከሆነ ከክርስቲያኖ ሮናልዶ የበለጠ ተከፋይ ይሆናል ማለት ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

ኂሩት መለሰ