1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥላቻ ንግግር ህግ በአፍሪቃና የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት

ቅዳሜ፣ የካቲት 14 2012

በኢትዮጵያ ብሄርና ሀይማኖት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች እንዲሁም ጥቃት የታከለበት አመፅና ተቃዉሞ  የተለመዱ ጉዳዮች ሆነዋል። በኢንተርኔት በሚሰራጩ የጥላቻ፣ ያልተረጋገጡና የተዛቡ መረጃዎች ደግሞ ሁኔታዉን አባብሰዉታል በሚል የሀገሪቱ ፓርላማ የበይነ-መረብ የጥላቻ ንግግሮችንና የተዛቡ መረጃዎችን  ለመቆጣጠር የሚያስችል ህግ ያለፈዉ ሀሙስ አፅድቋል።

https://p.dw.com/p/3Y9qm
Äthiopien Addis Ababa | Parlament diskutiert Anti-Hassrede und Missinformationsgesetz
ምስል DW/Y. Gebrezihaber

ትኩረት በአፍሪቃ

 
በኢትዮጵያ ብሄርና ሀይማኖት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች እንዲሁም ጥቃት የታከለበት አመፅና ተቃዉሞ  የተለመዱ ጉዳዮች ሆነዋል። በኢንተርኔት በሚሰራጩ የጥላቻ፣ ያልተረጋገጡና የተዛቡ መረጃዎች ደግሞ ሁኔታዉን አባብሰዉታል በሚል የሀገሪቱ ፓርላማ የበይነ- መረብ የጥላቻ ንግግሮችንና የተዛቡ መረጃዎችን  ለመቆጣጠር የሚያስችል ህግ ያለፈዉ ሀሙስ አፅድቋል።አዲሱ የጥላቻ ህግ አንድን ግለሰብ ወይም ቡድን በብሄር ማንነቱ፣በሀይማኖቱ፣በዜግነቱ፣በፃታዉና በአካል ጉዳተኝነቱ ላይ ተመርኩዞ መገለልን የሚፈጥር ንግግር ማድረግን የጥላቻ ንግግር ነዉ ብሎ ይተረጉመዋል።።በዚህ መሰረት ህጉን የሚጣረሱ  የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች እስከ ሶስት ዓመት እስራትና የመቶ ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።በጥላቻ ንግግሩ ሳቢያ ግለሰብ ወይም ቡድን የአካል ጉዳት ያደረበት  ከሆነ ደግሞ ቅጣቱ እስከ አምስት አመት እስራት ሊዘልቅ ይችላል። ይህ ህግ በህግ አዉጭዎች ዘንድ ማንነት ላይ ያተኮሩ ጥቃቶችን ለማስቆም ተገቢ ተደርጎ ቢወሰድም  በጋዜጠኞች  በመብት ተሟጋቶችና  ጦማሪያን ዘንድ ትችት እየቀረበበት ነዉ። ህጉ በመጭዉ ነሀሴ ከሚካሄደዉ  ሀገራዊ ምርጫ በፊት መንግስት  የተቃዉሞ ድምጾችን ለማፈን ያዉለዋል የሚል ስጋትም አሳድሯል።የድህረ ገፅ ፀሀፊዉ በፈቃዱ ሀይሉም ይህንን ስጋት ይጋራል።እሱ እንደሚለዉ መንግስት ሀሳቡን በነፃነት በሚገለፀዉ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚ ላይ ገደብ ከመጣል ይልቅ ሌሎች ችግሮች ላይ ቢያተኩር የተሻለ ነዉ ይላል።
«እንደሚታወቀዉ የጥላቻ ንግግር ህግ የመናገር ነፃነትን ከሚገድቡ ህጎች አንዱ ነዉ።ራሳቸዉን በኢንተርኔት የሚገልፁ ሰዎችን በኢትዮጵያ ለከተሰተዉ  ነገር ሁሉ ተወቃሽ ማድረግ ትክክል አይደለም።ምክንያቱም የችግሩ መነሻ መሬት ላይ ያለዉ ነዉ።ይህም በገዡ ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የሚካሄደዉ ፉክክር ነዉ።።መንግስት የድረ ገፅና የህትመት መገናኛ ብዙሃንን  ከመገደብ ይልቅ ችግሩን ከመነሻዉ መፍታት አለበት ብዬ አስባለሁ።»
ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ አንድ  የህግና የዲሞክራሲ  ማሻሻያ ማዕከል  ሀላፊ እንዳሉትም ሕጉ ብዙ ጋዜጠኞች ፅሁፋቸዉን ከማተም እና የፕሬስ ነፃነት መብታቸውን ከመጠቀም የሚከለክል ነዉ።ይህን መሰሉን ህግ ስታወጣ ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ አፍሪቃዊት ሀገር አይደለችም።የጥላቻ ንግግር ህግ የአዉሮፓ ሀገራትም ከረጅም ጊዜ አንስቶ ይጠቀሙበታል።በጀርመንም« የአዉታረ-መረብ  አስገዳጅ ህግ» በመባል የሚታወቅ በኢንተርኔት የሚደረግን የጥላቻ ወንጀል ለመከላከል በጎርጎሮያኑ 2018 ወጥቷል። ይህንና ሌሎች  ይህንን የመሳሰሉ የአዉሮፓ ህጎች ለኢትዮጵያ መንግስት አምሳያ ሆነዉ ማገልገላቸዉንም ጦማሪ በፈቃዱ ይገልፃል።ነገር ግን ለአዉሮፓ ጠቃሚና ትርጉም የሚሰጥ አንድ ህግ በአፍሪቃ የፕሬስ ነፃነት ላይ በጣም አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር  ይችላል ባይ ነዉ።ምክንያቱም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ጠንካራና ገለልተኛ የፍትህ ተቋማ እጥረት አለ።የዳኝነት ስርዓቱም ቢሆን ዉሱንነት ያለዉ ነዉ። ከዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሂዉማን ራይትስ ወች የአፍሪቃ ከፍተኛ ተመራማሪ ሊቲሺያ ባደርም ህጉ አሳስቦናል ይላሉ።  
«ረቂቅ ህጉ ጥቃት የተቀላቀለበት የተቃዎሞ አመፅ  ከተቀሰቀሰና ልዩ ሁከት ከተፈጠረ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ነዉ በካቢኔው  የቀረበው ። በተቃውሞ ሰልፈኞቹ ተፃራሪ የፀጥታ ሀይልም ነበር ።ሁለት ቀን በዘለቀዉ ጥቃት 86 ሰዎች ምናልባትም ከዚያ በላይ  ሰዎች ተገድለዋል። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ መንግስት  ህጉን በካቢኔው በኩል  አስተላልፏል። ይህንን ጉዳይ ይህንን የጥላቻ ንግግር ረቂቅ ህግ በጣም አሳሳቢ ሆኖ አግኝተነዋል።የዚህን  ሕግ  መዉጣት ሃሳብ የሚደግፉ ብዙ ሰዎች አሉ ።ነገር ግን በርካታ የሕግ ባለሙያዎችና  የሰብዓዊ መብት ተሟጋቶች በጣም አሳስቧቸዋል።»
ኬንያም በጎርጎሪያኑ በ2017 ዓ/ም የኢንተርኔት  የጥላቻ ንግግርን የሚከለክል ህግ አዉጥታለች ።በዚህ ወቅትም የኬንያ የህግ አዉጭዎች የጀርመንን ህግ እንደመነሻ መዉሰዳቸዉን  የሕግ ባለሙያዉ ጄምስ ማሻማ ገልጸዋል። ህጉ በሀገሪቱ በአጭር የፅሁፍ መልዕክቶችንና በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የሚፃፉ አላስፈላጊ የተባሉ የፖለቲካ ይዘቶችን እንዳይሰራጩ ከልክሏል።
ልክ እንደ ጀርመን ህግ የኬንያ የማኅበራዊ መገኛኛ ዘዴዎች አግልግሎት ሰጪዎች አላስፈላጊ የሆነ ይዘት ያላቸዉን ፅሁፎችና መልዕክቶችን በመመሪያዉ መሰረት በ24 ስዓት ዉስጥ እንዲሰረዙ ያደርጋሉ።የጀርመን ህግም ህገ ወጥ መልዕክቶች በ24 ስዓት ዉስጥ እንዲሰረዝ ይደነግጋል።ያ ካልሆነና ስህተቱ በተደጋጋሚ የሚፈጠር ከሆነ እስከ 50 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ መቀጮ ያስከፍላል።
ለኢንተርኔት ነጻነት የሚታገለዉ ጃኮብ ማቻንጋማ እንደ ጀርመን ያሉ ሀገራት አንዳንድ ህጎች በአፍሪቃ ሊያመጡ ስለሚችሉት ተፅዕኖ ማሰብ አለባቸዉ ይላል።
«ጀርመን  እንደ ዲሞክራሲ መሪ ሀገርነቷ ስለ ዓለም አቀፍ ጨቋኝ ህጎች ማሰብ አለባት።ይህ ህግ  በእርግጠኝነት  በአፍሪቃ ተቃዋሚዎችንና ከመንግስት ጥብቅ ቁጥጥር ለመሸሽ  በድረ-ገፅ ላይ እምነት በሚጥሉና የራሳቸዉን አዉታረ መረብ በሚፈጥሩ  ሰዎች ላይ ተፅዕኖ ሊያደርግ ይችላል።»
ያማለት ግን ጀርመን በኢንተርኔት ሳንሱር ተጠያቂ ትሆናለች ማለት እንዳልሆነ  የመብት ተሟጋቹ ማቻንጋማ ይገልፃል።ጀርመን ዲሞክራሲ የሰፈነባትና በርካታ መንግስትን  የሚቆጣጠሩ ተቋማት ስላሏት ይህንን ህግ ስታወጣ ለሳንሱር ላይሆን ይችላል።ነገር ግን የአፍሪቃ ሀገራት የጀርመንን ፈለግ ተከትለዉ ኢንተርኔትን በመቆጣጠር የራሳቸዉን ስልጣን የሚያስጠብቅ ህግ ሊያወጡ ይችላሉ ሲል ስጋቱን አያይዞ ገልጿል።
በዲሞክራሲና በመልካም አስተዳደር በሚወቀሱት የአፍሪቃ መንግስታት ይህ ህግ  በጣም ጥብቅና አፋኝ ሊሆን እንደሚችልም ናይጄሪያ ጥሩ ምሳሌ መሆኗን የሚናገሩ አሉ።የናይጄሪያ ሴኔት በአሁኑ ወቅት በኢንተርኔት ሀሳብን በነፃነት መግለፅ ላይ  ሁለት ጥብቅ  ጉዳዮችን እየተመለከተ ይገኛል።አንደኛዉ በበይነ መረብ መንግስትን የሚተቹ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃንን መዝጋትና እስከ ሶስት ዓመት በሚደርስ እስራት መቅጣት ፣ሌላዉና ሁለተኛዉ ደግሞ የሚፀድቅ ከሆነ እስከሞት ቅጣት ይደርሳል።
የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ሀይላት ስምምነት
በደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኬርና በአማፅያኑ መሪ ሪክ ማቻር መካከል ላለፉት 6 ዓመታት  የዘለቀዉን ግጭት ለማስቆም የሰላም ስምምነቱን መቀበላቸዉን ገልፀዋል።ሁለቱ ወገኞች ከዚሕ ቀደም በተያዘላቸዉ ቀነ ገደብ መሰረት ዛሬ ቅዳሜ ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት እንደሚመሰርቱ አረጋግጠዋል።የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳላቫ ኪር እና የቀድሞዉ አማፂ ቡድን መሪ ሪያክ ማቸር በጋራ ከመከሩ በኋላ ሰሞኑን በየግላቸዉ እንዳስታወቁት መንግስት ለመመስረት እስካሁን ያልተግባባቡቸዉን ጉዳዮች አጥርተዋል።ሁለቱ ወገኖች ተጣማሪ መንግሥት ለመመስረት ከተስማሙ ዓመት ከመንፈቅ ያለፋቸዉ ሲሆን የምስረታዉን ጊዜ ግን በሰበብ አስባቡ ሲያራዝሙ ነበር የቆዩት።ፕሬዝደንት ሳልቫኪር  ዋና ተቀናቃኛቸዉን ማቸርን ካነጋገሩ በኋላ እንዳሉት ማቸር የተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንትነቱን ስልጣን ይይዛሉ።ለእሳቸዉና ለፖለቲካ ፓርቲያቸዉ ባለስልጣናት በሙሉ ጥበቃና ከለላ እንደሚደረግላቸዉ ቃል ተገብቶላቸዋል።ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ የምስራቅና የአፍሪቃ ቀንድ ተንታኝና አማካሪ ማሪና ፒተር እንደሚሉት ግን በሁለቱ ተፋላሚ ሀይሎች መካከል ያለዉ አለመተማመን በቀላሉ ይፈታል ብለዉ አያስቡም።
« እርግጠኛ አይለሁም።እስካሁን ብዙ ያልተፈቱ ጉዳዬች አሉ።በሁለቱ ተፋላሚ ሀይሎች መካከል መተማመን የለም።በዚያዉ ልክ ጫና አለባቸዉ።የሱዳኑ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሀምዶክ እንዲሁም የኢጋድ ጫና አለ።እናም ሁለቱ ሀይሎች ይህንን የፈሩ ይመስላል። ካርቱም የሚገኙት ሪክ ማቻርም እዚያ ብዙ ላይቆዩ ይችላሉ።እናም በዓለም ዙሪያ ብዙ ጫና አለባቸዉ» 
ከዚህ በተጨማሪም  በስምምነቱ መሰረት የተቃዋሚ መሪዉን ሪክ ማቻርን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አድሮጎ መሾሙም ከሌሎች ተቃዋሚዎች አንፃር ሌላ የሚፈጥረዉ ችግር አለ ይላሉ።
« ችግሩ አሁንም ድረስ ብዙ ብርቱ ጉዳዮች አሉ።አዲስ መንግስት ይመሰረታል።ዋነኛዉ የተቃዋሚ መሪ ዶክተር  ሪክ ማቻር ተቀዳሚ ፕሬዝዳንት ይሆናሉ።ግን ሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲዎችም አሉ።ስለዚህ አራትና አምስት ምክትል ፕሬዝዳንቶች ሊኖሩ ነዉ።ስለዚህ ሁኔታዎች የበለጠ አስቸጋሪ ሊሆኑ ይችላሉ።» 
ከቀናት በፊት የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻር እንዳስታወቁት 32 የነበሩትን  የሀገሪቱን ግዛቶች ወደ 10 ማዉረድ  የስምምነቱ አንዱ አካል ነዉ።ከዚህ ሌላም ሶስት አስተዳደራዊ ቦታዎች አሉ ከነዚህ ዉስጥ ሁለቱ በነዳጅ ዘይት ሀብት የበለፀጉ መሆናቸዉ ደግሞ  ፒተር እንደሚሉት ሌላዉ የዉዝግብ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
 የሁለቱ ሀይሎች የዛሬዉ የአንድነት መንግስት ምስርታ በመስከረም ወር 2018  ዓ/ም በተካሄደዉ የሰላም ስምምነት  ቀን ተቆርጦለት የነበረ ሲሆን ከጎርጎሮሳዊዉ 2016 ጀምሮ በስደት ላይ የሚገኙት ሪክ ማቻር ላለመቀበል ሲያንገራግሩ የቆዩ ሲሆን ቀነ ገደቡ ከመጠናቀቁ ከሁለት ቀን በፊት ነበር ያለፈዉ  ሀሙስ ስምምነቱን መቀበላቸዉን የገለፁት። 
በደቡብ ሱዳን ለአምስት ዓመታት በዘለቀዉ የርስበርስ ግጭት ሚሊዮኖች ለስደትና ለረሀብ የተጋለጡ ሲሆን 400 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል።

Südsudan Salva Kiir und Riek Machar | Entscheidigung für  Einheitsregierung
ምስል Reuters/J. Solomun
Südsudan Salva Kiir und Riek Machar | Entscheidigung für  Einheitsregierung
ምስል AFP/A. McBride
Äthiopien Zone9 Blogger Gruppe
ምስል Zone9
Infografik Karte Internet Afrika EN (SPERRFRIST)

ፀሐይ ጫኔ

ኂሩት መለሰ