1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጣና በለስ የስኳር ልማት ፕሮጀክት የገበሬ እርግማን?

ረቡዕ፣ ጥር 6 2012

ለጣና በለስ የስኳር ፋብሪካዎችና የሸንኮራ አገዳ ልማት በጃዊ ወረዳ ከ50 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ ከ4 ሺሕ በላይ አባወራዎች እንዲነሱ ከተደረገ ስምንት አመታት ተቆጠሩ። በቦታው ከታቀዱ ሶስት ፋብሪካዎች በግንባታ ላይ የሚገኘው አንድ ብቻ ሲሆን ለስኳር የለማ የሸንኮራ አገዳ ተቃጥሏል። ገበሬዎች የተሰጣቸው ምትክ መሬት አመቺ እንዳልሆነ ይናገራሉ

https://p.dw.com/p/3WFpR
Äthiopien Projekt Zuckerfabrik Tana Belese
ጣና በለስ የሸንኮራ አገዳ ማሳ እና የስኳር ፋብሪካምስል Ethiopian Sugar Corporation

ለጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት 19 ሺሕ በላይ ሰው ከመኖሪያ አካባቢው ተነስቷል

ከስምንት አመታት በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት በአማራ ክልል አዊ ዞን ጃዊ ወረዳ ለመገንባት ላቀዳቸው ሶስት የስኳር ፋብሪካዎች የሸንኮራ አገዳ የሚያለማበት መሬት ሲያማትር ማሳቸውን ለመልቀቅ አሻፈረኝ ካሉ ገበሬዎች መካከል ቄስ ተፈራ ሙሉ አንዱ ናቸው። የአርባ አመቱ ገበሬ የአምስት ልጆች አባት ናቸው። ቄስ ተፈራ እንደሚሉት የእርሻ ማሳቸውን ለጣና በለስ የስኳር ልማት ፕሮጀክት ካስረከቡ በኋላ የተሰጣቸው መሬት ከቀያቸው የራቀ፤ ለተጨማሪ ወጪም የዳረጋቸው ነው። ተቃርኖው ግን ከሕይወታቸው መመሳቀል ባሻገር የቀድሞ ማሳቸው ለስኳር ፋብሪካ የሸንኮራ አገዳ እያለማ ሲቃጠል ማየታቸው ጭምር ነው።

«አገዳው በየአመቱ ይቃጠላል። እኛ የምንበላው የለንም። አንድ ሰው ገብቶ አገዳ ሲበላ 50 ብር ይቀጣል። አንድ መንጋ ከብት ቢገባ አምስት ሺሕ ብር ወይም አስር ሺሕ ብር ከፍሎ ነው የገዛ ንብረቱን የሚያስለቅቀው» ይላሉ።

በጃዊ ወረዳ አሉኩራንድ ቀበሌ የሚኖሩት የ5 ልጆች አባት ንጋቱ ዋሴ እንደ ቄስ ተፈራ ሁሉ ከስምንት አመታት በፊት የእርሻ ማሳቸውን ለጣና በለስ የስኳር ልማት አስረክበዋል። «አሁን የተሰጠን መሬት ውኃ ቢደፋበት እንኳ የማያሰምጥ ጭንጫ መሬት ነው። የፊተኛው መሬት ግን ከእኛ ቁመት በላይ የሆነ ዳጉሳ ያመርት ነበር» ሲሉ ንጋቱ ዋሴ ልዩነቱን ያስረዳሉ።

«በበጋ እና በክረምት የምጠቀምበት አንድ ሔክታር መሬት ነበረኝ። የቀድሞ ማሳዬን ከለቀኩ በኋላ የተሰጠኝ መሬት ከሶስት ሔክታር አያልፍም። ግማሹ ገደል እና ድንጋይ ነው። መጀመሪያ ከነበረኝ አንድ ሔክታር ላይ የማገኘው እና አሁን ከሶስቱ ሔክታር መሬት ላይ አርሼ የማገኘው ምርት በምንም አይገናኝም» የሚሉት ሌላው የጃዊ ወረዳ አርሶ አደር ብርሐኑ እንዳላማው ኑሮ ባለፉት ስምንት አመታት ከከፋባቸው መካከል አንዱ ናቸው። «መሠረታዊ ፍላጎታችንን ማሟላት አልቻልንም። ከአምስት ልጄቼ አራቱን አስተምራለሁ። የእነዚህን ልጆች መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት በጣም ከብዶኛል» ሲሉ በሕይወታቸው የተከሰተውን ለውጥ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የጣና በለስ የስኳር ልማት ፕሮጀክት ከስምንት አመታት በፊት በአጠቃላይ በ75 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ የተጀመረ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ወደ 50 ሺሕ ሔክታር የሚሆነው በጃዊ ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ነው። የጃዊ ወረዳ ኮምዩንኬሽን ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሐኑ ንብረት «ወደ 4 ሺሕ 310 አባወራ እና እማወራ፤ በሕዝብ ብዛት ደግሞ ወደ 19 ሺሕ 300 አካባቢ ሕዝብ በዚህ በ50 ሺሕ ሔክታር መሬት ውስጥ የነበረ የማኅበረሰብ ክፍል ነበር» ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

Äthiopien Omo Kuraz Zuckerfabrik
ኦሞ ኩራዝ የስኳር ፋብሪካምስል Ethiopian Sugar Corporation

ውዱ ጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት

የጣና በለስ ዕቅድ እጅግ የተለጠጠ እየተባለ የሚወቀሰው የኢትዮጵያ መንግሥት ግዙፍ የስኳር ልማት ፕሮጀክት አንድ አካል ነበር። ዕቅዱ ከወልቃይት እስከ ኦሞ ሸለቆ፤ ከጃዊ እስከ አፋር በአራቱም የአገሪቱ አቅጣጫዎች አስር የስኳር ፋብሪካዎች የመገንባት ነበር። በጀርመኑ የፍራይቡርግ ዩኒቨርሲቲ አርኖልድቤርግሽትራሰር ማዕከል የፖለቲካል ኤኮኖሚ ተመራማሪው ቤኔዲክት ካምስኪ «በአጠቃላይ የመጀመሪያው የዕድገት እና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በጣም የተለጠጠ ነበር ማለት እችላለሁ። ለስኳር ኢንዱስትሪው ብቻ ሳይሆን ለሌሎቹም ዘርፎች በቁጥር የታቀዱት ግቦች፤ የተቀመጡት ዓላማዎች እጅግ የተለጠጡ ነበሩ። የስኳር ኮርፖሬሽን እና ሌሎች ተቋማት ሹማምንትን ጨምሮ ያነጋገርኳቸው የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች `ይኸ በጣም የተለጠጠ እንደሆነ እናውቃለን ቢሆንም ከፍ ያለ ግብ ማቀድ ጠቃሚ ነው` ሲሉ በግልፅ ነግረውኛል። በስኳር ኢንዱስትሪው የሆነውም ይኸው ነው። ሲሉ ይናገራሉ።

ካምስኪ «በመጀመሪያው የዕድገት እና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተቋቋመው የኢትዮጵያ የስኳር ኮርፖሬሽን የስኳር ፋብሪካዎቹ ግንባታ ዋና ተቋራጭ ከሆነው ብረታ ብረት እና ኢንጂኔሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር በመቀናጀት ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች አንዱ ሆኖ መንግሥት መር የሆነውን የማክሮ ኤኮኖሚ ልማት እንዲያፋጥን ተልዕኮ ተሰጥቶ ነበር» ሲሉ ያስረዳሉ።

ቤኔዲክት ካምስኪ እንደሚሉት ይኸ ዕቅድ ሁለት ምዕራፎች ነበሩት። የመጀመሪያው ምዕራፍ በሥራ ላይ የነበሩ የስኳር ፋብሪካዎችን ማደስ እና የማምረት አቅማቸውን ማሳደግ ሲሆን ሁለተኛው አዳዲስ ፋብሪካዎችን በመገንባት የአገሪቱን ፍላጎት ማሟላት እና የተረፈውን ለዓለም ገበያ ማቅረብ ነበር።

«የመጀመሪያው ዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሐሳቡ ስኳር አምራች በሆኑ አገሮች የታየውን ስኬት በኢትዮጵያ መድገም ነበር። ለምሳሌ የኩራዝን ዕቅድ ብንመለከት በመጀመሪያ አምስት የስኳር ማምረቻ ፋብሪካዎች ለመገንባት እና በ175 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ የሸንኮራ አገዳ ለማልማት ነበር። ይኸ ግዙፍ ነው። በብራዚል እና በካሪቢያን አገሮች ካለው የስኳር ኢንዱስትሪ ጋር ቢነፃጸር እንኳ እንዲህ ትልቅ ከሆነ ፕሮጀክት እምብዛም አይጀመርም። በጥቂት ሺህዎች የሚቆጠር ሔክታር መሬት በማልማት በትንሹ ትጀምርና ከዚያ ታሳድገዋለህ። በዚህ የሆነው ግን እንዲያ አይደለም። በአንድ በኩል የስኳር ኮርፖሬሽን ዘርፉን ለማሳደግ ተቻኮለ። ይኸን ደግሞ የኩራዝ ዕቅድን ስትመለከት ትረዳዋለህ» ሲሉ ግዙፉ የኢትዮጵያ መንግሥት ውጥን ፈተና ይገልጻሉ።

የጥናት ባለሙያው የኢትዮጵያ መንግሥት ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ተቻኮለ ሲሉ አስፈላጊውን የአዋጭነት ጥናት በተገቢው መንገድ አለማከናወኑን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት በዕቅዱ ቢገፋበትም ለስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ እና ለሸንኮራ አገዳ ማምረቻ በተመረጡ አካባቢዎች ግን ቅሬታ መፈጠሩ አልቀረም።

ለምሳሌ በአማራ ክልል አዊ ዞን ጃዊ ወረዳ ለም የእርሻ ማሳቸውን ለስኳር ልማት ፕሮጀክት የመልቀቅ እጣ-ፈንታ የገጠማቸው ገበሬዎች በቀላሉ እጅ እጅ አልሰጡም። ከወረዳ እስከ ክልሉ መንግሥት፤ ከእንባ ጠባቂ ተቋም እስከ ጠቅላይ ምኒስትር ፅህፈት ቤት አቤቱታቸውን አቀረቡ።  አቤቱታ ይዘው እስከ አዲስ አበባ ከተጓዙ ተወካዮች አንዱ የሆኑት ቄስ ተፈራ ሙሉ «መሬት የመንግሥት ነው። እናንተ በመሬት አታዙም፤ የተሰጣችሁን ትክ ተቀብላችሁ ቦታችሁን ለቀቅ ማድረግ እንጂ በመንግሥት መሬት ማዘዝ አትችሉም። እናንተ ጸረ-ልማት ናችሁ» የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

Äthiopien Omo Kuraz III Sugar Factory
ኦሞ ኩራዝ የስኳር ፋብሪካምስል Ethiopian Sugar Corporation

የተሰበረ ቃል

ከወረቀት ባልተሻገረው ኢትዮጵያ መንግሥት ዕቅድ መሠረት ከበለስ ወንዝ የመስኖ ውኃ በመጥለፍ በ75,000 ሔክታር መሬት ላይ ሸንኮራ አገዳ ይለማል፤ሶስት የስኳር ፋብሪካዎችም ይገነባሉ።  እንደውጥኑ ቢሆን ኖሮ ፋብሪካዎቹ 7,620,000 ኩንታል ስኳር፤ 62,481 ሜትር ኪዩብ ኢታኖል እና 135 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጩ ነበር። የአካባቢው አርሶ አደሮችም ከእርሻ ማሳቸው ሲነሱ ኑሯቸውን መሠረተ-ልማት በተሟላላቸው የሰፈራ ማዕከላት ያደርጉ ነበር። እነዚህ ሥራዎች በአጠቃላይ ለ69,000 ዜጎች ሥራ ይፈጥራሉ የሚል ዕምነት የነበረው መንግሥት ለዜጎች የተስፋ ዳቦ ሰጥቷል።

የጃዊ ወረዳ ገበሬዎች ምትክ መሬት ተሰጥቷቸው ከማሳቸው ቢነቀሉም ዛሬም የመንግሥትን የተሰበረ ቃል እያስታወሱ ይብሰለሰላሉ። አቶ ብርሐኑ እንዳላማው «የገባልን ቃል ነበረ። ቃሉን ሳያከብር ነው እኛን አንሸራቶ፤ ወደጎን ገፍቶ ለችግር የዳረገን። በዚህ መስኖ ተፋሰስ ተጠቃሚ ትሆናላችሁ የሚል አንድ ዓላማ ነበረው። ይኸን ጥሎ ነው አሁን እኛን ለችግር የዳረገን» ሲሉ ታጠፈ የሚሉትን የኢትዮጵያ መንግሥት የተስፋ ቃል ይገልጻሉ።

ሥራውን የተረከበው በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሥር የሚገኘው የቀድሞው ብረታ ብረት እና ኢንጂኔሪንግ ኮርፖሬሽን ሶስቱን ፋብሪካዎች ገንብቶ ለማስረከብ የገባው ውል ፈርሶበታል። ከእቅዶቹ መካከል የጣና በለስ ቁጥር ሶስት የስኳር ፋብሪካ ተሰርዟል። የፋብሪካ ግንባታዎቹ በወቅቱ ባለመጠናቀቃቸው እንደእነ ብርሐኑ እንዳላማው እና ንጋቱ ዋሴ ያሉ ገበሬዎች በለቀቁት ማሳ የተመረተ የሸንኮራ አገዳ እንዲቃጠል ሆኗል።

በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ኮምዩንኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጋሻው አይችሉህም «በ13 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ ነበር አገዳ የለማው። ሁለቱ ፋብሪካዎች በ18 ወራት ነበር ይጠናቀቃሉ የተባለው። ውሉ እስኪቋረጥ ድረስ ለአምስት አመታት ነው የቆዩት። አገዳ ደግሞ ተቆርጦ ወደ ፋብሪካ የሚገባበት የራሱ ጊዜ አለው። ስለዚህ በማርጀቱ ምክንያት የተወሰነ ሔክታር ላይ ያለ እንዲወገድ ተደርጓል። ይኸም ኮርፖሬሽኑን ለኪሳራ ዳርጓል» ሲሉ ምክንያቱን ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

Äthiopien Omo Kuraz Zuckerfabrik
ኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካምስል Ethiopian Sugar Corporation

የጣና በለስ ቁጥር አንድ የስኳር ፋብሪካ ግንባታ በቻይና ኩባንያ እየተከናወነ ይገኛል። የጣና በለስ ቁጥር ሁለት እጣ-ፈንታ ግን አልታወቀም። ባለፈው ታኅሳስ ወደ ቦታው ያቀናው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ «ለመስኖ መሬት ውስጥ የሚቀበሩ ከቱርክ በውጭ ምንዛሪ የተገዙ ፕላስቲክነት ያላቸው በጣም ብዙ ቱቦዎች ለፀሐይና ዝናብ ተጋልጠው የሚበላሹበትን ጊዜ እየተጠባበቁ ናቸው» ብሎ ነበር። የግንባታ ግብዓቶቹ በብረታ ብረት እና ኢንጂኔሪንግ ኮርፖሬሽን የተሸመቱ ናቸው የሚሉት አቶ ጋሻው አይችሉህም ለጉዳዩ መፍትሔ ለማበጀት ኮሚቴ መቋቋሙን ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በእጁ የሚገኙ የስኳር ፋብሪካዎችን ለመሸጥ አሊያም በአጋርነት ሊሰራ የሚችል ኩባንያ እያፈላለገ ነው። እስካሁን በነበረው የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ የተፈጠሩ ቴክኒካዊ ስህተቶች መላ ሊበጅላቸው ይችላል የሚሉት ካምስኪ ከማሳቸው የተነሱ ሰዎች ጉዳይ ግን ጥንቃቄ እንደሚያሻው ያሳስባሉ። «የስልጠና መርሐ-ግብሮች፤ ሸንኮራ አምርቶ ለፋብሪካዎቹ የማቅረብ አሰራሮች፤ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሚቀርቡ አገልግሎቶች አሁን ቅድሚያ የሚሰጣቸው ናቸው» የሚሉት ቤኔዲክት ካምስኪ «የአገር ውስጥም ይሁን የውጭ ባለወረቶች የኢትዮጵያ የስኳር ኮርፖሬሽንን ሙሉ በሙሉ የሚተኩ ከሆነ» ይኸ ሊቀየር እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሠ