1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጣና ሐይቅ እና የተደቀኑበት ችግሮች

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 13 2011

በደለል መሞላትና በፍሳሽ ቆሻሻ መመረዝ ሌላኛው በጣና ሐይቅ ላይ የህልውና ሥጋት መሆኑን ነዋሪዎችና ባለሙያዎች እያስጠነቀቁ ነው፣ ጉዳቱን ባፋጣኝ መከላከል ካልተቻለ በአካባቢና በጤና ላይ የደቀነው አደጋ የከፋ መሆኑም እየተነገረ ነው፡፡

https://p.dw.com/p/3705W
Überschwemmungen in Kenia
ምስል picture alliance/AP Photo/A. Kasuku

«በዝናብ አማካይነት ወደ ሀይቁ የሚገባ ማዳበሪያ የሀይቁን ንጥረ ነገር ይዘት ከፍ ማድረጉ ሌላ ችግር ፈጥሯል።»

የተቀናጀ የአካባቢ ጥበቃ ስራና የፍሳሽ ማስወገድ ተግባራት ያለማቋረጥ ሊሰራ እነደሚገባ ደግሞ የአማራ ክልል የአካባቢ፣ የደንና የዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን አሳስቧል፡፡ የፌደራል መንግስት ባለድርሻ አካላትም ከሐይቁ ከመጠቀም ውጪ ለሐይቁ ህልውና የሚያደርጉት ድጋፍ የለም ተብሏል፡፡

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ተንሳፋፊ የእምቦጭ አረም የጣና ሐይቅን በስፋ በመውረሩ የሐይቁ ህልውና ጥያቄ ላይ ወድቋል፡፡ አረሙን ለማጥፋት እየተሰራ ነው ቢባልም የቅንጅትና የቁርጠኝነት እጦት በሐይቁ ላይ የደቀነው ሁሉ አቀፍ ችግር ከጊዜ ወደጊዜ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ የሐይቁን ህልውና የሚፈታተኑ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች እተበራከቱ መጥተዋል፡፡ 

See Tana in Äthiopien
ምስል DW/A. Mekonnen

በስነምህዳርና ብዝሓይወት ዙሪያ ተመራማሪ የሆኑት እና በጣና ሐይቅ ህልውና ዙሪያም በርካታ የምርምር ሥራዎች ያካሄዱት ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ ደለልና የፍሳሽ ቆሻሻ ተፈጥሯዊ የሆነውን የጣና ሐይቅ እየበከለ፣ እንዲሁም፣ ወንዞች ከእርሻ ማሳ ይዘውት የሚመጡት ማዳበሪያ አዘል ደለል በሐይቄ ላይ ሄቪ ሜታል ስለሚፈጥሩ  በሰዎች ላይ የጤና ችግር፤ አጠቃላይ በሀይቁ ብዛ ሕይወት ላይ ደግሞ ጥፋት እየፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል የአካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን የጣና ሐይቅ ስነ ምህዳር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መዝገቡ ዳኘው ተቋማቸው የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች የአካባቢ ችግርን በሚፈታ መልኩ መሰራታቸውን መቆጣጠር መሆኑን ጠቁመው በዚህ ረገድ ከፍተኛ ክፍተቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ ፍሳሽ ወደ ሐይቁ በሚለቁ አካላት ላይ ደግሞ ርምጃ እየወሰደ እንደሆነ ገልጸዋል። ጣናን ለማዳን የአንድ ወገን ጥረት ውጤት አያመጣም ያሉት አቶ መዝገቡ በተላይ የሚመለከታቸው የፌደራል መንግስት አካላት ተሳትፎ የለም ነው ያሉት፡፡

ዓለምነው መኮንን

አርያም ተክሌ