1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዶክተር ዐብይ ከአዉሮጳ

ነጋሽ መሐመድ
ሐሙስ፣ ጥቅምት 22 2011

በስም ያልጠቀሷቸዉ ቡድናት ወይም ግለሰቦች ሐገር ዉስጥ ከገቡ በኋላ ጠመንጃ «በቦቲ» መኪና እየደበቁ ወደ ሐገር ዉስጥ ያስገቡ መኖራቸዉን ተናግረዋል።ጉዳዩን ለመቆጣጠር መንግሥታቸዉ እየተነጋገረበት ነዉ-ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉት።                            

https://p.dw.com/p/37X8H
Frankfurt Ministerpräsident Äthiopien Abiy Ahmed in Commerzbank-Arena
ምስል DW/T. Waldyes

«ኢትዮጵያ የምታምረዉ አንድ ስንሆን ነዉ» ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ

ዉጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን እና ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን (ዲያስፖራ) አንድነቱን ጠብቆ፤ የኢትዮጵያዉያን አንድነት እንዲጠበቅ፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሠላም እና እዉቀት ለማስረፅ እንዲጥር ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ጠየቁ።ጠቅላይ ሚንስትሩ ትናንት ፍራንክፈርት አም ማይን፣ ጀርመን ዉስጥ ከመላዉ አዉሮጳ ለተሰበሰቡ ኢትዮጵያዉያን እና ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን ባደረጉት ንግግር እንዳሉት ኢትዮጵያዊነት እሚያምረዉ ኢትዮጵያዉያን አንድ ሲሆኑ ነዉ።ጠቅላይ ሚንስትሩ የተሰብሳቢሳቢዎቹ «ተወካዮች» ከተባሉ ሰዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች መልስ እና ማብራሪያ ሰጥተዋልም።

 

Compact with africa የተሰኘዉ የበርሊኑ ጉባኤ ዓላማ፤ጊዜ፤ ሥፍራ፤የሒደቱ ቅደም ተከተል እና የመግቢያ ፍቃድ ጉዳይ በአስተናጋጆቹ በጀርመን ባለሥልጣናት እጅ ሥለ ነበር ብዙም አደናጋሪ አልነበረም።የፍራንክፈርቱ ግን፣ በርሊን ላይ በባለ ሙሉ ሥልጣን አምባሳደር፤ ፍራንክፈርት በቆንስላ የሚመሩት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የመሩት የድጋፍ ሥብሰባን ሒደት ቅደም ተከተል ጠጋ ብሎ ላስተዋለ ግን ስብሰባዉ «ማብቃቱ በጀ» የሚያሰኝ ነዉ።ጋዜጠኞች ከስብሰባዉ ሥፍራ በስተቀር ስለ ጉዞዉ፤ ጉብኝት፤ስብሰባዉ፤ሒደት እና ዓላማ፤ ስለተሳታፊዉ ሕዝብ መግቢያ እና መንቀሳቀሺያ፤ ያወቁት ኳስ ሜዳ ከገቡ በኋላ በራሳቸዉ ጥረት እና ጥናት ነዉ።

በድብቅ «ለተመረጡ» ጥቂት መገናኛ ዘዴዎች ባልደረቦች ከተሰጠዉ የእጅ አምባር መሰል ፈቃድ ዉጪ ለአብዛኛዉ ጋዜጠኛ፤ «የሚዲያ መግቢያ» ተብሎ ከኢትዮጵያ ቆስላ የተሰጠዉ የፍቃድ ወረቀት ኳስ ሜዳ ላይ ከመንጎራደድ ዉጪ የጋዜጠኝነትን ሥራ ዋጋ እንደሌለዉ በግልፅ ያወቅነዉ ስታዲዮሙ ዉስጥ ከገባን በኋላ ነዉ።የኃይማኖት አባቶች ትክክለኛ ሥፍራ የተሰጣቸዉ እንኳ የክብር እንግዳዉ በዓሉ ሥፍራ ከደረሱ ወይም ሊደርሱ ጥቂት ሲቀራቸዉ ነበር።

Frankfurt Ministerpräsident Äthiopien Abiy Ahmed  in  Commerzbank-Arena
ምስል DW/Tesfalem Waldyes

የጠቅላይ ሚንስትሩ የንግግር መጀመሪያ እሳቸዉን ብሎ፣ የአዘጋጆችን ዝብርቅርቅ-ትርምሱን መስተንግዶ አልፎ፤ ቁር እየፈደፈደዉ የተሰበሰበዉን ሕዝብ ጭፍግግ ስሜት ገለል፤ቀለል ሳያደርግ አልቀረም።የጠቅላይ ሚንስትሩ ጥቅል መልዕክት ከዚሕ በፊት ከአዲስ አበባ እስከ ዋሽግተን፤ ከአዋሳ እስከ ሚኒያፖሊስ እንዳደረጉት ሁሉ ከዕቅድ፤ድርጊት፤ከተጨባጭእርምጃ ቃል ይልቅ ተስፋ በመስጠት የተሞላ ነዉ።እራሳቸዉም አረጋገጡት።

                            

ጠቅላይ ሚንስትሩ የኢትዮጵያዉያን እና ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን «ተወካዮች» የተባሉ ተሰብሳቢዎች ላቀረቡት በርካታ ጥያቄ ሰፊ መልስ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።መደመር ሥለሚሉት ፖለቲካዊ መርሕ ወይም ፍልስፍናቸዉ በቀለም በተመሰለ ሰፊ ፍልስፍናዊ መግለጫ መልሰዋል።የእግረመንገድ በመሰለ አገላለፅ ሥለ መደመር የደረሱት መፅሐፍ በቅርቡ እንደሚታተም አስታዉቀዋልም።ኢትዮጵያ ዉስጥ በየስፍራዉ የሚደረገዉ የጎሳ ግጭት፤ ግድያ እና መፈናቀል በተለያ አቀራረብ የተለያዩ ተሰብሳቢዎች እያነሱ የሚጥሉት ትልቅ ርዕሥ ነበር።ጠቅላይ ሚንስትሩ ተጠየቁ-መለሱም።

ከዉጪ የገቡ የቀድሞ አማፂ ቡድናት  በተለይም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ታጣቂዎች በየስፍራዉ ሕዝብን ያዉካሉ ሥለመባሉ ለተነሳዉ ጥያቄም ጠቅላይ ሚንስትሩ የቀድሞ አማፂ ቡድናት ከዉጪ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ትጥቅ እንዳልያዙ አረጋግጠዋል።ይሁንና በስም ያልጠቀሷቸዉ ቡድናት ወይም ግለሰቦች ሐገር ዉስጥ ከገቡ በኋላ ጠመንጃ «በቦቲ» መኪና እየደበቁ ወደ ሐገር ዉስጥ ያስገቡ መኖራቸዉን ተናግረዋል።ጉዳዩን ለመቆጣጠር መንግሥታቸዉ እየተነጋገረበት ነዉ-ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉት።

Vorbereitungen Premierminister Abiy Ahmed in Frankfurt
ምስል DW/E. Fekade

ከአንድ ሰዓት በላይ በፈጀዉ መልስ እና ማብራሪያቸዉ ዉጪ የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ ለዉጡን ለመደገፍ ሥለሚጠበቅበት የሰጡት መልስም ያዉ የፖለቲካ መርሐቸዉ ነፀብራቅ ነዉ።ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በቅርቡ አዋሳዉ ላይ በተደረገዉ የኢሕአዴግ ጉባኤ «ሌባን ሌባ እንበለዉ» ሲሉ፣ ዲፕሎማሲያዊ ግድምድሞሽ አገላለጥን ወይም ቃል የማይፈልጉ  ይመስሉ ነበር።ትናንት ፍራንክፈርት ላይ አንድ ያልሆኑትን ተሰብሳቢዎች «አንድ ናችሁ» ማለታቸዉ ግን አንድም ምፀት፤ አለያም ዲፕሎማሲያዊ ሽግላ መሆን አለበት።የፖለቲካ ፓርቲ አርማ እና የኢትዮጵያን ባንዲራ በመያዝ እና አለመያዝ እሁለት ተገምሶ፤ የመቀመጫ ሥፍራ ለይቶ፤ መልዕክት መርጦ ሲደግፍ እና ሲቃወም የነበረዉ ታዳሚ አንድ መሪ ለማየት ለዚያዉ መሪ  ልዩነቱን ለማሳየት መሰብሰበዉ አልሸሸገም።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ለዛሬ በቀጠሮ ያሳደሩት መልስ ነበርም።ዛሬ ሰማነዉ።ግን የተባለለትን ያክል «አስደናቂ» ወይም «ትልቅ» ዜና ነበር?

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ