1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጠ/ሚሩ ምላሽ፤ ምዕራቡ ዓለም አድሏዊ መባሉ፤ መነኩሴዋ የፒያኖዋ ንግሥት

ዓርብ፣ መጋቢት 22 2015

አንዱ የፌስቡክ እድምተኛ ጠቅላያችን ስለ ተባበሩት አረብ ኤምረትስ መሆን አለበት ሚያወሩት እንጂ ስለ ኢትዮጵያ እንዲህ በድፍረት አይሞክሩትም ሲሉ ሌላዉ፤ የሰላም ተምሳሌት የኖቤል ተሸላሚው መሪያችን እንኳን ለኢትዮጵያ ለዓለም የሚተርፍ እውቀት ያላቸዉ እውቀቱንም በተግባር ያሳዩ መሪ ብለዉ አስተያየት ሰጥተዋል።

https://p.dw.com/p/4PZSM
Äthiopien | Premierminister | Abiy Ahmed Ali
ምስል Michel Euler/REUTERS

የመጋቢት 23 ቀን 2015 ዓ.ም የአድማጮች ማህደር ዝግጅት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ መጋቢት 19/2015 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥትን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ለቀረበላቸዉ ጥያቄዎች የሰጡት መልስ፤ አምስቲ ኢንተርናሽናል ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ወዲሕ በሞስኮ ላይ የሚጎርፈዉ ሰብአዊ መብቶች የመጣስ ወቀሳ፣ዉግዘትና ዉንጀላ፣የምዕራቡን ዓለም አድሏዊ አቋም እንደሚያረጋግጥ ማጋለጡ ፤ እንዲሁም ፤ ኢትዮጵያዊትዋ መነኩሲት የፒያኖ ንግሥት ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸዉ፤ በተሰኙ ርዕሶች ስር የተሰጡ አስተያየቶችን ይዘን ቀርበናል።

Uganda | Smartphone Nutzerin in Kampala
የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚምስል ISAAC KASAMANI/AFP/Getty Images

“መንግሥት ኢትዮጵያን ሊያፈርስ ነው መባሉ የዓመቱ ቀልድ ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረዋል።

መጋቢት 19/2015 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥትን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ተናግረዋል። የፓርላማ ተወካዮች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቀርቧቸዉ በርካታ ጥያቄዎች መካከል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታይቶ የነበረው መከፋፈል፣ ጦርነቱ ያስከተለዉ ችግር፣ በግጭቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን ዕጣ ፈንታ፣ ከአማራ ክልል የሚመጡ መንገደኞች ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ የተጣለው ዕግድ፣ እየቀጠለ ያለው የዋጋ ግሽበትና ንረት፣ ማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት፣ የሱዳን ታጣቂዎች ወደ ደቡብ ምዕራብ ክልል ዘልቆ ገብቷል መባሉ፣ ሰላማዊ ዜጎች የሚደርሰው ጥቃት እና ግድያ፣ እንዲሁም በቀጥታ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ያነጣጠረ “ የመፍትሄው አካል ለመሆን ሥልጣንዎትን አይለቁም ወይ?” በሚሉ ጥያቄዎች ላይ ምላሽ ሰጥተዋል። በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከተሰጡ በርካታ አስተያየቶች መካከል፤  

Äthiopien Ministerpräsident Abiy Ahmed Ali
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድምስል Tiksa Negeri/REUTERS

ቀለሙ በዛብህ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ ስልጣን እንጂ የሕዝብ ስቃይ ከማያሳስበው አካል ከዚህ የተሻለ አነጋገር አንጠብቅም ። ጠ/ሚሩ  እንደ መለስ ዜናዊ ብልጥ ለመሆን ቢሞክሩም የሰጡት ምላሽ ግን ራስን የመከላከል እንጂ ከአንድ የሀገር መሪ የማይጠበቅ ያልበሰለ ሰዉ አነጋገር ነበር ። ለምሳሌ በእንግሊዝ እና በሌሎችም ሀገራት ውስጥ መሪዎች ሀገራዊ ኃላፊነት ከአቅማቸው በላይ በሆነ ጊዜ ስልጣን በቃኝ ብለው ሲለቁ አይተናል ። ግን እንግሊዝ ውስጥ ያሉ ባለስልጣናትን ሁላችንም እንልቀቅ ማለታቸውን አልሰማንም ሲሉ ጽፈዋል።

አቢይ እንደ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ስልጣን በመልቀቅ የኢትዮጵያ ችግር የመፍትሄ አካል እንዲሆን በአቶ ክርስቲያን ታደለ መጠየቁን ለምን አልዘገባችሁም? መቼ ይሆን ከገደል ማሚቶነት የምትላቀቁት ያሉት ደግሞ ይነጋል በላቸዉ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ናቸዉ።

እዉነት ከጠቅላይ ሚኒስትራችን አንደበት የሰማሁት ቃላቶች እንደ አንድ በሪ ለህዝብ ሊያደርስ የሚገባዉ መልዕክት ነዉ። በመሪነቱ ኮራሁ፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን የፃፉት ደግሞ በቀለ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ናቸዉ። 

የዓባይን ልጅ ውሀ ጠማው የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ በአስተያየታቸዉ፤ ወይ ጉድ ሲሉ ይጀምራሉ። ወይ ጉድ እንደዚህ አይነት ጉድን ማን ሰምቶ ያውቃል? ሰው የሚበላው አጦ ኢኮኖሚያችን አድጓል ይባላል እንዴ?  ምናልባት የባለስልጣኖች ኪስ ሊያድግ ይችላል። በመንግስት ድጋፍ የሚፈናቀሉ ህዝቦች ቁጥርም ሊያድግ ይችላል። ኢኮኖሚ ግን አላደገም ብለዋል።

ዮሴፍ አዱኛ ይማም የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ በአስተያየታቸዉ፤ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በእኩል ተሳትፎ የሚኖሩባት ሃገር ለመፍጠር የመደመር መንገድ ፍቱን ነው። ወንድማማችነት! ብለዋል። 

ሃብታሙ ሙለታ አሰፋ የተባሉ ሌላዉ የፌስቡክ እድምተኛ ጠቅላያችን ስለ ተባበሩት አረብ ኤምረትስ መሆን አለበት ሚያወሩት እንጂ ስለ ኢትዮጵያ እንዲህ በድፍረት አይሞክሩትም ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል። 

የሰላም ተምሳሌት የኖቤል ተሸላሚው መሪያችን እንኳን ለኢትዮጵያ ለዓለም የሚተርፍ እውቀት ያለው እውቀቱንም በተግባር ያሳየ መሪ አብይ ነዉ ሲሉ አስተያየታቸዉን በማህበራዊ ሚዲያ ያስቀመጡት ኦሮምያ ኢንሳይደር የሚል ስም ያላቸዉ የፌስክ ተጠቃሚ ናቸዉ።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለፈው 2022 በዓለም ላይ ከተከሰቱት ግጭቶች ሁሉ እጅግ አውዳሚው የትግራዩ ጦርነት እንደነበር በዚሁ ሳምንት ባወጣው ሪፖርቱ ገልጿል። ድርጅቱ፣ በኢትዮጵያው ጦርነት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተፈጸሙት ከዓለማቀፉ ኅብረተሰብ ትኩረት ውጭ እንደኾነ በሪፖርቱ ጠቅሷል። ዓለማቀፍ ድርጅቶች፣ በኢትዮጵያ፣ የመን፣ በርማ እና አፍጋኒስታን ለነበሩ ግጭቶችና ሰብዓዊ ቀውሶች በቂ ምላሽ አልሰጡም በማለትም አምነስቲ ወቅሷል።

Logo amnesty international
አምነስቲ ኢንተርናሽናል

ይትሳደዉ ፀጋዬ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ ያሳዝናል ሲሉ ይጀምራሉ አስተያየታቸዉን። ያሳዝናል አየህ ምዕራባውያን ስለመብት ሳይሆን ስለ እራሳቸው ጥቅም እንጂ ስለ ሰብዓዊነት ግድ ብሏቸው የሚያውቁበት የታሪክ አጋጣሚ የለም። ዓለም በነሱ እጅ አሁንም እየተናጠች ትገኛለች ብለዋል።

ፍስሃ ተወልደ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ በበኩላቸዉ፤ የአሜሪካ እና የእንግሊዝ ሴራ በደንብ ተጋልጧል። እውነት ማለት ይኸ ነው ሲሉ የዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት ዘገባ አወድሰዋል። ኢትዮጵያ ትቅደም የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይም፤ ዩክሬን አሜሪካ የምታዋጣት መስሏት ነበር። እሷ የምትታወቀው አገር በማፈራረስ ነው። ፑቲን እንደ ኢትዮጵያ መንግስት ብሄር ላይ ያተኮረ አይደለም። አሁን ገና በገሀዱ ዓለም ላይ እውነት ሰማሁ ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።

ለዲሞክራሲ የቆመ መንግስት በዓለም ላይ የለም ሲሉ በፊስ ቡክ ላይ አስተያየታቸዉን የጀመሩት ሳሚ ያለዉ ካሳ ናቸዉ። ለዲሞክራሲ የቆመ መንግስት በዓለም ላይ የለም ። ሁሉም ለጥቅሙ ነው፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ጽፈዋል።

በድንቅ የፒያኖ የሙዚቃ ሥራዎቻቸው የሚታወቁት እማሆይ ጽጌማርያም ገብሩ ማረፋቸዉ የተሰማዉ በዚሁ ሰሞን ነዉ። እማሆይ ጽጌማርያም በምንኩስና ወደ መንፈሳዊው ሕይወት ከመግባታቸው በፊት የሚታወቁት የውብዳር በሚል ስማቸዉ ነበር። በ1916 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተወለዱ እማሆይ ጽጌማርያም ገብሩ በኢትዮጵያ በቫዮሊን እና በፒያኖ ሙዚቃዎችን በማቀናበር በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው። የፒያኖዋ ንግሥት እማሆይ ጽጌማርያም ገብሩ፣ የሙዚቃ ሥራዎቻቸው በኢትዮጵያውያን እና በሌላዉ ክፍለ ዓለም ዘንድ ተወዳጅ እና ተደማጭ ለመሆን ችሏል። ምዕራባዉያን ጋዜጦች የብሉዝ ሙዚቃን በፒያኖ ያቀናበሩት መነኩሴ ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል። እማሆይ ጽጌማርያም ከ 40 ዓመታት በፊት ደግሞ ወደ እስራኤል በመሄድ እየሩሳሌም ውስጥ ገዳማት ዉስጥ ሲኖሩ ቆይተው በ99 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በድካም በሞት መለየታቸዉ ተዘግቧል።

አዴል አበበ የተባሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ በአስተያየታቸዉ በጣም ነበር የምወዳቸው። ሙዚቃቸው ነብስ ውስጥ ድረስ ዘልቆ የሚሰማ እጅግ ልዩ የነብስ ምግብ ነው ።  ከዚህ ዓለም ድካም በማረፋቸው አዝኛለው። ነብሳቸው በአፀደ ገነት ታርፍ ዘንድ ምኞቴ ነው።

የአበበ ልጅ የተባሉ የፊስቡክ ተከታታይ፤ እንደኔ የራሳቸው የጣት አሻራ ያረፈበት ፒያኖ እራሱ መቶ ለያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ቢሰጥ ከታሪካዊነቱ የተነሳ ጥሩ ነው። ይህን እስራኤል ሀገር ያለው ኢንባሲ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያ ጉምሩክ፤ የቅርስ ባለአደራ የባህል ሚንስቴር፤ ትብብር ቢያደርጉ ጥሩ ነው። ትልቅ ቅርስ ነው። ይህን ሀሳብ ለቤተስባቸው አድርሱልኝ።  እስራኤል ያሉ ኢትዮጵያዉያንም ይተባበራሉ።  እማሆይ ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልን። ነፍስ ይማር! ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።

Äthiopien Emahoy Tsege Maryam Gebrue
እማሆይ ጽጌማርያም ገብሩምስል Mahlet Fasil/DW

ቴዮድሮስ ኃይለማርያም የተባሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ በበኩላቸዉ፤ የእህታቸው ልጅ መጨረሻ ላይ ስለፒያኖው ስትናገር ወደ ሀገር ለመውሰድ ውድነው ብላለች። ግን ይህን ሸጦ ሌላ ፒያኖ መግዛቱ ተገቢ አይደለም። ይሄ ኑዛዜንም መሻር ነው። ታሪኩንም ለሌላ ሰው ወይም ሀገር አሳልፎ መስጠት ነው። ካስፈለገ ፒያኖውን ለማስጫን የሚጠይቀውን ወጭ በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያዉያን ይተባበሩ እንጂ ከተሸጠ ታሪኩም አብሮ መሸጡ ነው፤ ሲሉ ያላቸዉን ሃሳብ አስተያየት አስቀምጠዋል።

በኢብራይስጥ ቋንቋ ስማቸዉን ያስቀመጡት አንድ የፌስቡክ ተጠቃሚ በበኩላቸዉ፤ የኔ እናት ሰብስሽን በአብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብ አጠገብ ያስቀምጥልን። እድሉን አግኝቼ በቀብሮ እለት በመገኘቴ ተመስገን።  አንድ እንቁ እናት ማጣታችን ልብ ሰባሪ ነው፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ጽፈዋል።

ዮኃንስ መጥምቁ የተባሉ ሌላዉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ፤ ፒያኖ መመማር ለምንፈልግ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ እንኳን ትምህርት ቤት የለም ሲሉ አስተያየት ጽፈዋል። ግን እዉነት የለምን። ዮኃንስ መጥምቁ እስቲ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤትን ይጠይቁ። አንድ እንኳ አይጠፋም የሚል አስተያየት አለን።

ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ

አዜብ ታደሰ

ዮኃንስ ገብረግዚአብሔር