1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ነሐሴ 22 2012

ከሰሞኑ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርካቶች ከተቀባበሏቸው እና የብዙዎችን ትኩረት ስቦ የነበረው የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ለይፋዊ የአንድ ቀን ጉብኝት ወደ ሱዳን ያቀኑበት እና ጉብኝታቸው ከዩናይትድስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፔዎ ጋር መገጣጠሙ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር።

https://p.dw.com/p/3hdZ1
Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ከሰሞኑ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርካቶች ከተቀባበሏቸው እና የብዙዎችን ትኩረት ስቦ የነበረው የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ለይፋዊ የአንድ ቀን ጉብኝት ወደ ሱዳን ያቀኑበት እና ጉብኝታቸው ከዩናይትድስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፔዎ ጋር መገጣጠሙ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሶስት አዳዲስ መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን ይፋ አድርጓል። ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት ከባንክ ውጪ ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ማከማቸት የሚከለክለውን ጨምሮ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ወደ ባንክ እንዲያድጉ እና የግል ባንኮች ከዓለማቀፍ የገንዘብ ተቋማት በውጭ ምንዛሪ እንዲበደሩ የሚፈቅዱ መመሪያዎች ናቸው ተግባራዊ የተደረጉት። የዘርፉ ባለሞያዎች ብርቱ ጥያቄ የማንሳታቸውን ያህል በርካቶች በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ወደ ሁለት ጫፍ የሚለጠጡ ሃሳቦችን አንሸራሽረውበታል። የኢትዮጵያ ትምሕርት ሚኒስቴር ደግሞ የ2013 ዓ/ም የትምሕርት ዘመን ለመጀመር የተማሪዎች ምዝገባ እደሚጀመር አስታውቋል። ጤና ይስጥልኝ አድማጮች  በሶስት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው የዕለቱ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ዝግጅታችን ተጀምሯል ። ከዕለቱ መሰናዶ ጋር ታምራት ዲንሳ ነኝ መልካም ቆይታ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ባለለፈው ማክሰኞ ወደ ካርቱም አቅንተው ከጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሃምዶክ እና ከሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሌትናንት ጄኔራል አብዱል ፋታህ አልቡርሃን ጋር መነጋገራቸው ተዘግቧል።ጠቅላይ ሚንስትሩ በቆይታቸው በተለይ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል እና ልቀት ላይ ሲደረጉ በነበሩ የድርድር ሂደቶች ላይ ማተኮራቸውም ተነግሯል። በቀጣይ ድርድሩን በተመለከተ የሚነሱ ቅሬታዎችን በውይይት ብቻ መፍታት እንደሚገባ መስማማታቸው ተነግሯል። ነገር ግን የጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ ሱዳን ማምራት በዚሁ ዕለት ሱዳንን ከጎበኙት የዩናይትድስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፔዎ ጋር መገጣጠሙ ለምን ይሆን ? የሚል ጥያቄ በበርካቶች ዘንድ አስነስቷል። ብዙዎችም በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አማካኝነት ሃሳባቸውን አጋርተውበታል። ምንም እንኳ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሚስተር ፖምፔዎ ጋር ስለመገናኘታቸው የተባለ ነገር ባይኖርም።

ጃገማ አበበ የተባሉ አስተያየት ሰጪ «ጉብኝቱ እንደተባለው ባጋጣሚ ሳይሆን ታስቦበት የተደረገ  ነው።»ብለዋል። መብቱ  ወርቁ የተባሉ አስተያየት ሰጭ ደግሞ የሱዳንና የኢትዮጵያ ወዳጅነት መጠንከር መተሳሰር ያለበት የሁለቱን ሀገሮችየሚርብሹ የሀገሪቱን ሠላም የነሱሽብር ፈጣሪዎችን ለአንዴና ለመጨረሻ ለማጥፋት ነው መሆን ያለበት ።ይህ ነው ትልቁ ስራቸዉ መሆን ያለበት። ሠላም ከሌለ ልማት የለም በሱዳን በኩል እየተላኩ በሱዳን ምድር እየሰለጠኑ  መሳሪያ እየተቀበሉ ነው ኢትዮጵያን የሚወጉ። ሲሉ አባዲ ወልደ ገብርኤል ምስግና የተባሉ ደግሞ «መጃጃል ምንም አያስፈልግም ስለዚህ ሁሌ ሁለንተናዊ ዝግጅት ያስፈልጋል ።በንግግራቸው  እና በድርጊታቸው የተለያዩ  እንዳይሆን  ቀርቦ ማናገሩ ተገቢ መስሎ ነው የሚታየኝ ።ያለምንም ስጋት ሁለንተናዊ ስብእና ሊኖረን ይገባል ። ከትናንትናው የማስፈራራት አካሄዳቸው ልናነባቸው ይገባል ምክንያቱም  አስረስተው ወይም አስተኝተው እንዲያዘናጉን መፍቀድ የለብንም። ስለዚህ ግድቡ  እስከታቀደለት ከፍታ  እስኪሞላ ድረስ እንዲህ ቀርበው መያዙ ተገቢ ነው የሚመስለኝ ...ከዚያ በኋላ ለራሳቸው ሲሉ ደህንነቱን ይከታተሉታል።»ብለዋል። ቴዎድሮስ አለም ባሰፈሩት አስተያየታቸው «ለመሆኑ በግልጽ ለመወያየት የሚበቃ ጊዜ ነበራቸው ወይ?»  ሲሉ ጠይቀዋል። በዳሳ ገመዳ «የቤትህን እሳት ማጥፋት ከሁሉ ነገር ይቀድማል ። ዲፕሎማሲ ከውጭ ወደ ውስጥ ሳይሆን ከውስጥ ወደ ውጭ ሲሆን ነው አሸናፊ የሚሆነው »ብለዋል። ሰው ሉሉ የተባሉ አስተያየት ሰጭ ደግሞ የጠቅላይ ሚንስትሩን ጉብኝት ተስፋ እንዳሳደረባቸው የሚገልጽ አባባል ተጠቅመው እንዲህ ብለዋል።«  ትልቅ ህልም ትንሽ አእምሮ ላለው ሰው አይነገርም፡፡ ጎበዝ ገበሬ አረም ባለበት ዘሩን አይተክልም ። ዶክተር መራመድዎትን ይቀጥሉ» ብለዋል። ስለ ሀገሬ በሚል ስም የሰፈረ አስተያየት ደግሞ « ይህቺ የአብይ ጉብኝት ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ጋር ምን ግንኙነት ይኖራት ይሆን  ? መልዕክት ለመቀበል ወይስ ጉብኝት ይሆን ? »ሲሉ ጥያቄአዊ አስተያየታቸውን አስፍረዋል።

Äthiopien | Nobelpreis | Premierminister Abiy Ahmed Ali
ምስል Getty Images/AFP/F. Varfjell

ሰሞኑን በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆነው ከሰነበቱ ጉዳዮች አንደኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሶስት አዳዲስ መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረጉ መጀመሩ ነው። ይኸውም ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት ከባንክ ውጪ ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ማከማቸት የሚከለክል፤ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ወደ ባንክ ማደግ እንዲችሉ የሚፈቅድ እና የግል ባንኮች ከዓለማቀፍ የገንዘብ ተቋማት በውጭ ምንዛሪ እንዲበደሩ የሚያስችሉ መመሪያዎችን ነው ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው። ብሔራዊ ባንክ በዚህ ክልልከላ እና ፈቃድ የታከለበት አዲሱ መመሪያ ሀገሪቱ ከምትመራበት የኢኮኖሚ ፖሊሲ እና ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር በሁለት መልኩ የተቃኙ አስተያየቶችን አስተናግዷል።

ናቡቴ ይመር የተባሉ አስተያየት ሰጭ  «እንግዲህ ይህ የግራ ዘመም ፖለቲካ አራማጆች ሥልጣን ከያዙ 30 ዓመት ሆነ መመሪያቸውም " አብዮታዊ ዲሞክራሲ" ነበር። የአልባኒያና ኮምኒዝም። አሁን ዞር አሉና ተረኞቹ "ብልጥግና " ስም ብቻ ነው የተቀየረው። ቀስ እያለ ይኸው አዲስ ዜና ሰማን! የግል ሀብት መገደብ ።።ሶሻሊዝም "አፈር በጋጠ ሰላሳ ዓመት" ምን እየሆነ እንደመጣ ግልጽ ሆነልን።» በማለት አስተያየታቸውን አስፍረዋል። የሀገሬ ሰው ደጉ በሚል ስም ሃሳባቸውን ያሰፈሩ ሰው ደግሞእና ብድር መበደር ከወለዱ እዳ መቆለል በስተቀር ትርፉ ምንድን ነው ?ዘጠኝ ገዝቶ ፡ ዘጠኝ ቢሸጡ ! ትርፉ ምንድን ነው ? ዘጥዘጡ !!ኧረ ለመሆኑ ?የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን የሚያቃልለው ፡ በስፋት የውጭ አገር ገንዘብ በብድር በማስገባት ነውን ?ብር እኮ ነግዶ ትርፍ ካላስገኜ የቻይና አርቴፊሺያል ሸቀጥ እንደ ማለት ነው ! የወጭ እና የገቢ ባላንሳችሁን ጠንቅቃችሁ ፈትሹ !የኢትዮጵያውን ገንዘብ ቀይሩት እሱ በየ ግለሰቡ ሳንዱቅ ውስጥ መሽጎ አገሪቱን ሰላም ያሳጣትን ቁልፍ ጉዳይ ትቀርፉበታላችሁ ! ቀሪውን አብረን እናያለን።»ብለዋል።

ከድር ይመር የተባሉ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸው «ከዚህ ይቅል መጀመሪያ የገቢ ወጭ ንግዱ ላይ ቁጥጥር ማድረግ ተገቢ ነው። ትልልቅ ካፒታል ከሚያንቀሳቅሱ አስመጪ እና ላኪዎች ጀምሮ እስከ ትንንሽ ተመላላሽ ነጋዴዎች በጉምሩክ ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል ። አንድ ነጋዴ የአንድ ሺ ዶላር እቃ ይዞ ወደ አገር ሲገባ ከንግድ ባንክ የገዛውን ዶላር ወይም ያስተላለፈበትን የባንክ ደረሰኝ ሲያቀርብ ፦ ጉሩክ እና ንግድ ባንክን የሚያገናኝ የኮምፒተር መረብ በመዘርጋት እቃው የሚገዛበትን ዋጋ እና ከባንክ የቀየረው ወይም ያስተላለፈው የዶላር መጠን ተሰልቶ እቃውን ጉምሩክ የሚጠበቅበትን ቀረጥ አስከፍሎ እንዲገባ መፍቀድ ይገባል።  ከዚህ የተለየ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ከሆነ ከቅጣት እስከ ውርስ የሚያደርግ ህግ ማውጣት ነው። እኔ እንደምረዳው አገሪቱን የጎዳት ከትንሽ እስከ ትልቅ ነጋዴወች የሚደረግ የህገወጥ ገንዘብ ዝውውር ነው።» የሚል ሃሳብ አስፍረዋል።

ያረጋል ኤን ኬ በሚል ስም አስተያየታቸውን ያሰፈሩ ሰዉ ደግሞ «የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያደረገ ያለው የማሻሻያ እርምጃ መልካም ነው በተለይ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ላይ በጎ እመርታ ማምጣት ያስችለዋል» በማለት አስተያየታቸውን እንዲሁ በደፈናው አኑረዋል። ግርማይ በላይ ደግሞ « ይኼ ማለት ባንኩ በሚወስደው እርምጃ በመጨረሻ የሃገሪቱ ውድቀት ይከሰታል። የውጭ ምንዛሬ እጦት በብድር መሸፈን ማለት ያለ ኣግባብ በብር ግሽበት ያልታሰበ የዋጋ ንረት ያስከትላል። የድሃን የመኖር መብት ይጋፋል። ሃገሪትዋ ለውጭ ባለፀጎች ሲሳይ ትሆናለች፤ የኢኮኖሚ እና የሃገር ሉዓላዊነትም ጫወታው ያበቃል ማለት ነው» ብለዋል። ያምራል ሀገሬ በሚል ስም ሃሳባቸውን ያሰፈሩ ሰው ደግሞ «ዋናው ጉዳይ መሆን ያለበት በትይዩ ገበያ ወይም በጥቁር ገበያ እና በባንክ መካከል ያለው ልዩነት እንዲሁም ወደ አገር በሚገባውና ወደ ውጪ በሚላከው መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ ነው

በእነዚህ መካከል ልዩነቱ የሰፋበት ዋነኛ ምክንያት ወደ ውጪ የሚላከው ምርት ስላላደገ መሆኑን ዶ/ር አለማየሁ የተባሉ ሰው ሀሳብ ጨምረው ጽፈዋል።  "በእኔ ስሌት ወደ አገር በሚገባውና ከውቺ በሚመጣው መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ወደ ውጪ የምንልካቸው ምርቶች በአማካይ በዓመት 20 በመቶ ለስምንት ተከታታይ ዓመት ማደግ ይኖርበታል" ።ስለዚህም የመንግሥት ትኩረት መሆን ያለበት "ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶች የሚጨምሩበትን መንገድና ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት አምራቾችን ማበረታት ላይ ነው"  የሚል ሃሳብ አስፍረዋል።

የኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስቴር የአዲሱ የ2013 የትምህርት ዘመን ምዝገባ ከትናንት በስትያ ማክሰኞ    ነሐሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በመንግሥት እና በግል ትምህርት ቤቶች እንደሚጀመር አስታውቋል። ሚኒስቴሩ እንዳለው ትምህርት ቤቶች የኮሮና ተሕዋሲ መከላከያ መንገዶችን በመተግበር ምዝገባ እንዲያከናውኑ ተፈቅዷል ። ምንም እንኳ በሀገሪቱ የበሽታው ሁኔታ እየተስፋፋ ቢሆንም የትምህርት ዝግጅት እና እንቅስቃሴ መጀመር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱን ምዝገባው መጀመሩንም ይፋ አድርጓል።

በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የኮሮና ተሕዋሲ  ባለፈው መጋቢት ወር መከሰቱን ተከትሎ ወረርሽኙን ለመግታት ሲባል ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ቆይተዋል። አሁን ከኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በተህዋሲው የተያዙ ሰዎች ከ46,000 በላይ ሲደርሱ ፤ ከኮሮና ጋር በተያያዘ ደግሞ 745 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ታዲያ የሰሞኑ የትምህርት ሚኒስቴር የተማሪዎች ወደ ትምህርት እንዲመለሱ ምዝገባ መጀመሩ እንዴታነት በርካቶች ሃሳባቸውን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እንዲያጋሩ አድርጓቸዋል።

አማረ ተሾመ ባሰፈሩት ሃሳብ «ትምህርቱን መጀመር አጠያያቂ ሊሆን አይችልም። ነገር ግን ሁሉንም ተማሪዎች ማስክ እንዲያደርጉ በማድረግ ማስተማር አይቻልም። ምክንያቱም ወደታች ክፍል ያሉ ህፃናት ተማሪዎች ማስክን እንዲጠቀሙ ቢደረግ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን የአለም ጤና ድርጅት ሰሞኑን ሲያሳውቅ ቆይቷል። ለነዚህ ህፃናት ተማሪዎች ምን የታሰበ ነገር እንዳለ ቢገለፅ መልካም ነው።» ብለዋል።

Äthiopien Addis Abeba | Nationalbank
ምስል DW/H. Melesse

ፈትለወርቅ ተፈሪ ባሰፈሩት አስተያየታቸው « ኢትዮጵያ ከተቀረው ዓለም አንጻር ወረርሽኙን የተቆጣጠረችበት መንገድ የተሻለ ነው። አሁን እየታዩ ያሉ ችግሮች እንዳይባባሱ በማድረግ ማስቀጠል ይቻላል » ብለዋል።

ዳግማዊ ሰኢድ አሊ የተባሉ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸው «ህዝብ ለመጨረስ ካልሆነ በቀር በሽታው እየጨመረ ትምህርት ይከፈት ማለት ምን ማለት ነው? ኮሮና ኢትዮጵያ ውስጥ ገባ ሲባል ተሽቀዳድማችሁ ዘጋችሁ፡፡ በኮሮና የተያዘው 40000 ከደረሰ በኋላ ትምህርት ቤት መክፈት ማለት ለእኔ ሌላ ነገር አለው፡፡ በዕቅዱ መሰረት በሽታው አልሄደላችሁም።28 ሚሊዬን ይደርሳል የተባለው 40000 ላይ ተቀመጠባችሁ። አንድ መምህር ወይም ተማሪ በበሽታው ተይዞ ቢገባ ስንት ተማሪ ተቀብሎ ወደቤተሰብ እንደሚቀላቀል አስባችሁታል፡ እውነት በየትኛው ክፍል ውስጥ ነው ተገቢው ጥንቃቄ ተደርጎ ትምህርት ይጀመራል የምትሉት፡፡ 50 እና 60 ተማሪ ታጭቆ በሚማርበት ክፍል ውስጥ፣ ተዛዝሎ በሚሄድ ተማሪ ምን አይነት ጥንቃቄ ሊደረግ ነው፡፡ » ብለዋል

ጌዲዎን የዘላለም ግርማ ደግሞ «ከበሽታው በላይ ልጆች ከትምህርት በመራቃቸው ለከፍተኛ ድብርትና ጭንቀት እየተጋለጡ ስለሆነ ትምህርት ማስጀመሩ የግድ ነዉ ደግሞስ በየትኛው ሞራል ነው ከዓለም የምንለየው » ሲሉ ጥያቄአዊ አስተያየታቸውን አስፍረዋል። አጉማስ ፈቃዱም « ልጆች ወደ ት/ቤት ባለመሄዳቸው በኢኮኖሚና በማህበራዊ መስተጋብር ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጥሯል ይሁን እንጂ ከተከበረው የሰውልጅ ህይወት አይበልጥም ።ስለሆነም የነ ቶሎ ቶሎ ቤት እንዳይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረግበት። ጉዳዬ የሰው ህይወት ነውና ከህሊናም ከታሪክም ተወቃሽ እንዳንሆን ።አይደለም ህጻናት አዋቂዎች እንኳ የወጣውን የአገሪቱን ህግ አላከብር ብለው ከፓሊስ ጋር የአይጥና ድመት ጫወታ ሲጫወቱ እያየን ነው።የአገራችን የክፍል መጠን፥የተማሪዎች ንቃተ ህሊና፥የትራንስፖርት ችግር በአጠቃላይ ለበሽታው የሚደረገው ጥንቃቄ ምን ያህል አስተማማኝ ነው ሚለው   ወሳኝ ነገር ነው።የህብረተሰቡን አስተያየት ተደራሽ ያአደረገ ህዝባዊ ውይይት በመገናኛ ብዙሃን ብታደርጉ ሸክማችሁን በተወሰነ መልኩ ትቀንሳላችሁ ።ሀላፊነቱ የሁሉም ቢሆንም ውሳኔ ሰጪዎች ስለሆናችሁ የእናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ እንዳይሆን ሰከን ያለ ሞያዊና በጥናት የተደገፈ መፍትሄ አዘልም መሆን አለበት።» በማለት ሃሳባቸውን አካፍለዋል። እንግዲህ አድማጮች የዕለቱ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ዝግጅታችንም ይኸንኑ ይመስል ነበር ለአብሮነታችሁ ምስጋናችን ይድረሳችሁ ። ታምራት ዲንሳ ነኝ ጤና ይስጥልኝ።

ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ