1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጠ/ሚ ዐቢይ የምክር ቤት ንግግር

ማክሰኞ፣ መጋቢት 19 2015

ለጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ከ25 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ካቀረቧቸው ዋና ዋና ጥያቄዎች መካከል፦ መንግሥት በሕዝብ ላይ ክህደት ፈጽሟል፣ ይልቁንም ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሠራ ይገኛል የሚል ቅሬታ አለና መንግሥት ያንን እያደረገ ነው ወይ? የሚልም ይገኝበት ነበር ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን «የዓመቱ ቀልድ» ብለውታል ።

https://p.dw.com/p/4POXU
Äthiopien, Addis Abeba | Äthiopisches Parlament
ምስል Solomon Muchie/DW

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን «የዓመቱ ቀልድ» ብለውታል

ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ 25 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ካቀረቧቸው ዋና ዋና ጥያቄዎች መካከል ሰላምና መረጋጋትን ፣ ፀጥታን እና ደህንነትን የተመለከቱት ጎላ ያሉት ናቸው ። በኦሮሚያ ክልል ከታጣቂዎች ጋር በሚካሄድ ግጭት የበርካታ ሰዎች ሕይወት እና ንብረት ውድመት መቼ በሰላም ተፈትቶ ይቆማል? የሚል ጥያቄም ተነስቷል ። መንግሥት በሕዝብ ላይ ክህደት ፈጽሟል፣ ይልቁንም ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሠራ ይገኛል የሚል ቅሬታ አለና መንግሥት ያንን እያደረገ ነው ወይ? የሚል ጥያቄም ቀርቦ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን «የዓመቱ ቀልድ» ብለውታል ። 

ሕገ ወጥ ታጣቂ ኃይሎች የጦር መሣሪያ ወደ አዲስ አበባ በማስገባት ከተማውን ለመበጥበጥ እና ለማወክ እየተደረገ ያለ ጥረት መኖሩ ተገልጾ ያንን መንግስት እንዴት ሊመክተው ነው የሚል ጥያቄም ቀርቧል።  ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ የተሻለ ሰላም መኖሩን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ «የኢትዮጵያ የመፍረስ ስጋት አልፏል» በማለት ሰላም ከጦርነት ጊዜ መሰባሰብ ባልተናነሰ ከፍተኛ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን ገልጠዋል ።  መንግሥታቸው የተሟላ ሰላም ለማምጣት እየተጓዘ መሆኑንምአብራርተዋል። በሌላ በኩል፦ በኦሮሞ እና አማራ ክልሎች የብልጽግና መዋቅሮች መካከል ከመካረር ያለፈ በተለያየ ጎራ የመቆም ችግር መኖሩ፤ ዜጎች ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ የመከልከል፣ የመታገት፣ የመገደል ፣ የመዘረፍ ችግር እንዲከሰት ማድረጉ እንዲቆም ተጠይቋል። 

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውጫዊ ገጽታ
የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውጫዊ ገጽታምስል Solomon Muchie/DW

ወደ አዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ ፍልሰት ከመኖሩ ባሻገር መንግሥት ለመገልበጥ ያለመ እንቅስቃሴ ጭምር በመኖሩ ያንን ለመከላከል የተሠራ ሥራ እንዳለ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አላግባብ የሚፈፀሙ ማጉላላቶች እንዲቆሙና በሁለቱ ክልሎች አመራሮች መካከል የሚታየው መገፋፋት ሁሉንም የሚጎዳ በመሆኑ እንዲቆም አሳስበዋል። 
ከውጭ ግንኙነት አንፃር ጎረቤት ሱዳን ለሦስት ዓመታትና በላይ በመተማ በኩል የኢትዮጵያን ድንበር ወርሮ መያዙ ፣ ደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች እና አርብቶ አደሮች እንዲሁም ወታደሮች ድንበር ጥሰው በመግባት የተቆጣጠሩትን መሬት እንዲለቁ መንግሥት እንዲሰራ ተጠይቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ችግሮቹን ከሁለቱ ሀገራት መንግሥታት ጋር በንግግር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

መንግሥት በሕዝብ ላይ ክህደት ፈጽሟል፣ ይልቁንም ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራ ይገኛል የሚል ቅሬታ አለና መንግሥት ያንን እያደረገ ነው ወይ? የሚል ጥያቄም ቀርቦ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን «የዓመቱ ቀልድ» ብለውታል።

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጣዊ ገጽታ፦ ፎቶ ከማኅደር
የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጣዊ ገጽታ፦ ፎቶ ከማኅደርምስል Solomon Muchie/DW

መነሻው ጨለምተኝነት ያመጣው ጩኸት መሆኑንም ገልፀዋል። "አሁን ላይ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የዜጎች ደህንነትና የአገር ሉዓላዊነት ዋነኛ ሥጋት ምንጭ መንግሥት ነው። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት በብልጽግና መንግሥት እየተናደ ነው ስለሆነም ሥልጣን በመልቀቅ የመፍትሔው አካል ለመሆን አላሰቡም ወይ"? የሚል ጥያቄም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቀርቦላቸው ነበር። ሌሎች የኢኮኖሚ ጥያቄዎችም በዛሬው ጉባኤ በስፋት ቀርበዋል። የኑሮ ውድነት መናር ፣ የፍትሓዊ ትጠቃሚነት እና ሌሎች የልማት ጥያቄዎችም ቀርበው ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

እዳ፣ የዋጋ ንረት፣ የመሠረተ ልማህ ችግር፣ እንዲሁም በፍላጎት እና አቅርቦት መካከል ልዩነት ማኖር የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እየጎዱ ያሉ ችግሮች መሆናቸውም ተገልጿል። በሌላ በኩል የትኞቹን እንደሆነ በግልጽ ለይተው ባያቀርቡም መገናኛ ብዙኃን ግጭት በመፍጠር፣ ግጭት በማባዛት እና መሰል ችግሮች ውስጥ መሆናቸውን ገልፀዋል። ሕዝብ መርጦ እንዲጠቀምም ጠይቀዋል። ብዙ መጎሳቆል ያመጣ ያሉትና ከሸኔ ጋር ያለው ግጭት በሰላም እንዲፈታከፍተኛ ፍላጎት በመንግሥት ደረጃ መኖሩንና በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር የሚመራ የሰላም ድርድርን የሚመራ ኮሚቴ መቋቋሙንም ገልፀዋል። 

የስንዴ ምርት ወደ ውጭ መላክ የውስጥ ፍላጎት ሳይሸፈን የተደረገ ነው በሚል ከጥቅሙ ጉዳቱ ማመዘኑ ተገልጾ ለቀረበ ጥያቄ ምርት በስፋት የተመረተ መሆኑን በመጥቀስ ነገር ግን ምርትን የመደበቅ ችግር መኖሩን አብራርተው ሥራው ግን ስኬት የታየበት መሆኑን አብራርተዋል ።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር