1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጎዳና ንግድ ግብይት

ዓርብ፣ ጥር 10 2011

በአዲስ አበባ ጎዳናዎች በእግረኛ መንገድ የንግድ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርጉ የህገወጥ የመንገድ ዳር ነጋዴዎች፤ እግረኞችንም የትራፊክ እንቅስቃሴንም እያስተጓጎሉ ነው ተብሏል። ህገ ወጥ ነጋዴዎቹም ህጋዊ ሆኖ ለመስራት አቅማቸው እንደማይፈቅድ ይገልጻሉ።

https://p.dw.com/p/3BnM4
Addis Abeba Äthiopien Straßenmarkt
ምስል Dawit Tefera

Street Market - MP3-Stereo

በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች የህገ ወጥ ንግድ ግብይትን መመልከት እንግዳ ነገር አይደለም። በስራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓታት በመዲናዋ ዋና ዋና የሚባሉ አካባቢዎች ይሄው የመንገድ ዳር ግብይት ግርግር ይስተዋላል። ህጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው አትክልት፣ ልብሶች፣ የቤት እቃዎች፣ ሌላም በአስፋልት መንገድ ዳር የሚሸጡ ጥቂቶች አይደሉም።  እነዚህ ነጋዴዎች ህጋዊ ባልሆነው ግብይት ምክንያት በደንብ አስከባሪ እና ፖሊስ መሳደዳቸውም የዕለት ተዕለት ትዕይንት ነው። ነጋዴዎቹ ደንብ አስከባሪዎች ሲመጡባቸው ለማምለጥ በሚያደርጉት ሩጫ ለመኪና አደጋ እንደሚጋለጡ ይገልጻሉ። ሲያዙም “እቃዎቻችን ይደፉብናል፤ በደንብ አስከባሪዎችም ይወረስብናል” ይላሉ። በእንዲህ አይነት ንግድ ላይ ከተሰማሩት አንዱ ካሳሁን ፋንቱ ነው። ስለሚገጥማቸው ችግር ይዘረዝራል። «የምሰራው ህገ ወጥ ንግድ ነው። አንዳንዴ የደንብ ልብስ ሳይለብሱ ይመጣሉ። ይመቱናል እቃችንንም ይደፉብናል» በተመሳሳይም ሌላው የጎዳና ንግድ ላይ የተሰማራው ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገው የካሳሁንን ብሶት ይጋራል። «ብዙ መከራዎች ብዙ ፈተናዎች አሉ። ደንቦች ይመጡብንና ይይዙናል ብለን ለመኪና አደጋ እንጋለጣለን። በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ነው ያለነው። እንመታለን፤ እቃችንን ይወስዱታል» ህጋዊ ፈቃድ ሳይገኙ እየሰሩ ያሉት እነኝሁ የመንገድ ላይ ነጋዴዎች “ህጋዊ ሆነን እንዳንሰራ አቅማችን አይፈቅድም” ይላሉ። «በህጋዊ መንገድ ለመስራት ብዙ ገንዘብ ይጠይቃል። የንግድ ቦታ ተከራይተን መስራት አልቻልንም።» ነጋዴዎቹ የምንሰራበት ቦታ ተሰጥቶን በህጋዊ መንገድ መስራት እንድንችል የሚመለከተውን አካል ብንጠይቅም ምላሽ ግን ተነፍጎናል ይላሉ። “ተመዝገቡ ተብለን ተመዘገብን ሆኖም ምንም ምላሽ የለም” ሲሉም ያማርራሉ። «ተመዝገቡ ቦታ ይሰጣችሃል ይሉን እና ይመዘግቡናል። ከዛ ቦታውን ይሸጣሉ። በሙስና ይሁን እንዴት እንደሚያደርጉት አናቅም።» እነዚሁ በመዲናዋ ጎዳናዎች ንግድን መተዳደሪያ ያደረጉ ነጋዴዎች የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች እንደሆኑ፤ ከራሳቸው አልፈው ቤተሰብ እንደሚረዱና በችግር ላይ እንዳሉ ይገልጻሉ።
 

Addis Abeba Äthiopien Straßenmarkt
ምስል Dawit Tefera

ነጃት ኢብራሂም

ተስፋለም ወልደየስ