1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግንቦት 8 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ግንቦት 8 2014

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለአፍሪቃ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎቹን በደጋፊዎቹ ፊት እንዲያደርግ አልተፈቀደለትም። ከግብፅ፣ ማላዊ እና ጊኒ ጋር በሜዳው ሊያደርጋቸው የነበሩትን ጨዋታዎች በሙሉ ማላዊ ውስጥ ለማድረግ ተገዷል። ይህ ለምን ሆነ? በቡድኑ ላይ የሚኖረው ተጽእኖ ምን ይመስላል? የፕሬሚየር ሊግና ሌሎች የስፖርት መረጃዎችንም አካተናል።

https://p.dw.com/p/4BNSw
Manchester City v Liverpool
ምስል Martin Rickett/empics/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2023 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሜዳው ሊያከናውናቸው የነበሩ የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ (AFCON) የማጣሪያ ጨዋታዎችን ማላዊ ውስጥ ለማድረግ ወስኗል። ኢትዮጵያ በሜዳዋ ማድረግ የነበረባትን ጨዋታዎች እንዳታስተናግድ የታገደችው በአፍሪቃ የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) ነው። ምክንያቱ ደግሞ የባሕር ዳር ስታዲየም ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ብቁ አይደለም መባሉ ነው። ለመሆኑ ይህ ምንን ያመለክታል? 

ኢትዮጵያ በምድብ ማጣሪያው ወደ አፍሪቃ ዋንጫ ለማለፍ ማላዊ ከተፋላሚዎቿ አንዷ ሆና ሳለች ማላዊ ውስጥ ጨዋታዎቿን ማከናወኑ ጠቀሜታ እና ጉዳቱ ምንድን ነው?
ኢትዮጵያ ስታዲየሟን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንድታስተካክል በካፍ ማስጠንቀቂያ ከተሰጣት ረዥም ጊዜ የሚቆጠር ነው። ያ ኾኖ ሳለ ስታዲየሙ በሚፈለገው መልኩ አልተስተካከለም የተባለበት ምክንይቱ ምን ይሆን? በኢትዮ ኤፍ ኤም 107. 8 የኢትዮ ስፖርት ዋና አዘጋጅ እና አቅራቢን አነጋግረናል።

ኢትዮጵያ በሜዳዋ ታደርግ የነበሩትን ቀጣይ የማጣሪያ ጨዋታዎች ለማድረግ የሁለት ሃገራት ከተሞች እንደ አማራጭ ቀርበው ነበር። የደቡብ አፍሪቃ ጆሐንስበርግ ከተማ አለያም የማላዊ ዋና ከተማ ሊሎንግዌ። ፌዴሬሽኑ ማላዊን በመምረጡ በደጋፊዎቹ ፊት ሀገር ውስጥ ያደርጋቸው የነበሩ የማጣሪያ ጨዋታዎችን በአጠቃላይ ቢንጉ ብሔራዊ ስታዲየም እንደሚያደርግ ታውቋል። ኢትዮጵያ ለአፍሪቃ ዋንጫ የማጣሪያ ግጥሚያ በምድብ «መ» ከማላዊ፤ ጊኒ እና ግብጽ ጋር ተደልድላለች። 

ፕሬሚየር ሊግ

የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊጠናቀቅ ጫፍ ደርሷል። ከእንግዲህ መሪው ማንቸስተር ሲቲ አንድ ጨዋታ፤ ተከታዩ ሊቨርፑል ሁለት ጨዋታዎች ይቀራቸዋል። ማንቸስተር ሲቲ በ90 ነጥብ ፕሬሚየር ሊጉን ሲመራ ተከታዩ ሊቨርፑል አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው 86 ነጥብ አለው። 

Fußball | English FA Cup | Chelsea - Liverpool
ምስል Ian Walton/AP Photo/picture alliance

ማንቸስተር ሲቲ ትናንት ከዌስት ሀም ዩናይትድ ጋር ባደረገው ጨዋታ ከሽንፈት የተረፈው ለጥቂት ነው። በጃሮድ ቦዌን ግቦች 2 ለ0 እየመራ ወደ ረፍት ያቀናው ዌስትሀም ዩንይትድ ማንቸስተር ሲቲን እጅግ አስጨንቆ አምሽቷል። አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ቡድናቸው በዌስት ሀም ዩናይትድ አጥቂዎች እንዲያ ሲተራመሱ በጭንቅ ተውጠው፤ ጭንቅላታቸውን ያሻሹ ነበር። የዌስት ሀም ዩናይትድ ተከላካይ ጥፋት ግን ማንቸስተር ሲቲን ጉድ ከመሆን አድኗል። 

የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ 2 ለ0 ተጠናቆ ከእረፍት መልስ ማንቸስተር ሲቲ ግብ ለማስቆጠር አፍታም አልቆየበት። የመጀመሪያዋን ግብ በጃክ ግሪሊሽ በድንቅ ኹኔታ ያስቆጠረው በሁለተኛው አጋማሽ 4ኛ ማለትም 49ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። በ69ኛው ደቂቃ ላይ የዌስት ሀም ዩናይትድ ተከላካይ ብላድሚር ኮፋል ኳሷን በጭንቅላት አጨናግፋለሁ ብሎ በስህተት ከመረብ አሳርፏታል። የሠራው ስኅተት እጅግ ያጸጸተው ተከላካይ ግቧ ከተቆጠረች በኋላ መሬት ላይ በሆዱ ተዘርግቶ ጭንቅላቱን ሳሩ ውስጥ ወሽቆ ለአፍታ ቆይቷል። 

85ኛው ደቂቃ ላይ ማንቸስተር ሲቲ ያገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ሪያድ ማህሬዝ መትቶ ግብ ጠባቂው ፋቢያንትስኪ አጨናግፎበታል። ዌስትሀም ዩናይትድ ወደ አውሮጳ ሊግ ለመግባት እድሉ አሁንም አልተጨናገፈም። ቀሪ ጨዋታውን አሸንፎ የማንቸስተር ዩናይትድ ውጤት ግን መጠበቅ አለበት። 

Jürgen Klopp und Pep Guardiola
ምስል Michael Regan/Getty Images)

66 ነጥብ ሰብስቦ 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል ዛሬ ማታ በኒውካስትል ሜዳ ይጫወታል። ሻምፒዮንስ ሊግ ለመግባት ወሳኝ የሞት ሽረት ግጥሚያው ነው። አርሰናል በዛሬ ተስተካካይ ጨዋታው ካሸነፈ ነጥቡን 4ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ቶትንሀም በአንድ አስበልጦ የሻምፒዮንስ ሊግ ቦታውንም መረከብ ይችላል። ሊቨርፑል 15ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ሳውዝሀምፕተን ጋር ነገ ማታ ይጋጠማል።  
ወደ አውሮጳ ሊግ የምድብ ማጣሪያ ለመግባት ሰፊ ዕድል ለነበረው ዌስትሀም ዩናይትድ በእርግጥም የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር። የማንቸስተር ሲቲን ሽንፈት ቋምጠው ይጠብቁ ለነበሩት የሊቨርፑል ደጋፊዎችም ጭምር። 

በ38ኛው እና የመጨረሻው የፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያ፦ ማንቸስተር ሲቲ አስቶን ቪላን ሲያስተናግድ፤ ሊቨርፑል ዎልቭስን አንፊልድ ላይ ይገጥማል። ማንቸስተር ሲቲ አሁን ባለው 90 ነጥብ ምንም እንኳን ትናንት ከዌስት ሀም ዩናይትድ ጋር ነጥብ ቢጋራም ዋንጫውን የመውሰድ ሰፊ እድል አለው። የሚጠበቅበት ቀሪ አንድ ጨዋታውን ማሸነፍ ብቻ ነው። በዚህም አለ በዚያ ማንቸስተር ሲቲ እሁድ አስቶን ቪላን ካሸነፈ ዋንጫውን በእጁ ያስገባል። ከተሸነፈ ግን ሊቨርፑል ዋንጫውን ከእጁ ሊነጥቀው ይችላል። 

ትናንት ማንቸስተር ሲቲን ነጥብ የተጋራው ዌስትሀም ዩናይትድ በ56 ነጥቡ ከማንቸስተር ዩናይትድ በ2 ነጥብ ተበልጦ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። አሁን ባለው ሁኔታ ማንቸስተር ዩናይትድ የአውሮጳ ሊግ የምድብ ማጣሪያ ተሳታፊ ለመሆን ሰፊ እድል አለው። 

የዘንድሮውን ኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫ ሊቨርፑል ከቸልሲ ጋር ተጋጥሞ በእጁ አስገብቷል። ቅዳሜ ዕለት 90 ደቂቃ ው አልቆ በተራዘመው ጨዋታም ግብ ሳይቆጠር በመለያ ምት 6 ለ5 አሸንፏል። ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ ገና በ23 ዓመቱ ከሻምፒዮንስ ሊግ አንስቶ ሁሉንም ዋንጫዎች በማግኘት ታሪክ ሠርቷል።  

ቡንደስሊጋ
የቡንደስ ሊጋውን ዋንጫ አስቀድሞ የወሰደው ባየርን ሙይንሽን ትናንት ከሽቱትጋርት ጋር ሁለት እኩል ተለያይቷል። መደበኛው 90 ደቂቃ አልቆ በጭማሪው 5 ደቂቃ ላይ ኪንግስሌይ ኮማን ኮንስታንቲን ማቭሮቫኖስን በጥፊ በመምታቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። 

የሜዳ ቴኒስ 
በሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ ትናንት የዓለማችን ድንቅ ተጨዋች ኖቫክ ጄኮቪች ሽቴፋኖስ ትሲትሲፓስን 6 ለ0 እና 7 ለ6 አሸንፏል። በዚህም ኖቫክ ጄኮቪች በዓለም ከፍተኛ ነጥብ ያለው ተጨዋች ሆኖ የመጀመሪያውን ቦታ ይዟል። ሩስያዊው ዳኒል ሜድቬዴቭ በሁለተኛነት ይከተላል። የሩስያ ተጨዋቾች ከዓለም አቀፍ ውድድሮች በመታገዳቸው ነጥቡ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳርፎበታል። እንዲያም ሆኖ በፍጻሜው ለድል ከበቃው ኖቫክ ጄኮቪች ነጥቡ ብዙም አይራራቅም። 

Fussball 2. Bundesliga Werder Bremen - Jahn Regensburg
ምስል Claus Bergmann/IMAGO

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ