ሀዋሳ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በኢትዮጵያውያን ላይ የቀጠለው ጥቃት
በደቡብ አፍሪካ የመጤ ጠል እንቅስቃሴ ጋብ አያለ ቢመጣም «ሕገ ወጥ ግንባታ» በሚል ምክንያት ሱቆቻቸው እየፈረሱባቸው እንደሚገኙ ፍልሰተኛ ኢትዮጵያዊያውያን ለዶቼቬለ ተናገሩ ። በተለይም በጆሃንስበርግ ከተማ ከትናንት ሐሙስ ጀምሮ የበርካታ ፍልሰተኞች ሱቆች በፀጥታ ኃይሎች መፍረሳቸውን በጆሃንስበርግ ከተማ ነሪዎ ኢትዮጵዊያን ተናግረዋል። አንድ ኢትዮጵያዊ «አርምጃው በስደተኞች ላይ ተጨማሪ እንግልት እየፈጠረ ይገኛል» ሲሉ ተናግረዋል።
በደቡብ አፍሪካ ካለፈው አንድ ወር ጀምሮ በተቀሰቀሰው የመጤ ጠል እንቅስቃሴ የኢትዮጵያዊያንና የሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ፍልሰተኞች በርካታ ንብረት መዘረፉንና መቃጠሉን ሸዋንግዛው ወጋየሁ ዘግቧል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቲዎስ በሕንድ ኒው ዴልሂ ከተካሄደው የብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባኤ ጎን ለጎን ከደቡብ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር ሚኒስትር ሮናልድ ላሞላ ጋር በኢትዮጵያውያን ዜጎች ስጋቶች ላይ መነጋገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል። ሚኒስትሮቹ በሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ባተኮረው ውይይታቸውም በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያውያንን ስጋቶችንና ችግሮችን በጋራ ለመፍታት በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጿል።
ኬፕ ታውን ኤቦላ በኮንጎ 64 ሰዎችን ገደለ
በኮንጎዋ ኢቱሪ ክፍለ ሀገር በተከሰተ አዲስ የኤቦላ ወረርሽኝ 65 ሰዎች መሞታቸውን መታወቁን የአፍሪቃ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል አስታወቀ። ድርጅቱ እንዳለው 246 ሰዎች በበሽታው ሳይያዙ አልቀረም። ሰዎች በኤቦላ መሞታቸው የታወቀውና እና ተይዘዋል ተብለው የተጠረጠሩት ፣ሞንግዋሉ እና ርዋምፓራ በተባሉት የጤና ዞኖች በተሰበሰበ መረጃ መሠረት ነው። ከሟቾቹ መካከል አራቱ በተህዋሲው መያዛቸው በላቦራቶሪ በተካሄደ ደም ምርመራ በኤቦላ መሞታቸው ተረጋግጧል።
የማዕከሉ ሃላፊ ማክሲሚላን ጌርትለር የአዲሱ ኤቦላ ስርጭት አጀማመርን አደገኛ ብለውታዋል። ወደ 250 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጠ ኤባላ ሳይታወቅ እየተስፋፋ ነውም ብለዋል። ጌርትለር እንዳሉት ተውሃሲው ምናልባትም በጣም ሩቅ ከሆነ አካባቢ የተሰራጨ ነው። በጀርመን ዜና አገልግሎት ዘገባ መሠረት አዲሱ ወረርሽኝ ከተለመደው የዛየር ኤቦላ ተኅዋሲ ጋር የተያያዘ ሳይሆን ዝርያው ሌላ በሆነ የኤቦላ ተህዋሲ የተከሰተ ነው። የኤባላ ተኅዋሲ ከደም እና ከሰውነት በሚወጡ ሌሎች ፈሳሾች ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል።
ቤጂንግ የዩናዮትድ ስቴትስ እና የቻይና ጉባኤ ፍጻሜ
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሁለት ቀናት የቻይና ጉብኝታቸውንአጠናቀው ዛሬ ወደ ዋሽንግተን አምርተዋል። ትራምፕ ከቤጂንግ የተነሱት ከቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂን ፒንግ ጋር የመጨረሻውን ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው። ሁለቱ መሪዎች የዩናዮትድ ስቴትስ እና የቻይናን ግንኙነት በማረጋጋት ረገድ ለውጦች ማድረጋቸውን ተናግረዋል። ይሁንና ከሁለቱ ቀናት ውይይት በኃላ አሁንም ጥልቅ ልዩነቶች እንዳሉ ሳይገልጹ አላለፉም
ቻይና በኢራኑ ጦርነት ጉዳይ ያን ያህል ይበልጥ ተሳታፊ የመሆን ፋላጎት እንዳላሳየች አሶስየትድ ፕሬስ ዘግቧል። ይሁንና ትራምፕ እንዳሉት ዢ ፣ቻይና የኢራኑን ጦርነት ለማስቆም እና የሆርሙዝ ሰርጥ እንደገና እንዲከፈት ለመደራደር እንደምትረዳ ነግረዋቸዋል። ቻይና ትልቋ የኢራን ነዳጅ ገዢ ሀገር ናት። እናም ትራምፕ ዢ ይህንን ኃይል ኢራንን በአሜሪካ ውሎች መሰረት ወደ ስምምነት ለማስገባት እንደሚጠቀሙበት ተስፋ ያደርጋሉ። ትራምፕ በተጨማሪም ዢ ቻይና ለኢራን ወታደራዊ መሳሪያ እንደማትሰጥ አረጋግጠውኛል ብለዋል። ዢ በታይዋን ጉዳይ ላይ አሜሪካ እና ቻይና ያላቸው ልዩነቶች አገራቸውን ወደ ግጭት ሊያመሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል። ሁለቱም ወገኖች ከፍተኛ የታሪፍ ጭማሪ እንደሚያደርጉ አሁንም ስጋቶች አሉ።
ኒውዴልሂ የብሪክስ አባል ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባኤ ያለ ጋራ መግለጫ አበቃ
በማደግ ላይ ያሉ አገሮች የተሰባሰቡበት የብሪክስ አባል ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ለሁለት ቀናት ኒው ዴልሂ ህንድ ውስጥ ያካሄዱትን ጉባኤ የጋራ መግለጫ ሳያወጡ ዛሬ አበቁ። አስተናጋጇ ህንድ ብቻዋን ባወጣችው መግለጫ እንዳለችው ይህ የሆነው በመካከለኛው ምሥራቅ ሁኔታ ላይ አንዳንድ አባል ሀገራት የተለያዩ አመለካከቶች በማንጸባረቃቸው ነው። እነዚህ ልዩነቶችም የመስፋፋት ፍላጎት ያለውን ብሪክስን በአባል ሀገራት መካከል አንድነቱን ይዞ የማቆየት ፈተና ላይ ጥሎታል። የህንድ መግለጫ እንዳመለከተው አባል ሀገራት በመካከለኛው ምስራቅ ሉዓላዊነትን፣ የባህር ደህንነትን እና የሲቪል መሠረተ ልማቶችን እና የሲቪል ህይወትን መጠበቅን ጨምሮ በጉዳዩ ላይ “የየራሳቸውን ብሔራዊ አቋም” እና የተለያዩ አመለካከቶች አጋርተዋል። በኢራን ጦርነት ወቅት በተለይም ኢራን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን በተመለከተ በአባል ሀገራት መካከል ያለው ክፍፍል በግልጽ ታይቷል። የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ “ሕገ-ወጥ ወረራ” ያሉትን አሜሪካንና እስራኤልን በኢራን ላይ የከፈቱትን ጦርርነት የብሪክስ አባል አገራት ፣ እንዲያወግዙ ትናንት ሐሙስ አሳስበዋል። ከዚህ በተጨማሪም አባል ሀገራት ፣ዓለም አቀፍ ተቋማትን ለፖለቲካ ዓላማ መጠቀሚያ ማድረግን እንዲቃወሙም ጥሪ አቅርበዋል። ብሪክስ ፣ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ኢራን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ኢንዶኔዥያ ያካትታል።
ምዕራቡ ዓለም በሚወዛገብበት የኒዩክልየር ጉዳይ ሩስያ ድጋፍ የማድረግ ሃሳብ ማቅረቧን ኢራን አረጋገጠች
ኢራን ከምዕራቡ ዓለም ጋር በሚያወዛግባት በኒዩክልየር ጉዳይ ላይ ሩስያ የበኩሏን ድጋፍ የማድረግ ሃሳብ እንዳቀረበች ኢራን አረጋገጠች። የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ዛሬ ኒውዴልሂ ውስጥ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በሩስያ ጉብኝታቸው ወቅት ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ስለ ዩራንየም ጉዳይ መነጋገራቸውን ገልጸው ድጋፍ ለመስጠት ላቀረቡት ሀሳባቸውም አመሰግናቸዋለሁ ብለዋል። ከብሪክስ አባል ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባኤ ጎን ለጎን አራግቺ በሰጡት በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ፑቲን በቅርቡ ስለዚሁ ጉዳይ የተናገሩትን አረጋግጠዋል። ፑቲን ባለፈው ሳምንት ሀገራቸው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተጎናጸፈችው ድል በተዘከረበት የመታሰቢያ በዓል ላይ ሩሲያ በከፍተኛ ደረጃ የበለፀገ ዩራኒየምን ከኢራን ወስዳ ለማከማቸት ዝግጁ መሆኗን አስታውቀው ነበር።
የኢራን የኒዩክልየር መርሀ ግብር ሲያወዛግብ ብዙ ዓመታት አስቆጥሯል። ዩናይትድ ስቴትስ እሥራኤል እና ምዕራባውያን ሀገራት ቴህራን የኒዩክልየር ጦር መሣሪያዎችን ለማምረት ትፈልጋለች ሲሉ ይከሷታል። ኢራን ግን ይህን ታስተባብላለች። ምዕራቡ ዓለም ኢራን አሁን ያላት የዩራንየም ክምችት ከ
ዳበረ በርካታ የኒዩክልየር ጦር መሣሪያዎች ለመስራት በቂ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አለው። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የሚገኘው ዩራንየም ከሀገሪቱ እንዲወጣ ግፊት እያደረጉ ነው። ዩራንየሙ ከምድር በታች ከሚገኙ የኢራን የኒዩክልየር ተቋማት በአንዱ ውስጥ እንደተከማቸው ይገመታል።
ቡዳፔስት ሀንጋሪ በሀገርዋ የሩስያን አምባሳደር ጠርታ አነጋገረች
የሀንጋሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አኒታ ኦርባን በሀንጋሪ የሩስያውን አምባሳደር ኤቭግኒ ስታኒስላቮቭን ሩስያ በዩክሬንዋ በትራንስካርፓትያ ግዛት ረቡዕ ስላካሄደችው የድሮን ጥቃት ትናንት ጠርተው አነጋገሩ ። ጥቃቱ የተፈጸመበት ስፍራ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው አናሳ ሀንጋርያውያን መኖሪያ ነው።
ሚኒስትሯ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴያቸው ከሩስያው አምባሳደር ጋር የአናሳ ሀንጋሪያውያን መኖሪያ የሆነው ትራንስካርፓትያ ላይ ጥቃት መፈጸሙ በሀንጋሪ ፍጹም ተቀባይነት እንደሌለው እንደነገሩዋቸው ጽፈዋል። ከዚሁ ጋር አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና በተቻለ ፍጥነት ጦርነቱ በሰላማዊና ዘላቂ መንገድ እንዲያበቃ ሩስያ የተቻላትን ሁሉ ማድረግ እንዳለባትም ማሳሰባቸውን ገልጸዋል።
አምባሳደሩ ከ30 ደቂቃ በኋላ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮ ሲወጡ ታይተዋል። ሩስያ ረቡዕ ዩክሬን የሚገኙ 20 ግዛቶችን ዒላማ ያደረጉ 800 ድሮኖችን ተኩሳለች። በስፍራው በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ 6 ሰዎች ሲገደሉ ህጻናትን ጨምሮ በርካቶች ቆስለዋል።
ከአምባሳደሩ ጋር ከተካሄደው ንግግር በኋላ የሩስያ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ የሩስያ ጥቃት ዒላማ ለዩክሬን ጦር ጥቅም ላይ የሚውሉ ተቋማትና መሠረተ ልማቶች እንጂ ሰላማዊ ሰዎች እንዳልነበሩ አስታውቋል። ሀንጋሪ የሩስያን አምባሳደር ጠርታ ማናገሯን ወሳኝ መልዕክት ያሉት የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ የሀንጋሪን ፕሬዝዳንት ፒተር ማግያርን አመስግነዋል።
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ