መተከል፤ በመኪና ላይ በደረሰው የታጣቂዎች ጥቃት የበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፉ
ትናንት ከአሶሳ ወደ መተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ ይጓዙ በነበሩ ተሽከርካሪዎች ላይ በተፈጸመ የታጣቂዎች ጥቃት የበርካቶች ሕይወት ማለፉ ተሰማ። ጥቃቱ የደረሰው በጉባ ወረዳ በሚገኘው አፍሪካ እርሻ ልማት በሚባል አካባቢ ሲሆን ከሞቱ መካከል የ23 ሰዎች ሰርዓተ ቀብር አይስድ እና ማኩንሽ በተባለ ከተማ መፈጸሙን ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የጤና ባለሙያ ገልጸዋል። በደረሰው ጥቃት የሟቶች ቁጥር ከ30 በላይ እንደሆነ አንድ ሌላ የአካባቢው ነዋሪ ተናግረዋል። በጥቃቱ ከሕይወት ህልፈት በተጨማሪ ተሽከርካሪዎችም መቃጠላቸው ነው የተነገረው። የጉዳት መጠኑን በተመለከተ ሁለት ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ የተለያየ ሃሳብ የሰጡ ሲሆን በዚህ ጉዳይ ላይ በክልሉ መንግሥት በኩል በይፋ የተባለ ነገር እንደ ሌለ ከአሶሳ ዘጋቢያችን ነጋሳ ደሳለኝ የላከው ዜና ያስረዳል።
አዲስ አበባ፤ የፈረንሳይ ፕሬዝደንት አዲስ አበባ ገቡ
የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ማኑዌል ማክሮ በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ ገብተዋል። ማክሮ ወደ አዲስ አበባ ያቀኑት ሰሞኑን ከአፍሪቃ መሪዎች ጋር የሀገራቸውን ትብብር ለማጠናከር ባለመ ጉዟቸው መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ። ማክሮን የተቀበሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከፈረንሳዩ መሪ ጋር «በጋራ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የሁለትዮሽ ውይይት አካሂደናል» ሲሉ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ገጻቸው መልእክት አስተላልፈዋል። አክለውም «በሁለቱ ሃገራት መካከል የተደረጉ ቁልፍ ስምምነቶች ልውውጥን» በጋራ የመሩ መሆኑን አመልክተው፤ ከስምምነታቸው መካከልም፤ «የታዳሽ፣ የተቀናጀ እና ዘላቂ ኃይል እንዲሁም የዲጂታላይዜሽን» መርኀግብርን ለመተግበር የሚውል የ54.6 ሚሊዮን ዩሮ የብድር ስምምነት መደረጉን ገልጸዋል። ከዚህም ሌላ «የ150 ሜጋ ዋት የጂኦተርማል የመንግሥትና የግል አጋርነት አዲስ የማዕቀፍ እና የፍኖተ ካርታ ልውውጥ»ም ከስምምነቶቹ ውስጥ እንደሚገኙም አስታውቀዋል።
ማክሮ ናይሮቢ ኬንያ ከአፍሪቃ መሪዎች ጋር ባደረጉት የአፍሪቃ ትቅደም ጉባኤ ላይ አፍሪቃ ውስጥ ሀገራቸው ፈረንሳይ 27 ቢሊየን ዶላር ሥራ ላይ እንደምታውል ተናግረዋል። ከኬንያ ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙት የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ግብጽንም እንደሚጎበኙ ይጠበቃል።
አክራ፤ ጋና ዜጎቿን ከደቡብ አፍሪቃ ልታወጣ ነው
ጋና ከደቡብ አፍሪቃ 300 ዜጎቿን ልታወጣ መሆኑን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት ዜጎች ላይ የሚፈጸመው የጥላቻ ድርጊት መደጋገም ብዙዎቹ የክፍለ ዓለሙን ሃገራት መሪዎች አስቆጥቷል። የጋና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦኩድ ዜቶ አባላ ካዋ፣ ደቡብ አፍሪቃ የሚገኙ ዜጎች የመንግሥታቸው እርዳታ ፈልገው ተመዝግበዋል ብለዋል። አንዳንድ ደቡብ አፍሪቃውያን ከሌላ የአፍሪቃ ሃገራት በሕገወጥ መንገድ ወደ ሀገራቸው የሚደረገውን ስደት ይቃወማሉ። የሀገሪቱ ባለሥልናት በጥላቻ የሚፈጸመውን ጥቃት ቢያወግዙም ሕገ ወጥ ስደት ችግር አምጥቷል እያሉ ነው። ጥቃቱን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ባሰራጩት መልክእት የተቃወሙት የጋና ባለሥልጣናት፤ የዜጎቻቸውን ደኅንነት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ እንደሚጠብቁ ቃል ገብተዋል። ሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት ኬንያ፤ ማላዊ፤ ሌሴቶና ዚምባቡዌ ደቡብ አፍሪቃ የሚገኙ ዜጎቻቸው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። ናይጀሪያም 130 የሚሆኑ ዜጎቿ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ መመዝገባቸውን አስታውቃለች።
ቤይሩት፤ በእስራኤል የአየር ጥቃት ዘጠኝ መገደላቸው
እስራኤል በዛሬው ዕለት ሊባኖስ ላይ የምታደርሰውን የአየር ጥቃት ማጠናከሯ እየተገለጸ ነው። የሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ይፋ እንዳደረገው በቤይሩት እና በሲዶን ከተሞች መካከል ባነጣጠረው የዛሬው ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች ተገድለዋል። ሂዝቦሃህ በበኩሉ በዛሬው ዕለት ደቡባዊ ሊባኖስን በወረሩ የእስራኤል ወታደሮች ላይ በርካታ ጥቃት አድርሻለሁ ማለቱን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል። የእስራኤል ሰው አልባ አውሮፕላኖች በደቡባዊ ቤይሩት አካባቢ ባደረሱት ጥቃትም አንድ እናትን ከሁለት ልጆቻቸው ጋር ጨምሮ ስምንት ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል። የእስራኤልና ሊባኖስ ባለሥልጣናት በአሜሪካ አደራዳሪነት ተኩስ ስለማቆም ቢነጋገሩም ጥቃቱ እንዳላባራ ዘገባዎች ያመለክታሉ። የሊባኖስ የጤና ሚኒስትር ራካን ናስረዲን ትናንት በሰጡት መግለጫ የእስራኤል ጥቃት የጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ላይም ጉዳት እያደረሰ መሆኑን አመልክተዋል። በዚህ መሀልም በዓለም አቀፍ ደንቦች ከለላ እንዲደረግላቸው የተደነገገላቸው ሲቪሎች ለጉዳት እየተዳረጉ መሆኑንም ተናግረዋል።
«በዓለም አቀፍ ስምምነቶች፤ በሰብአዊ መብቶች ደንቦች እና ውሎች ጥበቃ እንዲደረግላቸው ስለተደነገገው ሲቪሎች ሰብአዊ መልእክት ነው። ሆኖም ሁሌም እንደተናገርነው እና አሁንም እንደምንለው እስራኤል በዚህ ደንብ እየተገዛች አይደለም።»
በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ሊባኖስ አሜሪካ እስራኤል ጥቃቷን እንድታቆም ጫና እንድታደርግ ጠይቃለች። የሂዝቦላህ መሪ ነኢም ቃሲም በበኩላቸው ተዋጊዎቻቸው የጦር ሜዳውን ለእስራኤል ወደ ሲኦልነት ይቀይሩታል ሲሉ ትናንት ማስጠንቀቃቸው ተዘግቧል።
ቴህራን፤ ኢራን በእስራኤል ሰላይነት የጠረጠረችውን ሰው በስቅላት መቅጣቷ
የኢራን ባለሥልጣን በዛሬው ዕለት ለእስራኤል በመሰለል የተጠረጠረ ግለሰብን በስቅላት መቅጣታቸው ተዘገበ። እስራኤል እና አሜሪካ ከኢራን ጋር ጦርነት ከጀመሩ አንስቶ የቴህራን ባለሥልጣናት በስቅላት የቀጧቸው ሰዎች ቁጥር ስድስት መድረሱን የአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ ያስረዳል። በሠላሳዎቹ የዕድሜ መጀመሪያ ላይ ይገኝ ነበር የተባለው ኤህሳን አፍረሽታህ ኔፓል ውስጥ በሞሳድ የሰለጠነ እንደሆነ የኢራን የፍትህ ጉዳይ ድረገጽ ባወጣው መረጃ አመልክቷል። ለእስራኤልም ልዩ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው መረጃዎችን ልኳል ሲልም ከሷል። መቀመጫውን ኖርዌይ ያደረገው የኢራን የሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ግን ሟቹ ለእስራኤል ሰጥቷል የተባለውን መረጃ አልሰጠሁም ማለቱን ገልጿል። ሆኖም ተጠርጣሪው በቴሌቪዥን ቀርቦ በግዳጅ ክሱን እንዲያምን መደረጉን አመልክቷል። ድርጅቱ አክሎም ግለሰቡ ቱርክ ውስጥ ይኖር እንደነበርና በኢራን ባለሥልጣናት ዋስትና ተሰጥቶት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ወደዚያ በሄደበት ተይዞ፤ ለብቻው ታስሮ ቆይቶ፤ በስቅላት መቀጣቱን ነው የገለጸው። እንደ መብት ተቆርቋሪው ድርጅት ተጠርጣሪው ላይ የቀረበው የሀሰት ክስ ነው።
ቤጂንግ፤ ትራምፕ ለጉብኝት ቻይና ገቡ
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በዛሬው ዕለት ከቀትር በኋላ ቻይና ገብተዋል። ትራምፕ ወደ ቻይና የተጓዙት በሀገሪቱ ፕሬዝደንት ሺ ጂምፒንግ በተደረገላቸው ግብዣ እንደሆነ ተገልጿል። የትራምፕ ጉዞ በዘጠኝ ዓመታት ውስጥ በአሜሪካ ፕሬዝደንት ወደቻይና የተደረገ የመጀመሪያ ጉብኝት ነው። ሁለቱ መሪዎች በሚኖራቸው የቆይታ ጊዜ ከቻይና አሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነት አንስቶ፤ ስለዓለም ሰላምና እድገት በሰፊው እንደሚነጋገሩ የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጉኦ ጃኩን ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫም የመሪዎቹ ዲፕሎማሲ ለቻይና አሜሪካ ትብብር የማይተካ ስልታዊ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።
«የመሪዎች ዲፕሎማሲ በቻይና እና በአሜሪካ ግንኙነት ውስጥ የማይተካ ስልታዊ ሚና ይጫወታል። ቻይና የፕሬዝደንት ትራምፕን ጉብኝት በደስታ ተቀብላለች፤ የሁለቱ ሃገራት መሪዎች በሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሰላምና ልማት ባሉ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ዕይታ ይለዋወጣሉ። ቻይና ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ትብብሯን ለማስፋት እና ልዩነትን ለማጣጣም፤ እንዲሁም በተበጠበጠው ዓለም መረጋጋትን ለማምጣት በእኩልነት መንፈስ፤ በመከባበርና ለጋራ ጥቅም ትሠራለች። »
ኢስታንቡል፤ ቱርክ 300 ተጠርጣሪ የእስላማዊ መንግሥት አባላትን ማሰሯ
የቱርክ ፖሊስ እራሱን እስላማዊ መንግሥት በሚለው ጽንፈኛ ቡድን አባልነት የተጠረጠሩ ከ300 በላይ ሰዎችን ማሰሩን የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር ዛሬ አስታወቀ። ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን የያዘው በ47 ክፍለ ሃገራት ባካሄደው አሰሳ መሆኑ ተገልጿል። የቱርክ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ሙስጠፋ ሲፍቲች በኤክስ ገጽጻቸው ባሰተላለፉት መልእክት፤ የሀገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች የጦር መሣሪያዎችን፤ ጥሬ ገንዘብ እና ዲጂታል መረጃዎችን ይዘዋል። የቱርክ ባለሥልጣናት በተጠቀሰው ቡድን አባልነት የተጠረጠሩና ለትስስሩ ምልመላ የሚያካሂዱትን ለመያዝ ተደጋጋሚ አሰሳ እንደሚያደርጉ የጀርመን የዜና አውታር ዲፔአ በዘገባው ጠቅሷል። ጽንፈኛው ቡድን ባለፉት ዓመታት ቱርክ ውስጥ ለደረሱና ሕይወት ለቀጠፉ ጥቃቶች ኃላፊነቱን የወሰደባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉም አመልክቷል። ባለፈው ታኅሣስ ወር ቡድኑ እንዳደረሰው በተጠረጠው ጥቃት ሦስት የቱርክ ፖሊሶች ተገድለዋል። የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ባለፈው ወር ኢስታንቡል በሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ ላይ ለደረሰው ጥቃትም ቡድኑን ተጠያቂ ያደርጋሉ። ቡድኑ ግን ለጥቃቱ ኃላፊነቱን አልወሰደም።
ሸዋዬ ለገሠ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር