1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግንቦት 23 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ግንቦት 23 2013

አውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ቸልሲን ለድል ያበቁት ጀርመናዊው አሰልጣኝ ቶማስ ቱኁል ማን ናቸው? እኚሁ አሰልጣኝ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግም ቸልሲን ከነበረበት የ9ኛ ደረጃ በአጭር ጊዜያት ወደ አራተኛ ከፍ ለማድረግስ እንዴት ቻሉ? ትንታኔ ይኖረናል።

https://p.dw.com/p/3uEtF
Weltspiegel | 31.05.2021 | Chelsea gewinnt Champions League Finale
ምስል David Ramos/REUTERS

ሣምንታዊ የስፖርት ዜና

አውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ቸልሲን ለድል ያበቁት ጀርመናዊው አሰልጣኝ ቶማስ ቱኁል ማን ናቸው? እኚሁ አሰልጣኝ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግም ቸልሲን ከነበረበት የ9ኛ ደረጃ በአጭር ጊዜያት ወደ አራተኛ ከፍ ለማድረግስ እንዴት ቻሉ? ትንታኔ ይኖረናል። በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ (ቤት ኪንግ) አሸናፊ ፋሲል ከነማ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ከወዲሁ ቃል ተገብቶለታል። የአውሮጳ እግር ኳስ ፍልሚያ ሊጀምር ከሁለት ሳምንት በታች ይቀረዋል። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ሁለት የቀድሞ ተጨዋቾችን ልምድ እና ብቃት ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ዳግም ያስፈለገው ይመስላል።

ፕሬሚየር ሊግ

በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ (ቤት ኪንግ) አሸናፊ ለኾነው ፋሲል ከነማ ከ170 ሚሊዮን በላይ ብር ቃል ተገብቶለታል። ቡድኑ ባለፈው አርብ ባሕር ዳር ከተማ ሲገባም ደማቅ አቀባበል ነበር የተደረገለት።

የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበትም በአቫንቲ ብሉናይል ሆቴል የእራት ግብዣ ለተደረገለት ፋሲል ከነማ ቡድን ከተለያዩ ባለሀብቶችና ደርጅቶች የ31ሚሊዮን ብር ቃል ተገብቶለታል። ባለፈው ሳምንት ማክሰኞም ቡድኑ በሸራተን አዲስ የክልሎች ባለስልጣናት በተገኙበት አቀባበል የተደረገለት ሲሆን ለቡድኑ መጠናከሪያ ከ170 ሚሊዮን ብር በላይ ቃል ተገብቷል። የቡድኑ የመሐል ተጫዋች ሱራፌል ዳኛቸው ከዶይቼ ቬለ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጎ ነበር።

Äthiopien| Fasil Kenema Sport Club
ምስል Alemenew Mekonnen/DW

በነበረው አጭር ቃለ ምልልስ «ከዚህ በኋላ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር አለብን ደስታውን በልክ እናደርግና ኮንፌደሬሽን ካፕ ተወዳድረናል፣ ብዙ ልምድ አግኝተንበታል በደንብ ተዘጋጅተን የተሻለ ውጤት እናስመዘግባለን ብዬ አስባለሁ» ብሏል። በአዲስ አበባና በባሕር ዳር ሕዝቡ ያደረገላቸው አቀባበል ከጠበቁት በላይ እንደነበረም ሱራፌል ተናግሯል።

ባለፈው ቅዳሜ ቡድኑ ጎንደር ከተማ ሲገባ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የከተማዋ ነዋሪ የክለቡን መለያ በመልበስ አደባባይ በመውጣት ለፋሲል ከነማ በጣም በደመቀ መልኩ እንደተቀበለው የባህር ዳሩ ወኪላችን ዓለምነው መኮንን የላከልን ዘገባ ይጠቁማል።

ዘንድሮ በእንግሊዝ ፕሬሚየ ርሊግ ሲዋዥቅ የነበረ ቡድናቸውን በአችር ጊዜ ውስጥ ለሻምፒዮንስ ሊግ ስላበቁት ጀርመናዊው አሰልጣኝ ቶማስ ቱኁል የተወሰኑ ነገሮችን እናካፍላችሁ። ቶማስ ቱኁል፦ ለዓመታት ከነበሩባቸው ቡድኖች በበለጠ ከቸልሲ ጋር ያላቸው አጭር ቆይታ እጅግ እንደሚያስደስታቸው ሰሞኑን ዘ ጋርዲያን ለተሰኘው ጋዜጣ ተናግረዋል። ከሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ድል በኋላም የቸልሲው ባለሀብት ሮማን አብራሞቪች ውላቸውን እንዲታደስ ለማድረግ ትናንት አነጋግረዋቸዋል። ጀርመናዊው አሰልጣኝ ስታምፎርድ ብሪጅ ውስጥ ለቸልሲ መጀመሪያ የፈረሙት ለ18 ወራት ብቻ ነበር።

Fußball Porto | UEFA Champions League Finale | Trainer Thomas Tuchel
ምስል Pierre P. Marcou/AFP/AP/picture alliance

ቶማስ ቱኁል ባለፈው ጥር ወር ከፈረንሳዩ ፓሪ ሳንጃርሞ ቡድን አሰልጣንነታቸው እንደተሰናበቱ ነበር ቸልሲን የያዙት። የቸልሲ አሰልጣኝ ኾነው ውል ሲፈርሙም እንዲያሰለጥኑ ኃላፊነት የተሰጣቸው ቡድን በፕሬሚየር ሊጉ ደረጃው ዘጠነኛ ነበር። በፕሬሚየር ሊጉ አራተኛ ኾነው በማጠናቀቅ በቀጣይ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነታቸውን አረጋግጠዋል። በግማሽ ፍጻሜው የፔፕ ጓርዲዮላን ማንቸስተር ሲቲን 1 ለ0 በማሰናበት ቸልሲን ለኤፍ ኤ ካፕ ፍጻሜ አብቅተዋል። በእርግጥ በፍጻሜው በላይስተር ሲቲ 1 ለ0 ተሸንፈው ዋንጫውን ማንሳት ቢሳናቸውም ማለት ነው። ከምንም በላይ ግን ከአሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ እጅ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን መንጠቃቸው እጅግ ከፍተኛው ስኬታቸው ነው። ይኽን ዋንጫም ለወላጆቻቸው እና ለባለቤታቸው መታሰቢያ አድርገዋል።

ቸልሲ በፍራንክ ላምፓርድ የአሰልጣኝነት ጊዜ ተደጋጋሚ የመከላከል ችግር ተስተውሎበት ነበር። የባላጋር ቡድን ኳስ አስጨንቆ ሲነጥቅ በተለይ ቡድኑ መከላከል ሲሳነው ተስተውሏል። ይኼ ደግሞ ቡድኑ የነበረውን የሜዳ ላይ አወቃቀር ችግር የሚያመላክት ነበር። ሜዳ ላይ የተጨዋቾች አሰላለፍ በጣም ተጠጋግቶም ኾነ ተራርቆ የሚዋቀር ከኾነ ቡድኑ በአስጨናቂ ባላጋራ ለችግር ይጋለጣል። ይኽ የፍራንክ ላምፓርድ ትልቁ ችግር ነበር በኋላ ላይ ቶማስ ቱኁል በፍጥነት ሊቀይሩት የቻሉት። በዚያ ላይ ፍራንክ ላምፓርድ የትኛው ተጨዋች የትኛው ቦታ ይበልጥ ይመጥነዋል የሚለውን ወሳን ጥያቄ መመለስ የቻለ አልነበረም። ለአብነት ያኽል ጀርመናዊው አጥቂ ካይ ሐቫርትስን በ8፣ 9፣ እና 10 ቁጥር ቦታዎች እንዲሁም በክንፍ አሰልፎ ለማጫወት በተደጋጋሚ ሞክሯል።  

ቶማስ ቱኁል ቸልሲን በአሰልጣኝነት እንደተረከቡ ግን በመጀመሪያ ጨዋታቸው የቡድን አወቃቀር እና የአጨዋወት ስልት በፍጥነት ነው የቀየሩት። የተጨዋቾች የግል ጥረትም ፈጣን ለውጥ ዐሳይቷል። ጀርመናዊው አሰልጣኝ፦ ከዎልቨርሐምፕተን ጋር ባደረጉት የመጀመሪያ ግጥሚያቸው ከኋላ አምስት ተጨዋቾችን በማሰለፍ አማካይ ቦታውን እኩል በእኩል ወደ ኋላ እና ወደፊት በሚመለሱ አማካዮች አጠናክረዋል።

Fußball Porto | UEFA Champions League Finale | Kai Havertz Jubel Pokal
ምስል Manu Fernandez/AP/picture alliance

በዚህም መሰረት ሁለት ወደ ኋላ ተመላሽ አማካይ ተጨዋቾችን ከሌሎች ሁለት ወደማጥቃቱ የሚያዘነብሉ አማካዮች ጋር በማድረግ አሰለፉ። በአጥቂ መስመር ያሰለፉት አንድ ተጨዋች ብቻ ነበር፤ ኦሊቨር ጂሩን።  ከ10 ቁጥር ጀርመናውያን ተሰላፊዎቹ መካከል ቲሞ ቬርነርን ተቀያሪ ወንበር ላይ አድርገው ካይ ሓቫርትስን በአጥቂ አማካይ መስመር ነበር ያሰለፉት። በ3-2-4-1 አሰላለፍ ስልታቸው ቸልሲ ጨዋታው ከጀመረ ከ15 ደቂቃ በኋላ 85 በመቶ ኳስ መቆጣጠር ችሎም ነበር። የመጀመሪያ ጨዋታቸው ያለምንም ግብ ቢለያይም ከፍራንክ ላምፓርድ በተለየ መልኩ ቸልሲ ኳስ መቆጣጠር እንደሚችል በተግባር ያሳዩበት ግጥሚያ ነበር።

ከዚያ በኋላ አሰልጣኙ በሁለተኛ ግጥሚያቸው በርንሌይን 2 ለ0 በማሸነፍ በፕሬሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ድላቸውን አስመዝግበዋል። በዚህኛው ግጥሚያቸው ግን ቶማስ ቱኁል ከ3-2-4-1 ወደ 3-4-2-1 የማጥቃት ስልት አሰላለፋቸውን ይዘው ነበር ወደ ሜዳ የገቡት። ከፊት መስመር በጂሩ ፈንታ ታሚ አብራሀምን አጥቂ አሰልፈው አጥቂው ቲሞ ቬርነርን እና እንግሊዛዊው አማካይ ማሶን ማውንትን ከአራቱ አማካዮች እና ከብቸኛው አጥቂ መሀል አሰልፈው ባላጋራቸውን አስጨንቀዋል። በርንሌዎች በአጥቂዎችን አማካዮች ሲጨነቁ የቸልሲን ውጤት የቀየሩት ተከላካዮቹ ማርኮስ አሎንሶ እና ሴዛር አዝፒሉቼታ ነበሩ። አሰልጣኙ በምዕራብ ለንደን ግራ ተጋብተው የነበሩ ጀርመናውያን አጥቂዎች፦ ካይ ሐቫርትስ እና ቲሞ ቬርነር ጎልተው እንዲወጡም ዕድሉን የበለጠ አመቻችተዋል። ሦስቱ ጀርመናውያን ወደፊት በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የሚያሳዩትን መጠበቅ ነው።

Infografik Tuchel's men in possession EN

እንዲህ እንዲህ እያሉ ታዲያ አሰልጣኝ ቶማስ ቱኅል ግራ የተጋባውን የቸልሲ ቡድን መልክ ማስያዝ ችለዋል። በተለይ በፕሬሚየር ሊጉ ሦስተኛ ግጥሚያቸው በ22ኛው ዙር ጨዋታ ቶትንሀምን አንድ ለዜሮ ማሸነፋቸው አሰልጣኙ ዋዛ እንዳልሆኑ ማሳያ ነበር። በዚህ ግጥሚያ የበለጠ የማጥቃት ስልትን የተከተለ አሰላለፍ ይዘው ነበር ወደሜዳ የገቡት። ቲሞ ቬርነር እና ካሉም ሑድሰን ኦዲን ከፊት አጥቂ መስመር አሰልፈው አማካዩ ማሶን ማውንት አጥቂዎቹን እንዲያግዝ አድርገዋል። ከኋላ አራት አማካዮች እና ሦስት ተከላካዮችን በማካተት ይበልጥ በአማካይ እና አጥቂ የተዋቀረ ቡድን ይዘው ነበር የገቡት 3-4-1-2 አሰላለፍ። በዚህ ወሳኝ ግጥሚያም ሁለተኛ ድላቸውን ያስመዘገቡት ቶማስ ቱኅል በደረጃው ከ7ኛ ወደ ስድስተኛ ከፍ በማለት የተቀናቃኛቸው ቶትንሀምን ቦታ መረከብ ችለዋል። በሦስተኛ ድላቸው ሼፊልድ ዩናይትድ 2 ለ1 በአራተኛ ስኬታቸው ኒውካስትል ዩናይትድን 2 ለ 0 ድል አድርገዋል። በ24ኛ ዙር ግጥሚያ ቸልሲ ከ9ኛ ደረጃ ከፍ አድርገው አራተኛ ደረጃ ላይ ማስቀመጥ ችለዋል።  ከዚያ በኋላ ቸልሲን የሚያቆመው አልተገኘም ማለት ይቻላል።

የዝውውር ዜና

ሠርጂዮ አጉዌሮ ለባርሴሎና መፈረሙ ዛሬ ተረጋግጧል። ከማንቸስተር ሲቲ ጋር የገባው ውል የተጠናቀቀው ሠርጂዮ አጉዌሮ ለባርሴሎና የፈረመው በ122 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ነው።  የ32 ዓመቱ አርጀንቲናዊ አጥቂ ለባርሴሎና የፈረመው ለሁለት ዓመታት ነው። ሉዊስ ሱዋሬዝ ወደ አትሌቲኮ ማድሪድ ካቀና በኋላ በአጥቂ እጦት የለተቸገረው ባርሴሎና የሠርጂዮ አጉዌሮ ወደ ቡድኑ መምጣት ታላቅ የምሥራች ነው።  በሌላ ዜና የሪያል ማድሪዱ ተከላካይ ሰርጂዮ ራሞስን ለሁለት ዓመት ለማስፈረም ማንቸስተር ሲቲ ጫፍ መድረሱ ተዘግቧል። የ35 ዓመቱ ተከላካይ ሳንቲያጎ በርናቤው ውስጥ ውሉ የማይታደስ ከኾነ ማንቸስተር ሲቲ ሊጠልፈው ተዘጋጅቷል። ሰርጂዮ ራሞስ ከሪያል ማድሪድ ጋር የገባው ውል ተጠናቋል። ውሉ ለአንድ ዓመት እንዲራዘመለት ተጠይቆም ፈቃደኛ ሳይሆ ን ቀርቷል።

Bildergalerie | Fussballer vor dem Wechsel 2021
ምስል Darren Staples/imago images

በሌላ ዜና ዘንድሮ በጀርመን ቡንደስሊጋ 16ኛ ኾኖ በመጨረሱ ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ለመውረድ ስጋት ውስጥ የነበረው ኮሎኝ ቡድን ድል አድርጎ በቡንደስሊጋው ቆይቷል። ኮሎኝ በሁለተኛ ዲቪዚዮኑ ሦስተና ኾኖ ከጨረሰው ሆልሽታይን ኪይል ቡድን ጋር በመልሱ ጨዋታ 5 ለ1 ድል አድርጎ በቡንደስሊጋው መቆየት ችሏል። ቡድኑን የገጠመው የገንዘብ ችግር ግን ጣጣው በሚቀጥለው የጨዋታ ዘመንም ተከትሎት መኼዱ አይቀርም። ከቡንደስሊጋው ቬርደር ብሬመን እና ሻልከ 17ና እና 18ኛ ኾነው ሲሰናበቱ ቦኹም እና ግሬውተር ፊዩርትከሁለተኛ ዲቪዚዮን ተክተዋቸዋል።

የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለቀጣይ የአውሮጳ እግር ኳስ ግጥሚያ አጥቂው ቶማስ ሙይለር እና ተከላካዩ ማትስ ሁመልስን ጠርቷል። ሁለቱ የረዥም ጊዜ ልምድ ያካበቱ ተጨዋቾች ላለፉት ሁለት ዓመታት ከቡድኑ ተቀንሰው ነበር። በቅርብ የሚሰናበቱት የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣን ዩርጊ ሎይብ በተደጋጋሚ በደረሰባቸው ሽንፈት እና በበርካቶች ውትወታ ሁለቱ ልምድ ያላቸው ተጨዋቾች ቡድኑን ይቀላቀላሉ።  የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ከዴንማርክ ቡድን ጋር ከነገ በስተያ የወዳጅነት ግጥሚያውን ያደርጋል። ለቀጣዩ ውድድር ከቡድኑ ጋር ልምምዳቸውን የጀመሩት ሁለቱ ተጨዋቾች ከወዲሁ ብዙ ይጠበቅባቸዋል።   

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ