1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋምቤላ የት/ቢሮ በአማራ ክልል ለወደሙ ት/ቤቶች የሰጠዉ ርዳታ

ሰኞ፣ ጥር 16 2014

የጋምቤላ ክልል ትምህርት ቢሮ በአማራ ክልል በጦርነት ለተጎዱ ትምህርት ቤቶች ድጋፍ የሚውል ድጋፍ አደረገ፣ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊና የማንጅመንት አባላት ዛሬ ድጋፉን ባሕር ዳር በመገኘት ለአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስረክበዋል፡፡

https://p.dw.com/p/460Qn
Äthiopien | Tigray Konflikt | Zerstörung durch militante Tigray Gruppen
ምስል Alemenew Mekonnen/DW

በአማራ ክልል ከ4ሺህ 100 በላይ ትምህርት ቤቶች ወድመዋል ተዘርፈዋል

የጋምቤላ ክልል ትምህርት ቢሮ በአማራ ክልል በጦርነት ለተጎዱ ትምህርት ቤቶች ድጋፍ የሚውል ድጋፍ አደረገ፣ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊና የማንጅመንት አባላት ዛሬ ድጋፉን ባሕር ዳር በመገኘት ለአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስረክበዋል፡፡ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በበኩሉ ሌሎች ክልሎችም ድጋፍ ንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ከነበረው ጦርነት ጋር ተያይዞ በአማራ ምስራቃዊ ዞኖች በርካታ ትምህርት ቤቶች ወድመዋል ተማሪዎችና መምህራንም ተፈናቅለዋል፡፡ በቁሳዊ ንብረት ላይ የወደመውን ሀብት ለመመለስ አንዳንድ አካላት ድጋፍ ማድረግ ጀምረዋል፡፡

የጋምቤላ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሴ ጋጂትና የስራ ባልደረቦቻቸው ዛሬ ባሕር ዳር በመገኘት ለአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ እርዳታ ስጥተዋል፡፡ ዛሬ የተደረገው ድጋፍ የተማሪ ዩኒፎርሞችንና ጥሬ ገንዘብ እንደሚያካትት ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ ሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርጉና የፈረሱ ትምህርት ቤቶችን መልሶ መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ነው ቢሮ ኃላፊው ያሳሰቡት።፡ ጦርነቱ ብዙ ጥፋቶችና ግፎች የታዩበት ቢሆን ያልታሰበ ጠነከራ አንድነትን በህዝቦች መካከል መፍጠሩን አቶ ሙሴ ተናግረዋል፡፡

Äthiopien | Tigray Konflikt | Zerstörung durch militante Tigray Gruppen
ምስል Alemenew Mekonnen/DW

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙላው አበበ ህወሓት በርካታ ውድመቶችን በትምህርት ቤቶች ላይ ማድረሱን ዘርዝረዋል፡፡ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት አቶ ሙላው፣ የተደረገው ድጋፍ በአግባቡ ስራ ላይ እንደሚውል ጠቁመው ሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ በጦርነቱ ምክንያት ከ4ሺህ 100 በላይ ትምህርት ቤቶች መዘረፋቸውን፣ መውደማቸውንና መበላሸታቸውን፣ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች ትምህርት ማቋረጣቸውን፣ 116 ሺህ በላይ መምህራን ለተለያዩ ችግሮች መዳረጋቸውን ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ