1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ 30 አባላቱ መታሰራቸውን አስታወቀ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 6 2012

የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ 30 አባላቱ ያለ ክስ ለረዥም ጊዜ በእስር ላይ ቆይተዋል ሲል ከሰሰ። ክልሉን የሚመራው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢሳቅ አብዱል ቃድር ግን በተለያዩ ጊዜያት የክልሉ መንስግት ህግን የማስከበር ተግባር በሚያከናውንበት ወቅት የሚቀርቡ የተለመደ ቅሬታ ነው ብለዋል።

https://p.dw.com/p/3T9ge
Asosa, West-Äthiopien und Hauptstadt der Region Benishangul-Gumuz
ምስል privat

የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ክስ

የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ በክልሉ የተለያዩ ዞኖች 30 የሚደርሱ አባላቱ ያለምንም ፍርድ ታስረው እንደሚገኙ አስታወቀ።  በካማሺ፣ አሶ እና መተከል ዞኖች አባላቱን ጨምሮ 310 ዜጎች ታስረው ከአንድ ዓመት በላይ መቆየታቸውን የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ግራኝ ጉዴታ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ በ2006 ዓ.ም  በምርጫ ቦርድ እውቅና አግኝቶ  በቤኒሻንል ጉሙዝ ክልል የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ድርጅት ነው።  ከ2010 ዓ.ም መጨረሻ አንስቶ በካማሺ አሶሳ  እና መተከል ታስረው የሚገኙ አባሎቹ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ግራኝ ጉዴታ ተናግረዋል። በካማሺ፣መተከል እና አሶሳ ዞን አባሎቻቸውን ጨምሮ ከ300 በላይ ዜጎች የሀገሪቱን ህገ መንግስት በጣሰ መልኩ ያለምንም ፍርድ ታስረው እንደደሚገኙ አክለው ገልጸዋል።   

የክልሉ መሪ ድርጅት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሰዎቹ የታሰሩት በክልሉ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ተሳትፈዋል በመጠርጠራቸው መሆኑን አስታውቋል።  የቤጉህዴፓ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢሳቅ አብዱል ቃድር በተለያዩ ጊዜያት የክልሉ መንስግት ህግን የማስከበር ተግባር በሚያከናውንበት ወቅት የሚቀርቡ የተለመደ ቅሬታ መሆኑን ተናግረዋል።  በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ከመወነጃጀል ይልቅ በትብብር በመስራት ክልሉን በልማት የማሳደግ ተግባር ላይ መሳተፍ አለባቸው ብለዋል።

 በወንጀል  ድርጊት ተጠርጥረው በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች ያሉ ዜጎች የክስ ሂደተ መጓተት መኖሩንና በክልሉ ተፈጥሮ ከነበረው ግጭት ጋር ተያይዞ  የአብዛኛቹ ተጠርጣዎች ጉዳይ በፌደራል መርማሪ ቡድን ሲታይ መቆየቱን  የቤኒሻንል ጉሙዝ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ጠቅላይ ዐቃቢ ህግ የልዩ ልዩ ወንጀልና ታክስ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ከማል አብዱል ጀለል በተጠቁሱት አካባቢዎች  ክስ ሳይመሰረትባቸው ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች እንዳሉ በመጥቀስ በፍርድ ሂደት ክፍተቶች መኖራቸውን አረጋግጠዋል።

ነጋሳ ደሳለኝ

እሸቴ በቀለ