1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጉሊሶ ወረዳ ከጅምላ ግድያ በኋላ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 24 2013

በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ ከደረሰው የጅምላ ግድያ በኋላ አሁንም  በአካባቢዉ የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ስጋት ላይ እንደሚገኙ ለዶይቸ ቬለ ገለፁ።ነዋሪዎቹ እንደሚሉት በአካባቢው «ልዩ ሀይል» ቢሠፍርም ነዋሪዎቹ ሊረጋጉ አልቻሉም። የሟች እና የቆሰለው ሰው ቁጥርም ትናንት ከተገለፀው እንደሚበልጥ ነዋሪዎቹ አስታዉቀዋል።

https://p.dw.com/p/3kobE
Karte Sodo Ethiopia ENG

ባለፈዉ ዕሁድ በርካታ ሠላማዊ ሰዎች በታጣቂዎች በተገደሉበት በጉሊሶ ወረዳ ልዩ ሀይል መስፈሩን የገለፁልን አንድ የአካባቢው ነዋሪ እንደሚሉት ህዝቡ አሁንም በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ይገኛል። «ነፍጠኛ ናቸው እነዚህ እየተባለን ነው» ልንረጋጋ አልቻልንም ይላሉ። ልዩ ኃይሉ ታጣቂዎቹን ለማሰስ ጫካ ገብቷል የሚሉት እኚሁ የአካባቢ ነዋሪ በተለይ የአማራ ተወላጆች ዛሬም የተገደሉባቸውን ሰዎች እየቀበሩ እና የቆሰሉትንም እያስታመሙ ይገኛል። እሳቸው እንደሚሉት እስከ ዛሬ ቀትር ድረስ  60 ሰዎች ተቀብረዋል ከ 20 እስከ 30 የሚሆኑ ደግሞ ቆስለዋል።

አስክሬንም ገና እያሰባሰቡ ነው።  ኦነግ ሸኜ የተባለው ቡድን እሁድ ዕለት ከምሽቱ 11 ሰዓት ተኩል አካባቢ እንደሰበሰባቸው እና በሟቾች ላይ ተኩስ እንደከፈተ የገለፁልን ሌላው የአካባቢ ነዋሪ ደግሞ « አንድ ቦታ ላይ ትምህርት ቤት ውስጥ አስገቧቸው እና በቦንብ አጠቋቸው። » ሴቶችን እና ልጃገረዶችን ደግሞ ጫካ ውስጥ እየወሰዱ ደፍረዋል ይላሉ።

ከዚህም ሌላ ቤት እና ንብረት አጥፍተዋል የሚሉት እንኚሁ ሰው መንግሥት ያለውን ችግር እያወቀ፣ የመከላከያውን ሠራዊቱን ከአካባቢው ማስወጣት አልነበረበትም ሲሉ ይወቅሳሉ። ከሁለት ሳምንት በፊትም በአሰቃቂ ሁኔታ አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት እና ባለቤቷ ላይ ግድያ መፈፀሙን ገልፀውልናል። ይህ ሁሉ የሚፈፀመው ሙሉ ትጥቅ በታጠቁ ሰዎች ነው። 

ጥቃቱ በተፈፀመበት አካባቢ የሚኖሩ የበርካታ ሰዎች ስልክ አይሰራም።  የአይን እማኞች እንደሚሉን ከሆነ ሰዎቹ ለስብሰባ በተጠሩበት ወቅት ስልካቸውን ስለተቀሙ ሊሆን ይችላል። «እሩጫ የሚችሉ እና አንዳንድ ልጆች ናቸው እንጂ አብዛኞቹ ስልክ ተቀምተው ነው ያሉት» ሲሉ ያክላሉ።

በምዕራብ ብቻ ሳይሆን ምስራቅ ወለጋ አሙሩ በተባለችው ወረዳም ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ሰዎች እየተለዩ በማንነታቸው እየተገደሉ እንደሆነ ሌላው ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን እንድንገልፅ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪ ገልጸውልናል። ታጣቂዎች በሰነዘሩት ጥቃት ወንድማቸውን እንዳጡም ነግረውናል። « ታፍነን ነው ያለነው። ዙሪያውን እነሱ ናቸው»

ጥቃት ፈፃሚው ኦነግ ሸኔ የተባለው ታጣቂ ኃይል ይሁን አይሁን ርግጠኛ ባይሆኑም ጥቃት ፈፃሚዎቹ ኦሮምኛ የሚናገሩ ሰዎች ናቸው ሲሉ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።እናት እና አባቴ ናቸው እንጂ ከጎጃም የመጡት እኔ እዚህ ነው ተወልጄ ያደኩት የሚሉት እኝሁ የምስራቅ ወለጋ ነዋሪ ብዙ ሰዎች በስጋት የተነሳ እቤታቸው እንደማያድሩ ገልፀውልናል።  በአማራ ብሔር ላይ ያተኮረ ጥቃት  ከዚህ በፊትም ሻሸመኔ፣ በደቡብ ክልል ጉራ ፈርዳ ወረዳ እና መተከል ላይ ጥቃት የተሰነዘረባቸው ሰዎች በተደጋጋሚ ሲገልፁ መሰማቱ ይታወሳል።

ልደት አበበ

ነጋሽ መሀመድ