1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን የጦር መሣሪያ በየመን ጦርነት

ሰኞ፣ የካቲት 25 2011

ጀርመን ሠራሽ ወታደራዊ ጦር መሣሪያዎች ለበርካቶች ሞት እና ለሚልዮኖች መፈናቀል መንስኤ በሆነው በየመኑ ደም አፋሳሽ ጦርነት ጥቅም ላይ መዋላቸውን የDW ጋዜጠኞችን ጨምሮ በጀርመን እና በሌሎች የአውሮጳ ሃገራት ለሚገኙ መገናኛ ብዙሃን የሚሰሩ ባለሞያዎች በዝርዝር አጋልጧል።

https://p.dw.com/p/3EQyI
DW Exclusive Deutsche Waffen in Jemen SPERRFRIST 26.02.2019 20 Uhr Oshkosh-Kampffahrzeuge mit Fewas-Waffenstation
ምስል EPA-EFE/REX/Shutterstock/N. Almahboobi

የጀርመን የጦር መሣሪያ በየመን ጦርነት

የፕሬዚዳንት አብዱ ራቡ መንሱር ሃዲ መንግሥትን በመደገፍ የሑቲ አማጽያንን ለመውጋት የመን የከተመው ሳውዲ መራሹ ጥምር ጦር እንደ ጎርጎራውያኑ ከ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአገሪቱ ወታደራዊ ጥቃት ከከፈተ ወዲህ ከ 60 ሺህ በላይ የመናውያን የጦርነቱ ሰለባ መሆቻቸው ታውቋል። በእርስ በእርስ ግጭት የምትናጠው የመን ከ28 ሚልዮን ዜጎቿ ገሚሱ ካለፈው አንድ ምዕተ ዓመት ወዲህ ታይቶ አይታወቅም በሚባል ጠኔ እየተሰቃየ ይገኛል።

አብዛኛው ሕዝብ በአሁኑ ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ቢገለጽም መተላለፊያ መንገዶች ሳይቀሩ የጦር ዓውድማ በመሆናቸው ሕይወት በማዳኑ ስኬት ላይ ትልቅ ማነቆ ፈጥሯል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎቿም በጤና አገልግሎቱ ዘርፍ መዳከም በምግብ እና ንጹህ የመጠጥ ውሃ እጥረት እንዲሁም በንጽህና ጉድለት ሳቢያ ለኮሌራ እና ሌሎችም ተላላፊ የጤና ወረርሽኞች ተጋልጠው በየዕለቱ እንደ ቅጠል እየረገፉ ነው። 

የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ አምና ባወጣው ዘገባ ባለፉት 3 የመከራ ዓመታት ዕድሜያቸው ከ 5 ዓመት በታች የሆኑ ከ 85 ሺህ በላይ ሕጻናት በተመጣጣኝ ምግብ እጥረት እና በረሃብ ምክንያት ገና በለጋ ዕድሜያቸው ሲቀጩ ከ 400 ሺህ የሚልቁ ሌሎች ሕጻናትም ሕይወት አሁንም አደጋ ላይ መውደቁን አስታውቋል። አሉ የተባሉ የምድራችን ዘመን አፈራሽ የጦር መሳሪያዎች መሞከሪያ የሆነችው የመን ሰቆቃ ዛሬም አላባራም:: አገሪቱ በመጀመሪያው ረድፍ ሚልዮኖች የሚሰደዱባት እና የሚፈናቀሉባት የምድር ሲዖል ሆናለች ሲሉ ታዛቢዎች ይገልጻሉ።

Bildergalerie Jemen Binnenflüchtlinge
ምስል Reuters/K. Abdullah

የDW የምርመራ ዘገባው ረዳት አዘጋጅ ናኦሚ ኮንራድ ከባልደረቦቿ ጋር ባደረገችው ቃለ መጠይቅም ይኸው ዕውነታ ነበር የተንጸባረቀው:: "ሳውዲ መራሹ የጦር ኃይል ዛሬ በሰላማዊ ሰዎች እና በማሕበራዊ ተቋማት ላይ እያደረሰ ያለው አስከፊ የቦምብ ጥቃት እና ውድመት በገንዘብ ሃብት የማይተመን እንዲሁም ምርጥ የጦር መሳሪያ ባለቤት ከመሆንም በላይ ነው" ሲል ነበር የዘጋቢው ቡድን ባልደረባ የገለጸው።

ዩናይትድ ስቴትስ ብሪታንያ ጀርመን እና ሌሎችም ምዕራባዉያን መንግሥታት የመን ዉስጥ ውጊያ ለሚያካሂዱ የአረብ ሐገራት እጅግ አደገኛ የሚባሉ የጦር መሳሪያዎችን ጭምር መሸጣቸውን ዓለማቀፉ ማህበረሰብ በተደጋጋሚ ሲያወግዘው የቆየ ጉዳይ ነው። በተለይም እነዚህን መሳሪያዎች በየመን የከተሙት ሳውዲ መራሹ ኃይላት በእጅ አዙር በአገሪቱ ለሚንቀሳቀሱ እና በጦር ወንጀለኝነት ለሚጠረጠሩ አደገኛ ለሚባሉ ሚሊሻዎች አሳልፈው የመስጠታቸው ጉዳይ እንደ አምንስቲ ኢንተርናሽናል ባሉ ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ጭምር ክፉኛ ተነቅፏል።

ሪያድና አቡዳቢ የጦር መሳሪያ እና ገንዘብ ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት ላለዉ ቡድን ለመስጠት ከቡድኑ መሪዎች ጋር መስማማታቸው ይፋ መሆኑም በቀጣናው ሌላ ተጨማሪ ሥጋትን የፈጠረ ጉዳይ ሆኗል። በተለይም በቅርቡ በእርስ በእርስ ጦርነት ለሚካፈሉ አገራት የጦር መሳሪያ ሽያጭን የሚከለክለውን ዓለም አቀፍ ሕግ በመጣስ የጀርመን ኩባንያዎች ለሳውድ አረቢያ እና ለተባበሩት አረብ ኢምሬቶች የጦር መሳሪያዎችን እና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን በገፍ የመሸጣቸው ተጨባጭ መረጃ ይፋ መሆኑ በዓለማቀፉ ማህበረሰ እና በሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጭምር ከፍተኛ መነጋገሪያ ርዕስ ከመሆን አልፎ ለዜጎች ሰብአዊ መብት እቆረቆራለሁ በምትለው ጀርመን ላይ ውግዘትን አስከትሏል።

Infografik Deutsche Waffentechnik im Jemenkrieg EN

የDW ጋዜጠኞች የታዋቂው የጀርመን መጽሄት ሽተርን እና የባየሪሸር ሩንድ ፉንክ ዘጋቢዎች ለተለያዩ የአውሮጳ አገራት መገናኛ ብዙሃን የሚሰሩ ባለሙያዎች እንዲሁም የደች የምርመራ ቢሮ እና ዓለማቀፉ የቤሊንግካት ዕውቅ የወንጀል ምርመራ ተቋም ጭምር ይፋ ያደረጉት ይኸው የምርመራ ዘገባ በጀርመን የተመረቱ የጦር መሳሪያዎች ለበርካቶች ሞት እና ለሚልዮኖች መፈናቀል መንስኤ በሆነው በየመኑ ደም አፋሳሽ ጦርነት መሳተፋቸውን በዝርዝር አጋልጧል።

በተለይ በ DW የምርመራ ዘገባ ከአንድ ሳምንት በፊት በኢምሬቶች ከ 1200 በላይ ዓለማቀፍ ድርጅቶች ዘመን አፈራሽ የጦር መሳሪያ ምርቶቻቸውን ያስተዋወቁበት ግዙፉ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት የመከላከያ ኃይል ቴክኖሎጂ የንግድ ትርዒት መካሄዱ በአብነት ጠቅሷል። በዚሁ በኢምሬቶች በተዘጋጀው ተሻሽለው የተሰሩ እና እጅግ የረቀቁ ዘመን አፈራሽ የጦር መሳሪያዎች እና ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች በተዋወቁበት ዓለማቀፍ ኤግዚቢሽን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጀርመን ድርጅት ወኪሎች ምርቶቻቸውን በማስተዋወቅ ተካፋይ ሆነዋል።

በወቅቱም የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች መንግሥት ለዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ግዥ እና ለወታደራዊ ቴክኖሎጂው ሽግግር ከ 4 ቢልዮን ዶላር በላይ ከአሜሪካ እና አውሮፓ የጦር መሳሪያዎች አምራች ድርጅቶች እንዲሁም ከብሔራዊ እና ዓለማቀፋዊ ኩባንያዎች ጋር ውሎችን መፈራረሙ ነው የተገለጸው።ኢምሬቶች የጀርመንን የጦር መሳሪያዎች ከሚሸምቱ አገራት ግንባር ቀደም መሆኗም በዘገባው ተመልክቷል። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ መረጃ ይፋ በሆነበት ሁኔታ የጀርመን መንግሥት የመን ላይ ዘመቻ በከፈቱት እና በከፍተኛ ሰብአዊ መብት ጥሰት በሚከሰሱት የሳውድ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ወታደሮች እንዲሁም በወንጀል በሚፈለጉ አማጽያን ጭምር ወታደራዊ ምርቶቹ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው ተብሎ የሚቀርብበትን ክስ እና ወቀሳ አሁንም እያስተባበለ ይገኛል። 

DW Exclusive Deutsche Waffen in Jemen SPERRFRIST 26.02.2019 20 Uhr IDEX Waffenmesse
ምስል DW/T. Hasel

በደቡባዊ የመን ግዛት ሑቲ አማጺያንን ለመውጋት የመን ላይ የዘመተው የሳውድ አረቢያን ኃይል ለመደገፍ በባብ ኧል ማንዳብ የባሕር ወሽመጥ አድርገው ከሱዳን የመጡ ቅጥረኛ ወታደሮች መኖራቸው በምርመራ ዘገባው ላይ ተመልክቷል። በጎርጎርጎሪዮሳዊው 2015ዓ.ም. የአሶሲየትድ ፕረስ ዘጋቢ በየመኗ የወደብ ከተማ ኤደን የቀረፀው ፊልምም ወታደራዊ ዩኒፎርም ከለበሱ የሱዳን ቅጥረኛ ወታደሮች ሌላ ንብረትነታቸው የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የሆኑ ታንኮችንም ጭምር የሚያሳይ ነበር። ታንኮቹ ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ እና ጀርመን ሠራሽ መሆናቸውም ተረጋግጥጧል።

የጀርመኑ የጦር መሳሪያዎች ማምረቻ የመከላከያ ፋብሪካ ዳይናሚት ኖቤል የ81 ሚሊኒየን ዩሮ ምርቱን የጦር ተሽከርካሪዎችን እና መለዋወጫዎችን ጭምር የመን ውስጥ የሰፈረውን የእግረኛ ጦር ለምትመራው ኤሜሬትስ የመላክ ፈቃዱን ከፌደራል መንግሥቱ ያገኘው የዛሬ 10 ዓመት ነው። የጀርመን የጦር መሳሪያዎች ሽያጭ ደንብ ራስን ለመከላከል ከሚረዱ የመሳሪያዎች ሽያጭ ውል ውጭ በእርስ በእርስ ግጭት እና ጦርነት ውስጥ ለሚገኙ ቡድኖች ወይም ሃገራት ቀውስን ለማባባስ የሚደረግ ሽያጭን ይከለክላል:። ሆኖም ጀርመን በየመን የእግረኛውን ጦር ውጊያ ለምትመራው ኢምሬቶች 126 ሚልዮን ዶላር የሚያወጡ ለአየር ለምድር እና ለባሕር ውጊያዎች ጭምር የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ የጦር መሳሪያዎችን ፈንጅ አምካኝ ተሽከርካሪዎችን እና ታንኮችን ጭምር መሸጧ ታውቋል። 

ይህን መረጃ መሰረት በማድረግም ለመሆኑ «የጀርመን የጦር መሣሪያ በየመን ጦርነት ውስጥ ገብቷል ወይ?» በሚል DW በሙኒኩ የፀጥታ ጉባኤ ላይ ጥያቄ ያቀረበላቸው የጀርመን የኤኮኖሚ ሚኒስትር ፒተር አልትማየር ጠይቋቸው ነበር:: እሳቸውም «የማውቀው ነገር የለም፤ በጥምር መንግሥታችን በቀጥታ እና ወዲያው በየመን ግጭት ውስጥ ጣልቃ ለገቡ ወገኖች ወታደራዊ መሣሪያዎች እንዳይሸጡ እጅግ ገዳቢ መመሪያዎችን አውጥተናል። ይህ ተግባራዊ እየሆነ ነው፤ እሱን በተመለከተ አዲስ ነገር አልሰማሁም» ሲሉ ነበር መልስ የሰጡት።

DW Exclusive Deutsche Waffen in Jemen SPERRFRIST 26.02.2019 20 Uhr VAE Soldaten Rückkehr
ምስል picture-alliance/dpa/EPA/ENA

የኤኮኖሚ ሚኒስትሩ መሣሪያዎቹ ለጦርነት እንደሚውሉ አለማወቃቸውን ለመግለጽ ቢሞክሩም እንደሳውድ አረቢ እና ኤሜሬትስ ያሉት ሃገራት ከጎርጎሪዮሳዊው 2015ዓ,ም ጀምሮ የጀርመንን የጦር መሣሪያዎች ሲሸምቱ ለመቆየታቸው ልዩ ልዩ ሰነዶች አረጋግጠዋል። ባለፈው ዓመት የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራትም የጀርመን የፌደራል ደህንነት መስሪያቤት እና የተለያዩ ሚኒስትሮች ለሳውድ አረቢያ 416 ሚልዮን ዩሮ ግምት ያለው የጦር መሳሪያ ሽያጭ ውልን የሚያጸድቅ ምስጢራዊ ውይይት ማድረጋቸው እንዲሁም ከጥቅምት እስከ ታህሳስ ባሉት ወራትም በተመሳሳይ ከኢምሬትቶች ጋር የ40 ሚልዮን ዩሮ የጦር መሳሪያዎች ሽያጭ ውል መደረጉ በምርመራ ዘገባው ላይ ተመልክቷል።

ባለስልጣናቱ እንዲህ በማስረጃ ተደግፎ የሚቀርብባቸውን ክስ ያስተባብሉ እንጂ የጀርመን የጦር መሣሪያ አምራች ኩባንያ ምርቶች ፎቶግራፎች እና የቪዲዮ ምስሎች በኢንተርኔት ማለትም በትዊተር፤ በዩቲዩብ እና በጉግል ኧርዝ ምስጢራዊ መረጃዎቹ ተሰራጭተው ይገኛሉ። የጀርመን ጦር መሣሪያዎች ላይ ምርመራ ያካሄዱ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እና ተንታኞችም ጦር መሣሪያዎቹ በየመኑ ጦርነት በምድር፣ በአየር እና በባሕር መሳተፋቸውን የሚያሳዩ በርከት ያሉ መረጃዎችን ማግኘታቸውን አስታውቀዋል። 

ከዚህ ሌላ የ DW የምርመራ ዘገባ በጀርመን መከላከያ ተቋም ስር በሚገኘው የራየን ብረታብረት እና ተሽከርካሪዎች ማምረቻ ኢንዱስትሪ የተፈበረኩ የጀርመን ቴክኖሎጂ ስሪት ከባድ የጦር ተሽከርካሪዎችንም በየመን አደባባይ ሲዘዋወሩ ማየቱን ጠቁሟል። ባለፈው ዓመት አረብ 24 በተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ በየመን የባህር ሰርጥ ሳውዲ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው እና የሳውዲ ጦር ተደጋጋሚ የአየር ጥቃት በፈጸመባት የሁቲ ሸማቂዎች ጠንካራ ግዛት የአል ካሃውክሃ መንደር ጀርመን ሰራሽ የጦር ተሽከርካሪዎችን የሚያሳይ የቪድዮ ምስል መሰራጨቱም ለማመሳከሪያነት ቀርቧል። 

DW Exclusive Deutsche Waffen in Jemen SPERRFRIST 26.02.2019 20 Uhr Hafen von Assab, Eritrea

ከየመን በ 60 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው የኤርትራዋ አሰብ ወደብም እንዲሁ ሳውዲ መራሹ ጦር በየመን ለከፈተው ጦርነት የዘመቻ ጣቢያ ሆናለች። ከዚህ ስፍራ የሚነሱት የአረብ ኤሜሬቶች የጦር መርከቦች ወደ ኤደን ወደብ በቀላሉ ፈጥነው መድረስ የሚያስችላቸው ሲሆን ለጦርነት ግዳጅ የሚፈለጉ ቅጥረኛ ወታደሮችም በወደቡ አማካኝነት ወደ የመን እንዲገቡ በኤሜሬቶች እና በኤርትራ መካከል ስምምነት መደረጉንም የተመድ አመልክቷል። ድርጅቱ በጎርጎሪዮሳዊው 2009 ዓ,ም በኤርትራው ፈላጭ ቆራጭ መንግሥት ላይ የጣለውን የመሣሪያ ማዕቀብ ተጥሷል ብሎም ሲተች ቆይቷል። 

እገዳው ግድ ያልሰጣት ኤሜሬትስ ግን ጀርመን ሠራሽ የጦር መርከቦቿን በአሰብ ወደብ ላይ ማጓጓዟን የሳተላይት የፎቶ ምስሎች ያሳያሉ። ሮኬት የተጠመደባቸው የጦር መርከቦች ብሬመን በሚገኝ የጀርመን ኩባንያ የተሠሩ እና 65 ሜትር ርዝመት ያላቸው ናቸው ተብሏል። አልጃዚራ ቴሌቪዥንም በጎርጎሪዮሳዊው 2017 ጥቅምት ወር ዘገባው የየመኗ ሞካ ወደብ በሳውዲ መራሹ ጥምር ኃይል ቁጥጥር ሥር መቆየቷን አመልክቷል። በዚህ ወቅትም በያዝነው ዓመት ጥር ወር ላይ የመን ውስጥ የተከሰከሰው ቶርኔዶ ተዋጊ ጀትን ጨምሮ የተለያዩ አውሮጳ ሃገራት እና የጀርመን የጦር መሣሪያዎች ለውጊያ ተግባር መዋላቸው ፍንጭ የሚሰጡ መረጃዎች ተገኝተዋል። የተዋጊ ጀት ነዳጅ ይሞሉ የነበሩ በግዙፉ የአውሮፕላን ማምረቻ ድርጅት የሚመረቱ የኤርበስ ምርቶችም እንዲሁ ጀርመን ሠራሽ አካላት የተገጠሙላቸው አውሮፕላኖች መሆናቸውንም ምርመራው አመላክቷል። 

እንዲህ ትችት እና ክሱ ባየለበት በአሁኑ ወቅት የጀርመን ወታደራዊ ምርቶቹ ለጦርነት በመዋላቸው ብቻ ጀርመን በቀጥታ በጦር መሣሪያ ንግዱ ተሳትፋለች ማለት አይቻልም በሚል የሚከራከሩ አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ጀርመን ስልታዊ ወዳጅ አድርጋ ከምትወስዳቸው ሳውዲ እና አረብ ኤሜሬቶች ጋር የጦር መሳሪያ ንግድ ውስጥ መግባቷ በራሱ በቀጥታ በየመን ጦርነት እጇን ያስገባች አስመስሏታል ሲሉ የሚተቹም ጥቂት አይደሉም። 

የፌደራል ጀርመን ተጣማሪ መንግሥት በየመን ጦርነት ለሚሳተፉ ሃገራት የጦር መሣሪያ እንዳይሸጥ ቢደነግጉም የሳውዲው ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ኢስታንቡል ውስጥ እስከተገደለበት ጊዜ ድረስ ውሳኔው ተግባራዊ እንዳልሆነ ነው የሚነገረው:: ይህ እገዳ የፊታችን መጋቢት ወር መጀመሪያ ቀናት እንደሚያበቃ ታውቋል። ከኤሜሬቶች ጋር ካለፈው ጥቅምት እስከ ታኅሳስ ወር በተደረገው ስምምነት ከ40 ሚሊየን ዩሮ በላይ የሚያወጣ የባሕር ኃይል መከላከያን የሚጨምረው የጦር መሳሪያ ሽያጭ ውል ግን አሁንም አልተቋጨም። 

የሰላም ኖቤል ተሸላሚው ታዋኮል ካርማን ጀርመን ለሳውዲ እና ለኤሜሬትስ መሣሪያ መሸጥ እንድታቆም ጥሪ አቅርበዋል። "ለሳውዲ አረቢያ እና ኢምሬቶች የሚሸጡ የጦር መሳሪያዎች በየመናውያን ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እና ተጽዕኖ እያስከተሉ ነው:: አገራቱ የመናውያንን ለመፍጀት እየተጠቀሙበት ነው።እናም ለሁሉም ምዕራባውያን ሃገራት እና መንግሥታት ለስውድ አረቢያ እና ኢምሬቶች የሚልኩትን የጦር መሳሪያ እንዲያቆሙ ጥሪዬን አቀርባለሁ" ብለዋል።

Royal Saudi Air Force Tornado IDS
ምስል imago/StockTrek Images

ሳዑዲ አረቢያ መራሹ ጦር ሰላማዊ ሰዎችን መግደሉንና ተቋማትን ማጥፋቱን በመቃወም ጀርመን፣ ኖርዌና ኔዘርላንድስ ለተባባሪዎቹ ሐገራት የሚሸጡትን ጦር መሳሪያ ለመገደብ እስከመወሰንም ቢደርሱም እስካሁን ውሳኔው ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም። ከዚህ ሌላ የጀርመን ፌደራል መንግሥት የተመድ የመንን ለመርዳት በሚያደርገዉ ጥረት 100 ሚሊዮን ዩሮ ያህል የገንዘብ ድጋፍ እንደሚሰጥ ቃል እየገባ በመንን ላይ ሰላምን በማስከበር ስም ጦርነት ከፍተው ከፍተኛ ሰብአዊ መብት ጥሰት በአገሪቱ ዜጎች ላይ ይፈጽማሉ ተብለው ለሚከሰሱ አገራት የጦር መሳሪያዎቹን መሸጡ ዛሬም ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሆኗል።

የጀርመን የካቶሊክ እና የወንጌላውያን አብያተክርስትያናት የጋራ ኮሚቴ በርሊን ላይ ባወጣው መግለጫ ዓለማቀፍ ስምምነትን በመጣስ በየመን ለደረሰው ሰብአዊ ቀውስ መንስኤ ሆኗል ያለውን የጦር መሳሪያ ሽያጭ ስምምነት ውል በጽኑ አውግዞ ጀርመን ከሳውዲ መራሹ ጦር ጋር ያላትን ትብብር እንድታቋርጥ ጠይቋል። አምኒስቲ ኢንተርናሽናል እና ሌሎችም የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶችም በየመን የሚገኘው በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች የሚመራው ኃይል በተለይም በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል ባቋቋማቸው ምስጢራዊ እስር ቤቶች በየመናውያን ላይ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደሚፈጽም ገልጸው ድርጊቱን አውግዘዋል። ተጣማሪው ኃይል በምድር እና በአየር በሚፈጽማቸው ተደጋጋሚ ጥቃቶች ሰላማዊ ዜጎች ትምህርትቤቶች መስጊዶች እና የህክምና ተቋማት ሳይቀሩ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ነው ያስታወቁት።  

DW በዛው በየመን ያነጋገራቸው እንዳንድ ነዋሪዎችም ለሰዓታት በገመድ ሰቅሎ በማንጠልጠል ድብደባ በመፈጸም እና በኤሌክትሪክ ንዝረት ሰውነትን መጥበስ ከፍተኛ ሰቆቃ እየተፈጸመባቸው አረጋግጠውለታል:: የሂውማን ራይትስ ዎች ምክትል ዳይሬክተር ኬንዝ ሮትም ለሳውዲ መራሹ ጦር የጦር መሳሪያዎችን በመሸጥ በየመን ለሚፈጸመው የሰብ አዊ መብት ጥሰት አባሪ ተባባሪ ሆነዋል ያሏቸውን ጀርመንን እና ሌሎችም የም ዕራባውያን መንግሥታት ወቅሰዋል።

እንዳልካቸው ፍቃደ 

ተስፋለም ወልደየስ