1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ሃላፊነት በአውሮጳ ህብረት ፕሬዝዳንትነት

ማክሰኞ፣ ሰኔ 16 2012

ኮቪድ 19 ለጎዳው የአውሮጳ ኤኮኖሚ ማገገሚያ የአውሮጳ ህብረት የ750 ቢሊዮን ዩሮ የገንዘብ እርዳታአቅርቧል።ይህም የአውሮጳ ምክር ቤትን ይሁንታ አግኝቷል።በገንዘቡ አከፋፈል ላይ ግን አባል ሃገራት በሙሉ አልተስማሙም። ገንዘብም ተሰሚነትም ያላት ጀርመን አባላቱን ማግባባትና ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ማድረግ ከጀርመን የሚጠበቅ አንዱ ተግባር ነው ።

https://p.dw.com/p/3eEZb
Deutschland | Bundeskanzlerin Angela Merkel hält eine Rede vor dem Bundestag in Berlin
ምስል Reuters/A. Hilse

የጀርመን ሃላፊነት በአውሮጳ ህብረት ፕሬዝዳንትነት

ጀርመን  በጎርጎሮሳዊው ሐምሌ አንድ 2020 በዙር የሚደርሰውን የአውሮጳ ህብረት የመሪዎች ምክር ቤት የፕሬዝዳንትነት ሃላፊነት ከክሮኤሽያ ትረከባለች።የአውሮጳ ግዙፍ ኤኮኖሚ አንቀሳቃሽ ጀርመን እስከ ታህሳስ 2020 የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት የሚያካሂዳቸውን ጉባኤዎች በሊቀ መንበርነት ትመራለች።የህብረቱን አጀንዳዎች ማስፈጸምና መርሃ ግብሮችንም ማስኬድ ከሃላፊነትዋ ውስጥ ይደመራሉ።ከዋነኛዎቹ ሃላፊነቶችዋ ውስጥም በአውሮጳ እንቅስቃሴን ይበልጥ ማዘመንና ፣ አስተማማኝ ማድረግ እንዲሁም ከኮቪድ 19 በሽታ ትምሕርት መውሰድ ይገኙበታል።ጀርመን በዚህ ጊዜ በተለይ አውሮጳ ከኮሮና ቀውስ ጠንክራ እንድታገግም  ይበጃሉ ያለቻቸውን መንገዶችንም ጠቁማለች። በተለይ የኮሮና ተህዋሲ ያስከተለው የጤና ቀውስ እንዳይባባስ ለመከላከል መሞከር ልዩ ትኩረት የምትሰጠው ጉዳይ መሆኑን  አስታውቃለች።የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ባለፈው ሳምንት ለጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሰሙት ንግግር እንዳሉት የኮሮና ወረርሽኝ እና በሽታውን ተከትሎ የተከሰተው የኤኮኖሚ ማሽቆልቆል አውሮጳ በታሪክዋ አይታው የማታውቀው ትልቅ ፈተና ነው።እናም አውሮጳ ከዚህ የጤና ቀውስ ልትላቀቅ የምትችለው ዜጎቿ ሲበለጽጉ እና አውሮጳም በዓለም ያላትን ሚናዋን ስታጎለብት መሆኑንም ሜርክል ተናግረዋል።በርሳቸው አባባል 27ቱ የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት ስኬታማ ሊሆኑ የሚችሉት በአንድ ላይ ሲቆሙ ብቻ እንደሆነ አሁን ከመቼውም በበለጠ ጠንካራ እምነት አላቸው።ጀርመን የዛሬ ሳምንት ረቡዕ በምትረከበው የህብረቱ የ6 ወራት የፕሬዝዳንትነት ሥልጣን ሜርክል ለሃገራቸው ምክር ቤት እንደተናገሩት ትኩረትዋ አውሮጳን ይበልጥ ማጠናከር ነው።ይህን ለማሳካትም የሃገራቸው የሕዝብ እንደራሴዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ተማጽነዋል።

Heiko Maas in Bulgarien
ምስል Imago Images/photothek/T. Imo

አውሮጳን ይበልጥ ማጠናከር የጀርመን የአውሮጳ ህብረት ፕሬዝዳንትነት ሃላፊነት ዋነኛው ዓላማ ነው። የጀርመን መንግሥት እና እኔ በጀርመን የፕሬዝዳንትነት ዘመን ባለን አቅምና ፍቅር ሁሉ ይህን ለማሳካት እንሰራለን።እናንተም ከኛ ጋራ እንድትሰሩ ድጋፋችሁን እጠይቃለሁ።ለአውሮጳ ያላችሁ ቁርጠኝነት የሚገባ መሆኑን አምንበታለሁ።በጣም አመሰግናለሁ።» 
«አውሮጳን በጋራ ዳግም ማጠናከር።»የስድስቱ ወራት የጀርመን የህብረቱ ፕሬዝዳንትነት ወቅት መሪ መፈክር ነው።የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይኮ ማስ ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳሉት አውሮጳን በጋራ ወደፊት ማስኬድ የጀርመን የስድስቱ ወራት ሃላፊነት ዐቢይ ትኩረት ነው።
«አሁን በአውሮጳ እጅግ አጣዳፊው ተግባራችን ጠንካራ ኤኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጅማሮን ማረጋገጥ ነው።ይህም ሐምሌ አንድ የሚጀምረው በጀርመን የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት የፕሬዝዳንትነት ሃላፊነት ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጠው «አውሮጳን በጋራ ዳግም ማጠናከር።» በትብብር የተቀረጸ አዲስ ጀብዱ የተሞላበት ጅማሮ እንዲሆን ነው የምንፈልገው።አንድም አውሮጳዊን ሃገር ወደ ኋላ ላለመተው ቆርጠናል።»
ጀርመን በዚህ ወቅት ላይ የአውሮጳ ህብረት ፕሬዝዳንትነት ሃላፊነትን መረከቧን ተንታኞች ጥሩ አጋጣሚ ይሉታል።ባለፈው ታህሳስ ከቻይና ተነስቶ መላውን ዓለም ያዳረሰው የኮሮና ተህዋሲ ጠንካራ የሚባሉትን የአውሮጳ ሃገራት ሳይቀር አንገዳግዷል።ኮቪድ ካደረሰው ጉዳት ለማገገም ድጋፍ የሚያሻቸው ሃገራት ጥቂት አይደሉም።ኮቪድ 19 ለጎዳው የአውሮጳ ኤኮኖሚ ማገገሚያ የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን የ750 ቢሊዮን ዩሮ የገንዘብ እርዳታ መርሃ ግብር አቅርቧል።በህብረቱ አባል ሃገራት የደረሰውን የጤና ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ለመታደግ የታሰበው ይህ የገንዘብ እርዳታ የአውሮጳ ምክር ቤትን ይሁንታ አግኝቷል።ሆኖም በገንዘቡ አከፋፈል ላይ ግን አባል ሃገራት በሙሉ አልተስማሙም።የብራሰልሱ ዘጋቢያችን ገበያው ንጉሴ እንደሚለው በዚህ ወቅት ላይ ታዲያ ገንዘብም ተሰሚነትም ያላት ጀርመን የፕሬዝዳንቱን ሃላፊነት መውሰዷ ብዙ ጥቅም ይኖረዋል።በተለይ አባላቱን ማግባባትና ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ማድረግ በጀርመን የህብረቱ ፕሬዝዳንትነት ወቅት የሚጠበቅ አንዱ ተግባር ነው የሚሆነው።

Symbolbild EU und Deutschland Flagge
ምስል AP

ኂሩት መለሰ