1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን - የአዉሮጳ ሙቀት

ዓርብ፣ ሐምሌ 19 2011

ምዕራብ አዉሮጳን የሚያነፍረዉ ሙቀት የሰዉ ሕይወት፣ጤናና እንቅስቃሴን አዉኮ ሰነበተ።ካለፈዉ ሮብ ጀምሮ አብዛኞቹን የምዕራብ አዉሮጳ ሐገራትን የሚለመጥጠዉ ሙቀት በርካታ ሰዎችን በተለይም አዛዉንትና ሕፃናትን ለተለያዩ በሽታዎች አጋልጧል። ሰሜን ምዕራብ ጀርመን ዉስጥ 42.6፣ ፓሪስ 42.6፣ ቤልጂግ 41.8 ዲግሪ ሴልሲየስ ተመዝግቧል።

https://p.dw.com/p/3Mnm9
Hitze in Europa
ምስል picture-alliance/dpa/N. Economou

ምዕራብ አዉሮጳን የሚያነፍረዉ ሙቀት የሰዉ ሕይወት፣ጤናና እንቅስቃሴን አዉኮ ሰነበተ።ካለፈዉ ሮብ ጀምሮ አብዛኞቹን የምዕራብ አዉሮጳ ሐገራትን የሚለመጥጠዉ ሙቀት በርካታ ሰዎችን በተለይም አዛዉንትና ሕፃናትን ለተለያዩ በሽታዎች አጋልጧል።ቤልጅግ ዉስጥ ዛሬ አንዲት የ66 ዓመት ባልቴት በግለቱ ምክንያት ሕይወታቸዉ አልፏል።ሙቀቱ ባቡሮችን፣ ማሺኖችን፤የመብራት፣ የኃይልና የመገናኛ መስመሮችን በማበላሸቱ የሰዎችን የዕለት ከዕለት ሥራና ጉዞ አጉሎታል።እዚሕ ጀርመን ዉስጥ የባቡር ማሽኖች በመበላሸታቸዉ ካንዱ ከተማ ወደሌላዉ የሚደረገዉ ጉዞ ከትናንት ጀምሮ ተደናቅፏል።የሐገሪቱ የምድር ባቡር ድርጅት የባቡሮች መነሻና መድረሻ ሰዓቶችን ለመቀየር ሲገደድ፣ የረጅም ርቀት ተጓዞች የጉዟቸዉን ጊዜ እንዲቀይሩ እየተማፀነ ነዉ።ከፓሪስ ወደ ብራስልስና ለንደን የሚጓዙ ባቡሮችም እስከ ዛሬ ቀጥር ድረስ ጉዟቸዉን አቋርጠዉ ነዉ የዋሉት። ሰዉ የአየር ፀባይን መመዝገብ ከጀመረ ከ150 ዓመት ወዲሕ ምዕራብ አዉሮጳ የሰሞኑን ያክል ግሎ አያዉቅም።
የተባበሩት መንግሥታት የሜትሪዮሎጂይ ድርጅት ቃል ቃል አቀባይ ክሌራ ነሊስ እንዳሉት የአየር ፀባይ ሪኮርድ በከፍተኛ ደረጃ ሲሰበር የዘንድሮዉ ለብቻዉ ነዉ።«አሳሳቢዉ ነገር፣በልማዱ የአየር ፀባይ ሪኮርድ የሚሰበረዉ ከአንድ ባነሰ ዲግሪ (ሴልሲየስ) ነዉ።ትናንት ያየነዉ ግን ሪኮርዱ በሁለት፣በሶስት እና በአራት ዲግሪ (ሴልሲየስ) ነዉ።ጭራሽ የማይታመን ነዉ።
 ትናንት ሰሜን ምዕራብ ጀርመን ዉስጥ 42.6፣ ፓሪስ 42.6፣ ቤልጂግ 41.8 ዲግሪ ሴልሲየስ ተመዝግቧል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለዉ የምዕራብ አዉሮጳ የሙቀት መጠን ዘንድሮ የናረዉ አጠቃላዩ የአየር ንብረት በመለወጡ ነዉ።ነገና ከነገ ወዲያ ቀዝቀዝ ይላል ተብሏል።

 

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ