1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ፣አፍሪቃና ዩናይትድ ስቴትስ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 11 2014

ጀርመንም ሆኑ ሌሎቹ የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት አፍሪቃ ዉስጥ መዋዕለ ነዋያቸዉን ማፍሰሳቸዉ፣አፍሪቃን መደገፍና መርዳታቸዉም የአፍሪቃን ችግር አላቃለለም።የብዙዎቹ የአፍሪቃ ሐገራት ሕዝብ ኑሮ አሁንም የከፋ ነዉ።የሥራ አጡ ቁጥር ከገዜ ወደ ጊዜ እየናረ ነዉ።

https://p.dw.com/p/43Glv
Kombobild Robert Habeck, Olaf Scholz und Christian Lindner
ምስል Frank Molter/Alexey Vitvitsky/Malte Krudewig/dpa/picture alliance

ትኩረት በአፍሪቃ፣ የጀርመን መርሕ፣ የብሊንከን ጉብኝት

የጀርመን አዲስ መንግስትና አፍሪቃ

ጀርመን ዉስጥ ባለፈዉ መስከረም በተደረገዉ አጠቃላይ ምርጫ የተሻለ ድምፅ ያገኙት የሶሻል ዴሞክራት (SPD)፣ ለዘብተኛዉ የነፃ ዴሞክራቲክ (FDP) እና የአረንጓዴዉ ፓሪቲዎች ፖለቲከኞች ተጣማሪ መንግስት ለመመስረት የሚያደርጉት ድርድር ወደ አግባቢ ፍፃሜ እያመራ ነዉ።የአዲሱ መንግስት ምሥረታ ለ16 ዓመታት ሐገሪቱን በመራሔ መንግሥትነት የመሩት የአንጌላ ሜርክል የፖለቲካ ሕይወት ፍፃሜ፣ የሚመሩት የክርስቲያን ዴሞክራቲክ ሕብረት (CDU) የተቃዋሚ ፓርቲነቱ መጀመሪያ ነዉ።

የሶስቱ ፓርቲዎች (እዚሕ ጀርመን በአርማቸዉ ቅደም ተከተል፣ SPD ቀይ፣FDP-ቢጫ፣ እና አረንጌዴዎቹ-አረንጓዴ) የትራፊክ መብራት ተብሎ የሚጠራዉ ተጣማሪ መንግሥት ስለአፍሪቃ የሚከተለዉ መርሕ ይዘትና እንዴትነት የአፍሪቃ ጉዳይን የሚመከታተሉ ታዛቢዎችን እያነጋገረ፣ ባለጉዳዮችን እያሳሰበም ነዉ።

ከአፍሪቃ ጋር የንግድና የመዋዕለ ነዋይ ግንኙነት ያላቸዉን ጀርመናዉያንን የሚያስተናብረዉ በጀርመን ምጣኔ ሐብት የአፍሪቃ ማሕበር ሊቀመንበር ክርስቶፈር ካኔንጊሰር ጉዳዩ ካሳሰባቸዉ አንዱ ናቸዉ።«አፍሪቃ፣ ሶስቱ ፓርቲዎች እስካሁን በሚደራደሩበት ሰነድ አልተጠቀሰችም» ይላሉ።ግን ጥርጣሬ ባይለያዉም ተስፋ አላቸዉ «ምናልባት በመንግስት ምስረታዉ ስምምነት ላይ የተሻለ ይኖራል የሚል ተስፋ አለን።»

ካኔንጊሰር ብቻቸዉን አይደሉም።በአንጌላ ሜርክል ዘመነ ሥልጣን የአዉሮጳ ጎረቤትዋ አፍሪቃ በጀርመን ፌዴራል መንግስት ዘንድ ከፍተኛ ተኩረት ተሰጥቷታል።ጀረመን ለአፍሪቃ የምትሰጠዉ የልማት ርዳታና ድጋፍ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።የጀርመን ቀጥታ የመዋዕለ ነዋይ ፍሰትም በቢሎዮን ዩሮ አሻቅቧል።

ሜርክል ቡድን 20 የተባለዉ የሐብታም ሐገራት ስብሰብ ሊቀመንበር በነበሩበት ዘመን የፀደቀዉ ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ (ከአፍሪቃ ቃር የቅርብ ትስስር) በተባለዉ ትብብር መሠረትም ጀርመን ከ12 የአፍሪቃ ሐገርት ጋር የምታደርገዉን ትብብርና የምትሰጠዉን ድጋፍ አጠናክሮታል።ካኔንጊሰር ትብብሩ በአዲስ መንግስትም መቀጠል አለበት ባይ ናቸዉ።

                                            

«ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ መቀጠል አለበት ብዬ አምናለሁ።ቡድን 20 የገባዉ ዓለም አቀፍ ግዴታ ነዉ። (መራሔ-መንግሥት ይሆናሉ ተብሎ የሚታመነዉ) አቶ ሾልስ ስምምነቱ ሲደረግ እንደ ገንዘብ ሚንስትር ተካፋይ ነበሩ።እስካሁን ይቀጥላል የሚል ተስፋ ነዉ ያለኝ።ጀርመን በሜርክል ዘመን የነበረዉን ያክል ቅድሚያ ትሰጣለች ወይ የሚለዉ ግን አጠያያቂ ነዉ።»  

ጀርመንም ሆኑ ሌሎቹ የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት አፍሪቃ ዉስጥ መዋዕለ ነዋያቸዉን ማፍሰሳቸዉ፣አፍሪቃን መደገፍና መርዳታቸዉም የአፍሪቃን ችግር አላቃለለም።የብዙዎቹ የአፍሪቃ ሐገራት ሕዝብ ኑሮ አሁንም የከፋ ነዉ።የሥራ አጡ ቁጥር ከገዜ ወደ ጊዜ እየናረ ነዉ።

ተቺዎች እንደሚሉት ጀርመን እስካሁን የምትከተለዉ መርሕ ከመሠረቱ ካልተቀየረ የመዋዕለ ነዋይ ፍሰቱም ሆነ የርዳታዉ መጨመር ለአፍሪቃ ሕዝብ ብዙም የሚተክረዉ የለም።ይሁንና መርሑ ለአፍሪቃ ሕዝብ በሚጠቅም መንገድ የሚቀየረዉ አሁን ያለዉ ትብብርና ድጋፍ መቀጠሉ ሲረጋገጥ ነዉ።APRI በሚል ሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የአፍሪቃ የፖለቲካ ጉዳይ አጥኚ ተቋም የበላይ ኦሉሚዴ አቢምቦላ መጀመሪያ ድጋፍና ትብብሩ መቀጠሉን እንወቅ ዓይነት ይላሉ።ሌላዉ ከዚያ በኋላ ይታሰብበታል።

Deutschland PK nach Ampel-Sondierungsgesprächen
ምስል Chris Emil Janßen/imago images

«ይሕ ጉዳይ የልማት ሚንስትርነቱን ሥልጣን የሚይዘዉ የየትኛዉ ፓርቲ ፖለቲከኛ ነዉ በሚለዉ ላይ የተመሠረተ ነዉ።ሥልጣኑን የሚይዘዉ የFDP የለዘብተኛዉ ፓርቲ ፖለቲከኛ ከሆነ፣ ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ እና የጀርመን የግል ባለሐብቶች አፍሪቃ ዉስጥ የሚደርጉት መዋዕለ ነዋይ ፍሰትን የመሳሰሉት መርሆች ይቀጥሉ ይሆናል።የሌሎቹ ፓርቲ ፖለቲከኛ ሥልጣኑን ከያዘ ግን የሚሆነዉ በግልፅ አይታወቅም።»

ስደተኞችን በተመለከተ የጀርመን መንግስትም ሆነ የአዉሮጳ ሕብረት ባጠቃላይ እስካሁን የሚከተሉት መርሕ ብዙዎች እንደሚሉት ወደፊም መቀጠሉ አይቀርም።መርሁ በጀርመኖች ዘንድ «ወዳጅ» የሚባሉትን ብዙዎቹን የአፍሪቃ ሐገራት ሳይቀር ቅር ያሰኘ ነዉ።አዉሮጶች፣ የአፍሪቃ ስደተኞች ወደ ግዛታቸዉ እንዳይገባ መከላከልን እንደ ዋና ጉዳይ አድርገዉ መጣራቸዉን አፍሪቃዉያን አይፈልጉትም።

እንዲያዉም ወደ አዉሮጳ ከሚገባዉ ወይም ሊገባ ከሚሞክረዉ ስደተኛ  ጋር ሲነፃፃፀር  እዚያዉ አፍሪቃ ዉስጥ ካንዱ ሐገር ወደ ሌላዉ ለሚሰደደዉ ሕዝብ ቁጥር በብዙ እጥፍ ይበልጣል።

ለSPD ይቀርባል የሚባለዉ የፍሬድሪሽ ኤበርት መታሰቢያ ጥናት ተቋም ባልደረባ ሔንሪክ ማይሐክን የመሳሰሉ ተንታኖች እንደሚሉት ጀርመንም ሆነች የአዉሮጳ ሕብረት እዚያዉ አፍሪቃ ዉስጥ ያለዉን ስደተኛ መርዳቱን ችላ ብለዉ አዉሮጳ ሊገባ በሚሞክረዉ ላይ በራቸዉን ለመዝጋት መሯሯጣቸዉ ለአፍሪቃዉን ተቀባይነት የለዉም።

 

                         የብሊንከን ጉብኝት

ጀርመን፣ በጀርመን በኩል የአዉሮጳ ሕብረት  ስለአፍሪቃ የሚከተለዉ መርሕ እዚሕ አዉሮጳ ላይ በሚያነጋግርበት በዚሕ ሳምንት፣ ዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊከን ሶስት የአፍሪቃ ሐገራትን ጎብኝተዋል።የዓለም ብቸኛ ልዕለ ኃያሊቱ ሐገር ትልቅ ዲፕሎማት፣ አሜሪካኖች «የአፍሪቃ የሠላም፣ የመረጋጋትና የዴሞክራሲ አብነት» የሚሏቸዉን ኬንያን፣ናጄሪያንና ሴኔጋልን የጎበኙት  ሶስት ትላልቅ አላማዎችን አንግበዉ ነበር።

የኢትዮጵያ ጦርነት፣የሱዳን መፈንቅለ መንግስትና የመሳሰሉ የአፍሪቃ ቀዉሶች ስለሚወገዱበት ብልሐት ከአፍሪቃዉያን ጋር መምከር-አንድ፣ የአፍሪቃን ገበያ ለመቀራመት ዩናይትድ ስቴትስ ከቻይና ጋር በገጠመችዉ ሽሚያ የበላይነትን ለመያዝ መጣር እና በዘመነ ትራምፕ «የተበላሸ» ያሉት የአሜሪካን ስም ማደስ-ሶስት።

አሜሪካዊዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ባለፈዉ ሮብ ናይሮቢ ዉስጥ ከኬንያ የሲቢል ተቋማት ተወካዮች ጋር ባደረጉት ዉይይት ዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪቃን ዴሞክራሲ፣ የሰብአዊ መብት ይዞታና የሕዝቡን ችግር ለማቃለል ከሚጥሩ ወገኖች ጋር ተባብራ እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።

ብሊንከን ናይሮቢ የገቡት የአፍሪቃ ሕብረትና የራስዋ የዩናይትድ ስቴትስ ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያ ተፋላሚ ኃይላትን ለመሸምገል የጀመሩት ዲፕሎማሲ በተስፋና ቀቢፀ ተስፋ በተቃረጠበት መሐል፣ የኬንያዉ ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ አዲስ አበባ ዉስጥ ከኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ጋር በተነጋገሩ በአራተኛዉ ቀን ነበር።ማክሰኞ-ለሮብ አጥቢያ።

Raychelle Omamo und Antony Blinken
ምስል Andrew Harnik/Pool/AP/picture alliance

ሮብ እስከ ማርፈጂያዉ ከኬንያ ባለስልጣናት ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ መስተዳድራቸዉ ከዚሕ ቀደም ያለዉን ነዉ የደገሙት።ተኩስ አቁምና ድርድር።

የኬንያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ራይቼለ ኦማሞ በአሜሪካዊዉ እንግዳቸዉ አስተያየት በከፊል የተስማሙ አይመስልም።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሯ ብዙ ሺሕ ሕዝብ የገደለ፣ ሚሊዮኖችን ያፈናቀለዉና ቢቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሐብት ያወደመዉን  ጦርነት ለማቆም ኢትዮጵያዉያን  ብልሐቱ አይጠፋቸዉም ነዉ ያሉት።ግን ያዉ «ተኩስ አቁም፣ድርድር» ከማለት አልዘለሉም።

«ኢትዮጵያ ለዚሕ ቀዉስ መፍትሔ የመፈለግ አቅም እንዳላት እናምናለን።ተኩስ አቁም ይቻላል ብለን እናምናለን።የሰብአዊ ርዳታ አቅርቦትን የሚመለከቱ ሌሎች ሁኔታዎች እንደሚሳካ እናምናለን።በኢትዮጵያ ሕዝብ መከራን በመቋቋም ፅናትና ብልሐቱ ማመን አለብን።ምክንያቱም መጨረሻ ላይ እነዚሕ መፍትሔዎች ከራሳቸዉ ይመጣሉና።»

ብሊንከን ከኬንያዊቱ አቻቸዉ ጋር ሆነዉ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የሱዳን የጦር ጄኔራሎች ከስልጣን ያስወገዱትን የሲቢል መስተዳድር ወደ ስልጣን እንዲመልሱም በድጋሚ ጠይቀዋል።

ብሊንከን የናይሮቢ ጉብኝታቸዉን አጠናቅቀዉ አቡጃ-ናጄሪያ ከመግባታቸዉ በፊት የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ «ናጄሪያ የኃይማኖት ነፃነት የማይከበርባት ሐገር» በማለት የፈረጁበትን ደንብ መስተዳድራቸዉ ሽሮ ነበር።

ትራምፕ በወንጌላዉያን ክርስቲያኖች ግፊት ያፀደቁት ደንብ በሕዝብ ብዛት ከአፍሪቃ አንደኛ፣ የብዙ ኃይማት ተከታዮችን አሰባጥራ በማኖር የምትታወቀዉን አፍሪቃዊት ሐገር ናይጄሪያን «የመጥፎች መዝገብ» ዉስጥ የከተተ ነበር።የአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር መጀመሪያ ያነጋገሩም የናጄሪያ የኃይማኖት አባቶችን ነዉ።

ትናንት በምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ማሕበረሰብ (ECOWAS) ዋና ፅሕፈት ቤት ተገኝተዉ ባደረጉት ንግግር ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ከቻይና ጋር በገጠመችዉ ሽሚያ የአፍሪቃዉያንን ልብ ለማማለል ማለማቸዉን ጠቋሚ ነበር።ቻይናን በስም ባይጠቅሱም «በዉጪ ኃይላት ሽሚያ አፍሪቃዉያን ግራ-ቀኝ መጓተቱ እንደሚያሰጋቸዉ እንገነዘባለን» ብለዋል።ይሁንና እኛ አንዱን ምረጡ አንልም አሉ-የአሜሪካዉ ዲፕሎማት፤ «አማራጭ እንሰጣችኋለን እንጂ»

«ግልፅ መሆን እፈልጋለሁ።ዩናይትድ ስቴትስ ከሌሎች ሐገራት ጋር የምታደርጉትን ወዳጅነት መወሰን አትፈልግም።ከኛ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት ግን ይበልጥ ማጠናከር እንፈልጋለን።አንዱን እድትመርጡ ማድረግ አንፈልግም።አማራጮች እንሰጣችኋለን እንጂ።»

ብሊንከን ከትናንት ማታ ጀምሮ የጎበኝዋት ሴኔጋል የቻይናና የአፍሪቃ የወዳጅነት ጉባኤን ለማስተናገድ እየተዘጋጀች ነዉ።ለቻይና ዕቅድና ዝግጅት ዩናይትድ ስቴትሱም ለአፀፋ እየተዘጋጀት ነዉ። ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በቅርቡ የአፍሪቃ መሪዎችን ለማነጋገር ጉባኤ ጠርተዋል።

ነጋሽ መሐመድ 

ኂሩት መለሰ