1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፋር ወጣቶች ቅሪታ

ሐሙስ፣ ሰኔ 21 2010

ወደ ውይይቱ አዳራሽ መግባት ተከለከልኩ የሚል ወጣት የአፋር ወጣቶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት ውይይት ላይ ለመካፈል ቢፈልጉም አለመጋበዛቸውን ይገልጻል። ውይይቱ ወደ ሚካሄድበት ስፍራ ሄደው ለመግባት የጠየቁ ወጣቶችም እርሱ እንደሚለ«በልዩ ፖሊስ ተደብድበው ጉዳት ደርሶባቸዋል፤የታሰሩም አሉ»።

https://p.dw.com/p/30UuI
Äthiopien Wissenschaftlerin Forscherin Lulit Tilahun Wolde Afar Triangle
ምስል L. T. Wolde

የአፋር ወጣቶች ቅሬታ

የኢትዮጵያ  ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ አብይ አህመድ ዛሬ በአፋር ክልል በሰመራ ከተማ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። በውይይቱ ላይ ከህብረተሰቡ ለተነሱ ልዩ ልዩ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልስ ሰጥተዋል። በውይይቱ ያልተጋበዙ ፣ግን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መወያየት እንፈልጋለን ሲሉ ውይይቱ ወደሚካሄድበት አዳራሽ ለመግባት የጠየቁ ወጣቶች በፖሊስ እንደተደበደቡ እና እንደታሰሩ በአካባቢው ነበርን ያሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ለዶቼቬለ ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ  እንደተገኙ የነገሩን አንድ የአፋር ተወላጅ እንዳሉት ህብረተሰቡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ካነሳቸው ጥያቄዎች መካከል በልማት ሰበብ የተፈናቀሉ ሰዎች ጉዳይ እና የአዋሽ ወንዝ ብክለት ያስከተለው የጤና ችግር ይገኙበታል።

የትኛውንም ወረዳ እንደማይወክሉ የተናገሩት እኚሁ ነዋሪ  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህብረተሰቡ ጥያቄዎች የሰጡት መልስ ከሞላ ጎደል ጥሩ ነው ብለዋል። ሆኖም ጥያቄ የማቅረብ እድል አለማግኘታቸውን ተናግረው በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ  አጥጋቢ መልሶች እንዳላገኙ መነሳት ነበረባቸው ያሏቸው ጥያቄዎችም እንዳልተነሱ ተናግረዋል።  

ወደ ውይይቱ አዳራሽ መግባት ተከለከልኩ የሚል ሌላው ወጣት ደግሞ የአፋር ወጣቶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት ውይይት ላይ ለመካፈል ቢፈልጉም አለመጋበዛቸውን ይገልጻል።

ውይይቱ ወደ ሚካሄድበት ስፍራ ሄደው ለመግባት የጠየቁ ወጣቶችም እርሱ እንደሚለው በልዩ ፖሊስ ተደብድበው ጉዳት ደርሶባቸዋል የታሰሩም አሉ።

ከተጎዱት መካከል ሴቶች እና በእድሜ የገፉም እንደሚገኙበት ወጣቱ ተናግሯል። በርሱ አባባል ወጣቶቹ ስብሰባው እንዳይገቡ የተከለከሉት በክልሉ ያለውን ችግር ያጋልጣሉ በሚል ስጋት ሳይሆን አይቀርም።  ዶቼቬለ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የክልሉን ባለሥልጣናት ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ