1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የድንጋጤ፣ የሐዘንና የውዝግብ ሳምንት

ዓርብ፣ ሰኔ 21 2011

የኢትዮጵያ መንግሥት በባሕር ዳር እና በአዲስ አበባ ለተፈጸሙት ግድያዎች ተጠያቂው ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ ናቸው ቢልም የማኅበራዊ ድረ-ገፅ ተጠቃሚዎች በየራሳቸው ትንታኔ እየተወዛገቡ ይገኛሉ። ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. የተፈጸመው ጥቃት ለተካረረው የብሔርተኞች ቁርቁስ ተጨማሪ ማቀጣጠያ ሆኗል።

https://p.dw.com/p/3LIi9
Äthiopien Trauerfeier für General Seare Mekonnen
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Ayene

በማኅበራዊ ድረ-ገፆች የመላምት ትንታኔዎች በዝተዋል

ፌስቡክን ጨምሮ ኢትዮጵያውያን የሚያዘወትሯቸው ማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ድንጋጤ፤ ሐዘን እና ግራ መጋባት በሚያንጸባርቁ  መልዕክቶች ተሞልተዋል። የመላ ምት ትንታኔዎች በማኅበራዊ ድረ-ገፆች በሽበሽ ናቸው። በዚህ ሁሉ ውስጥ ኢትዮጵያ የገባችበትን ቅርቃር እንድትሻገር የሚመኙ ብዙ ናቸው። ከእነዚህ መካከል «ጊዜው አስቸጋሪና ፈታኝ ቢሆንም ነገ ግን መልካም ይሆናል። ኢትዮጵያዬ ሆይ የሚገጥምሽ ፈታኝ ጊዜ እንዲያጥር እና ብሩህ ጊዜ በቶሎ እንድናይ የፈጣሪ ፈቃድ ይሁን» ያሉት ኤርሚያስ በላይ አንዱ ናቸው። 

ትናንት ምሽት የኢትዮጵያ መንግሥት ጄኔራል ሰዓረ መኮንን እና ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራ የተገደሉት አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ መኮንን በተባለ ወታደር መሆኑን አስታውቋል። ስለ ባለሥልጣናቱ ግድያ እና ተሞከረ ስለተባለው መፈንቅለ መንግሥት የጸጥታ እና ፍትኅ የጋራ ግብረ-ኃይል በሰጠው መግለጫ «ጥቃቱን የፈጸመው ግለሰብ በፌድራል የጸጥታ ኃይሎች ቆስሎ በቁጥጥር ሥር ውሏል» ብሏል።  ጉዳዩ ቀድሞም በባሕር ዳር ተሞከረ የተባለውን መፈንቅለ መንግሥት እና የአዲስ አበባዉን ግድያ ሲጠራጠሩ የነበሩ የማኅበራዊ ድረ-ገፅ ፀኃፍት ወደ ባሰ ግራ መጋባት ገፍቷቸዋል። መሕቡባ ወሎዬዋ «ክፍል 1 ታሰረ፤ ክፍል 2 ራሱን አጠፋ፤ ክፍል 3 ሆስፒታል ተገኘ፤ ክፍል 4 ማንነቱ ይፋ ሆነ ክፍል 5 ይቀጥላል» ሲሉ እርስ በርሱ የሚፋለሰው የኢትዮጵያ መንግሥት መረጃ ተዓማኒነት እንደሌለው ሐሳባቸውን ገልጸዋል። ባባ ቢኒ በበኩላቸው «መንግስት ለምን ይዋሻል? ገዳይ የተባለውን ይሄን ልጅ መጀመሪያ ራሱን አጠፋ አለ።ከዚያ በፀጥታ ሀይሎች ተመቶ ሞተ አለ። ለሶስተኛ ጊዜ ቆስሎ ሆስፒታል ነው አለ? ማንን እንመን?እውነታው የቱ ነው?» ሲሉ እንደ መሕቡባ ወሎዬዋ ሁሉ ግራ መጋባታቸውን ጠቁመዋል። አማኑኤል ግርማይ በበኩላቸው «ትወናዉን ችለዉበታል፤ ሙቶ የተነሳዉ የጀነራል ሰዓረ ገዳይ ፍርድ ከላይ ነዉ» ሲሉ በፌስቡክ ፅፈዋል።አሸናፊ አረጋዊ «ጀኔራል ሰዓረ መኮነን እና ሜጀር ጀኔራል ገዛኢ ኣበራ የተገደሉት መፈንቅለ መንግስት በማክሸፍ እያሉ በብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው ቅጥረኛ ነው ይሉናል:: መልሰው ደግሞ የጀኔራሎቹ ግድያ ከባህርዳሩ መፈንቅለ መንግስት ጋር ግንኙነት ስለመኖሩ አጣርተን ለህዝብ ይፋ እናደርጋለን ይላሉ» ሲሉ የመንግሥት እርስ በርስ የሚጣረሱ መረጃዎች ግራ እንዳጋቧቸው ፅፈዋል። 
የኢትዮጵያ መንግሥት ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ እና ግብረ አበሮቻቸውን «ሥልጣንን በኃይል እና በመሳሪያ አፈ-ሙዝ ለመያዝ የተደረገ» ለተባለው ጥቃት ተጠያቂ አድርጓቸዋል። የፖለቲካ ተንታኙ አወል አሎ በፌስ ቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት ረዘም ያለ ፅሁፍ የኢሕአዴግ አባል የሆነ የፖለቲካ ፓርቲ በሚያስተዳድረው ክልል ላይ መፈንቅለ-መንግሥት ማካሔድ አዋጪ ነወይ? ሲሉ ጠይቀዋል። አወል በፅሁፋቸው ካነሱት ሐሳብ መካከል «የመንግሥት የመረጃ ምንጮች ነገሩ ሁሉ በቁጥጥር ሥር መዋሉን እና ነገሮች ወደ ነበሩበት መመለሳቸውን እየገለጹ ነው። ይኸ ጥሩ ነገር ነው። ነገር ግን ከሕዝባዊ ኹከት ወደ ክልል ፕሬዝዳንት እና የአገሪቱ ጦር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፖለቲካዊ ግድያ መሸጋገራችን ወደ አዲስ ምዕራፍ መግባታችንን ይጠቁማል። በየትኛው አቅጣጫ ቢታይ ይኽ ትልቅ ነገር ነው። ጉዳዩ አገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓተ-መንግሥት ለመመስረት በምታደርገው ሙከራ ላይ የራሱ ዳፋ ይኖረዋል» ሲሉ ፅፈዋል። 

Äthiopien  Seare Mekonnen
ምስል Addis Abeba city mayor office

ከባሕር ዳር ወጣ ብላ በምትገኘው ዘንዘልማ የተባለች ቦታ ተገድለው በትውልድ ቀያቸው ላሊበላ በክብር የተቀበሩት ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ዋንኛ መወዛገቢያ ሆነዋል። ለደጋፊዎቻቸው እስከ ዕለተ ሞታቸው የአማራ ክልልን የሰላም ግንባታ እና ደሕንነት ቢሮ በኃላፊነት ይመሩ የነበሩት አሳምነው ለሕዝባቸው መብት ጥብቅና የቆሙ ጀግና ነበሩ። ሙሉነሽ አበባው «የአማራው አባት ጀኔራል አሳምነው ፅጌ እስከ መጨረሻ ለእውነት ለአማራ ህዝብ አላስነካም ብሎ የቆመ ነበር» ሲሉ አስፍረዋል። «እንደ ፖለቲካ ቆሻሻ ነገር የለም። ጄነራል አሳምነው ስለፈሩህ ነው ያለስም ስም ሰጥተው የገደሉህ። ድራማው ተጠናቋል ግን ደራሲው በህይወት አለ። እውነት ብትዘገይም መውጣቷ አይቀርም» ያሉት ደግሞ አቤኔዘር በላይ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ናቸው። 
ኢትዮጵያ የተሰኘ ስያሜ ያለው አንድ የፌስቡክ ገፅ «አሳምነው ፅጌ እራሱንም ጓዶቹንም አጠፋ ብቻ ማለት አይቻልም። አገለግለዋለሁ ያለውን አማራ ዛሬ አፈር አለበሰው። ማዕረጉን መልሳ አገርህን አገልግል ያለችውን ሀገር ለውለታዋ የሀዘን ሻማ ሸለማት፤ ለሀገሩ፣ ለዘመዱ፣ ለቤተሰብና ለልጆቹ ማሰብ ያልቻለው አሳምነው ለሀገር ፈተና ለወገን እርግማን ሆነ» ብለዋል። 
ለታ ቲ ባይሳ «በገዛ ወንድሞቻቸው ለይ እንዲህ የጨከኑት ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ ኢትዮጵያን የመምራት እድል ቢደርሳቸው ምን እንደሚፈጠር መገመት ከባድ አይደለም» ሲሉ ኮንነዋቸዋል። 
ሶስት ከፍተኛ የአማራ ክልል ሹማምንት ሁለት ከፍተኛ የጦር አዛዦች ከተገደሉባቸው የዕለተ-ቅዳሜው ጥቃቶች በኋላ የማኅበራዊ ድረ-ገጽ ተጠቃሚዎች አብዛኞቹ እንደ ብሔራቸው «በቢሆን» ትንተና ቢጠመዱም ግራ የገባቸው፤ የአገሪቱ እጣ-ፈንታ ያሳሰባቸው ብዙ ናቸው። የጥቃቶቹ ፈፃሚ ማንም ይሁን ማን ለታመመው ፖለቲካ በአፈሙዝ መፍትሔ ለመሻት መሞከሩ ያሳሰባቸው ሥጋታቸውን ለማኅበራዊ ድረ-ገጽ ተጠቃሚዎች እያጋሩ ነው። 
ሚካኤል ጎዲ በፌስቡክ እንዳሉት ለጥቃቱ መነሾ ሊሆኑ የሚችሉ ኩነቶች ቀደም ብለው ታይተዋል። «ጠቅላይ ምኒስትሩ አገሪቱን ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ የሔዱበት መንገድ ከተኮላሸ ቆይቷል። ተሞክሮ ከሸፈ ከተባለው መፈንቅለ-መንግሥት ቀደም ብሎ በርካታ የብሔር ግጭቶች እና መፈናቀሎች ነበሩ። መንግሥት ጸጥታን እና የዜጎችን ደሕንነት ማስጠበቅ ተስኖታል። በዚህ ምክንያት በርካታ አክራሪ ታጣቂዎች እና አበጋዞች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ እና ሕዝቡን እንዲያሸብሩ ተፈቅዶላቸዋል። በብሔር ፖለቲካ ያበደ አገር ሲኖር የሚፈጠረው ይኸው ነው» ሲሉ ሐሳባቸውን አስፍረዋል። 
ወገኔ አየነ «ዛሬም እንደ ትናቱ ወንድም ወንድሙን ገድሎ ስልጣን ለመያዝ፤ የበላይ ለመሆን መከጀል እጅግ የሚያስገርም ነዉ። ቢሳካ እንኳን የሚከተለዉን አለማስተዋል ድንቁርና ነዉ። እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እንዳለችዉ እንስሳ ስለሚጠፋዉ ሕይወት አለማሰብ ነዉ» ብለዋል። 
ሱራፌል ወንድሙ «ጥቃቶቹን ማንም ይፈፅማቸው ማን ፤ መገዳደል የፖለቲካ መፍትሔ ነው የሚለው ሃሳብ አሁንም መቀጠሉ ልብ ያደማል። በዘመናት ውስጥ ለተሻለ ህይወት ለውጥ እየሰራችሁ ህይወታችሁን እየገበራችሁ ያላችሁ፣ በማታውቁት ነገር በስግብግቦች ዳፋ በየዕለቱ ሰውነት-ነፍሳችሁን የተቀማችሁ፣ ጥቂቶች በጨካኝነት በሃብት ሲጨማለቁ እናንተ ከሰብዓዊ ክብር ተገልላችሁ ከቆሉበት የጋፉበት ሆናችሁ የምትሰቃዩ ሁሉ ዘወትር አስባችኋለሁ፤  አከብራችኋለሁ ! ስለእናንተና ስለቤተሰቦቻችሁ ሃዘኔ ቢበረታም፤ ስለ ሰውነታችሁ እመስክራለሁ! መፅናኛዬም፣ ተስፋዬም የተሻለ ሰውነትን የመፍጠር ህልም ነው» የሚል ሐሳብ በግል የፌስቡክ ገፁ አስፍሯል። 
ብሩክ አበጋዝ «ተረጋጉ! አሁንም ተረጋጉ! ምን እያደረግን ነበር ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ!ወደ ፊትም ምን ማድረግ እንዳለባችሁ በደምብ አስሉ። » ሲሉ ምክር ለመስጠት ሞክረዋል። ብሩክ በፌስቡክ ባሰፈሩት አጠር ያለ ሐተታ «ወደ ፌስቡክ ተመልሼ ዞር ዞር ብየ የቃኘሁት ነገር ብዙ ሰወች አሁንም የቅዠት ዓለም ውስጥ እንደሆኑ ነው። ከግምት፣ ከይሆናል፣ ከጥርጣሬ፣ ከውሸት የመነጩ አስተያየቶች እውነቱን ለማልበልስ በከፍተኛ ጥረት ላይ ናቸው። እባካችሁ በሽታችንን እንወቅ፣ ብዙወቻችን ራሳችን በፈጠርናቸው በሽታወች ያመጣነው የአእምሮ መዛባት ሌላ ችግር እየፈጠረ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ባላረጋገጥነው መረጃ ተመስርተን የምንሰጠው ትንታኔና ድምዳሜ ዋጋ ያስከፍለናል፤ እስካሁንም ሲያስከፍለን ኖሯል። ለሕዝብ ቆምን የምትሉ ሰወች ባልተረጋገጠ በይሆናል በግምት ማስረጃ ተነሳስታችሁ ትንታኔ ከመሰጠት ታቀቡ። እዚህ ማህበራዊ ሜዲያው ላይ የወጡና ያየኋቸው ግምታዊ ትንታኔና ድምዳሜወች የበለጠ በሽታ የሚፈጥሩ እንጂ ህመማችንን የሚፈውሱ አይደሉም። ለህዝብ እቆረቆራለሁ የሚል ሰው ከተራ አሉባልታ፣ ሀተታና ከግምት ትንታኔ ራሱን ያቅብ» ሲሉ ጥንቃቄ እንዲደረግ መክረዋል።
እሸቴ በቀለ 
ነጋሽ መሐመድ 
 

Äthiopien Einweihung der Sauerstoffanlage in Bari Dar
ምስል DW/A. Mekonnen
Äthiopien Amhara | Beerdigung in Bahrdar
ምስል DW/A. Mekonnen