1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ንግድአፍሪቃ

 የድሬዳዋ ነዋሪዎችን ያማረረው የሸቀጦች ዋጋ ንረት

ረቡዕ፣ ነሐሴ 12 2013

በድሬዳዋ ከተማ በምግብ ሸቀጦች ላይ የተፈጠረው የዋጋ ግሽበት ለማረጋጋት መንግስት የሸቀጦች መሸጫ ዋጋ ተምኖ በማውጣት በሥራ ላይ እንዲውል ቢያደርግም፤ በዋጋ ላይ ለውጥ አለመታየቱን ነዋሪዎች ገለፁ። ነጋዴው አለአግባብ ዋጋ እንደሚያንር የጠቀሱት ነዋሪዎች ነጋዴው ኅብረተሰቡን በፍትሀዊነት እንዲያገለግል ጠይቀዋል፡፡

https://p.dw.com/p/3z8LT
Stadt Dire Dawa in Äthiopien
ምስል Hailegzi Mehari

«በምኖርበት አካባቢ ሩብ ኪሎ ስኳር 14 ብር ነው»

በድሬዳዋ ከተማ በምግብ ሸቀጦች ላይ የተፈጠረው የዋጋ ግሽበት ለማረጋጋት መንግስት የሸቀጦች መሸጫ ዋጋ ተምኖ በማውጣት በሥራ ላይ እንዲውል ቢያደርግም፤ በዋጋ ላይ ለውጥ አለመታየቱን ነዋሪዎች ገለፁ። ነጋዴው አለአግባብ ዋጋ እንደሚያንር የጠቀሱት ነዋሪዎች ነጋዴው ኅብረተሰቡን በፍትሀዊነት እንዲያገለግል ጠይቀዋል። አንድ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ በሚኖሩበት አካባቢ ሩብ ኪሎ ስኳር 14 ብር፤ ሩብ ሊትር ዘይት ደግሞ ወደ 24 ብር እንደደረሰ በምሬት ተናግረዋል። 

በምግብ ሸቀጦች ላይ በአጭር ጊዜ የተፈጠረውን የዋጋ ንረት ተከትሎ አራት መቶ በሚጠጉ የንግድ ተቋማት ላይ የማሸግ ርምጃ የወሰደው የድሬደዋ አስተዳደር ለሸቀጦች የመሸጫ ዋጋ ትመና በማውጣት ተቋማቱ ተከፍተው በሥራ ላይ እንዲያውሉ ውሳኔ አሳልፏል። የአስተዳደሩ ንግድ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙክታር ከድር ችግሩን ለመፍታት ከአምራቾች፣ አስመጪዎች፣ አከፋፋዮች እና ቸርቻሪዎች ጋር ውይይት መካሄዱን እና አስመጪ እና ጅምላ አከፋፋዮችን ያካተተ ኮሚቴ በማዋቀር የሸቀጦች የዋጋ ትመና ወቶ ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉን ተናግረዋል።

አንድ ሳምንት ያህል ጊዜን ባስቆጠረው ውሳኔ መሰረት ከፊል የንግድ ድርጅቶች ተከፍተው ሥራ ቢጀምሩ በዋጋ ላይ የሚታው ችግር ግን አለመፈታተቱን ነዋሪዎች ገልፀዋል። በአስተዳደሩ በአጭር ጊዜ በእጥፍ ለጨመረው የሸቀጦች ዋጋ በምክንያትነት የሚነሱ በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም ነጋዴው ኅብረተሰቡን በፍትሃዊ መልኩ የማገልገል ችግር አለበት የሚሉት ነዋሪዎች ነጋዴው ይህንን እንዲገነዘብ ጠይቀዋል። በሸቀጦች ዋጋ ላይ ለታየው ጭማሪ በምክንያትነት የሚቀርቡ ትክክለኛ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት ከሚያደርገው የተለያየ ጥረት ጎን ለገን የኢኮኖሚ አሻጥር ለመፍጠር በሚሠሩት ላይ ተገቢውን ቁጥጥር በማድረግ ርምጃ እንደሚወሰድ ገልፃል። 
መሳይ ተክሉ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ