1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የድሬደዋዉ ሲሚንቶ ፋብሪካ ብናኝ እያደረሰ ያለዉ ጉዳት 

ዓርብ፣ ኅዳር 18 2013

በድሬደዋ ከሚገኙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች አንዱ ከሆነው ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ የሚወጣው ብናኝ በአካባቢው ህብረተሰብ ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ቢሆንም ለዓመታት ችግሩ መፍትሄ አላገኘም ሲሉ ነዋሪዎች ቅሬታ አቀረቡ፡፡ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ችግሩ መኖሩን አምኖ መፍትሄ እንዳልመጣም ገልፆአል።

https://p.dw.com/p/3lvFn
Äthiopien Dire Dawa Zementfabrik
ምስል Mesay Tekilu/DW

ከፋብሪካው የሚወጣው ብናኝ በዚሁ ከቀጠለ በህብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት ያስከትላል


በድሬደዋ ከሚገኙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች አንዱ ከሆነው ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ የሚወጣው ብናኝ በአካባቢው ህብረተሰብ ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ቢሆንም ለዓመታት ችግሩ መፍትሄ አላገኘም ሲሉ ነዋሪዎች ቅሬታ አቀረቡ፡፡ የአስተዳደሩ የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን በበኩሉ ችግሩ መኖሩን አምኖ መፍትሄ እንዲያገኝ የተደረጉ ጥረቶች መፍትሄ እያመጡ አይደለም ብሏል ፡፡
በከተማው ከሚገኙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች አንዱ የሆነው የናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ በአመራረት ሂደት ከፋብሪካው የሚያስወጣው ብናኝ በህብረተሰቡ ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን ለ«DW» ቅሬታ ካቀረቡ ነዋሪዎች መካከል አቶ የወንድወሰን አስፋው ተከታዩን አቅርበዋል፡፡
የአካባቢ ጤና ሳይንስ ባለሞያ በሰጡት አስተያየት ከፋብሪካው የሚወጣው ብናኝ በዚሁ ከቀጠለ በህብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት ያስከትላል ብለዋል፡፡ በፋብሪካው በኩል “ለችግሩ መፍትሄ ነው የተባለው መለዋወጫ ዕቃ ከውጭ ይመጣል” ይላሉ የሚሉት አቶ የወንድወሰን ችግሩ እንዲፈታ የመስተዳድሩ አካላት የተሳተፉበት ተደጋጋሚ ጥረት ቢደረግም ዛሬም መፍትሄ አለማግኘቱን ጠቁመዋል፡፡
የድሬደዋ አስተዳደር የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ አብዶ መሀመድ በበኩላቸው ህብረተሰቡ የሚያነሳው ችግር ትክክለኛ መሆኑን ገልፀው ችግሩ እንዲቀረፍ ጥረት ቢደረግም  ፋብሪካው መፍትሄ አለመስጠቱን አስረድተዋል፡፡ ባለስልጣን መ/ቤቱ በህግ በተሰጠው ስልጣን ፋብሪካውን ሙሉ በሙሉ መዝጋት የሚያስችል እርምጃ የመውሰድ ስልጣን አለው ያሉት አቶ አብዶ በሀገሪቱ ካለው የሲሚንቶ እጥረት እና ፋብሪካው ከሚያበረክታቸው ሌሎች ጠቀሜታዎች በመነሳት መዝጋት መፍትሄ አይደለም በሚል መቆየቱን እና አሁን ግን ቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫ ለመስጠት ለመስተዳድሩ ከንቲባ ጉዳዩን አሳውቀናል ብለዋል፡፡

Äthiopien Dire Dawa Zementfabrik
ምስል Mesay Tekilu/DW

ባለስልጣኑ ከናሽናል ሲሚንቶ በተጨማሪ ተመሳሳይ ችግር አለበት ለተባለው ሌላ ፋብሪካም እርምት እንዲወሰድ ማስጠንቀቂያ ሰጥቻለሁ ብሏል፡፡ በናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ተገኝቼ በምርት ሂደት የሚወጣውን ከፍተኛ ብናኝ ተመልክቻለሁ ይሁን እንጂ ችግሩን እና የመፍትሄውን እንዴትነት በሚመለከት ከፋብሪካው አመራሮች ምላሽ ለማግኘት ብሞክርም ፍቃደኛ ባለመሆናቸው አልተሳካም ፡፡

መሳይ ተክሉ 
አዜብ ታደሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ