1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የድምፃዊ እዮብ መኮንን የመጨረሻ አልበም ሥራዎች

እሑድ፣ ኅዳር 2 2011

በመጀመሪያ አልበሙ ተወዳጅነትን ያተረፈው ድምፃዊ እዮብ መኮንን ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ በኋላ የቀድሞ ባለቤቱና ጓደኛው ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ የመጨረሻ አልበሙን የዛሬ አንድ ዓመት ለአድማጭ ጆሮ አድርሰዋል። ድምፃዊ እዮብ ሠርቶ ያገኘውን ብር ለተቸገሩ ሰጥቶ ይጨርስ እንደነበር ጓደኞቹ ይናገራሉ።

https://p.dw.com/p/384AU
Album vom äthiopischen Sänger Eyob Mekonnen
ምስል Yisakal Entertainment

በመጀመሪያ አልበሙ ተወዳጅነትን ያተረፈው ድምፃዊ እዮብ መኮንን ይህችን ምድር ከተሰናበተ ወደ አምስት አመት እየሆነው ነው። በሰላሳ ሰባት ዓመቱ የሞተው ድምፃዊ የሙዚቃ መልዕክቶቹ ይዘት ከአዛዚያሙ ጋር ተደምሮ በቀላሉ አድማጭ ጆሮ ውስጥ መቅረት ችሏል። በ1975  እ ኤ አ ጥቅምት 12 በጂግጂጋ የተወለደው ድምፃዊው የሬጌና ሩት ሙዚቃዎችን ጠንቅቆ የሚጫወት፤ የሀገሩን ቺክቺካ ጭምር ከሬጌ ጋር አዋህዶ መስራት የቻለም ነበር።ዛየን ባንድን በመቀላቀል በተለያዩ የአዲስ አበባ ክለቦች ከነ ድምፃዊ ሀይልዬ ታደሰ ጋር ተጫውቷል። ከሀገር ውስጥ አሊ ቢራን ከውጭ ደግሞ ቦብ ማርሌ አርአያዎቹ እንደሆኑ ተናግሮ ነበር።ከ 8 አመት በፊት እንደቃል የተሰኘ አልበም ያበረከተው እዮብ በጊዜው የሙዚቃው ቶሎ አለመደመጥ አስግቶትም እንደነበር ተናግሮ ነበር ኋላ ላይ ከተማው ሁሉ የእርሱን ዘፈን ማጫወት አዘውትሮ ገላገለው እንጂ።ህይወትን በተለየ መነፅር ተመልክቷት እንዳለፈ የሚነገርለት ድምፃዊ እዮብ መኮንን የባንክ ቡክ እንኳን የኖረው በዛየን ባንድ ስራ አስኪያጅ ሚኪ በኩል እንደነበር ተናግሮም ነበር። ለቁሳዊ ነገር በዙም ቁብ ያልሰጠው ድምፃዊው ሰርቶ ያገኘውን ብርም ለተቸገሩ ሰጥቶ እንደሚጨርስ ጏደኞቹ ይናገራሉ።እርሱ ከዚህ አለም በሞት ከተለየ በኋላ የቀድሞ ባለቤቱና ጉዋደኛው ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ የመጨረሻ አልበሙን የዛሬ አንድ አመት ለአድማጭ ጆሮ አድርሰዋል።

ዳግማዊ ሲሳይ ተድላ

ልደት አበበ