የድምጻዊ ሃጫሉ ግድያና የኦፌኮ እስርን በመቃወም የተቃዉሞ ሰልፍ በፍራንክፈርት
ዓርብ፣ ሰኔ 26 2012
ዛሬ ከቀትር በኋላ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች የታዋቂውን ድምፃዊና የነጻነት ታጋይ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ /ኦፌኮ/ አመራሮችን እስር በመቃወም የተለያዩ መፈክሮችን እና መልክቶችን በማሰማት በፍራንክፈርት የኢትዮጵያ ቆንጽላ ጄኔራል ጽ/ቤትና በከተማዋ አደባባዮች ቁጣቸውን ለመግለፅና ድምፃቸውን ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ ለማሰማት ለተወሰኑ ደቂቃዎች መንገድ በመዝጋት ጭምር የታገዘ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል:: በከፍተኛ ቁጣ የተሞሉት ሰለፈኞቹ "ከዕውቁ ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጀርባ የገዢው መንግስት እጅ አለበት" ሲሉ ወቅሰዋል:: ከ 5ሺ በላይ ቄሮዎች ሕይወታቸውን ገብረው ጨቋኙን ስርዓት የለወጡት ሕብረ ብሄራዊ ሥርዓቱን በመናድ አሃዳዊ መንግስትን የሚገነባ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነን አስተዳደርን ለመተካት አይደለም ያሉት ሰልፈኞቹ ፤ በፖለቲካ ሴራ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ /ኦፌኮ/ አመራር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ እንዲሁም የፓርቲው አባልና አክቲቪስት አቶ ጃዋር መሃመድን ጨምሮ ሌሎችም ግለሰቦች መንግሥት ባቀነባበረው የፖለቲካ ሴራ ለእስር መዳረጋቸውንም አጥብቀው ተቃውመዋል:: የሰልፉ አስተባባሪ አቶ አብዶቃዲ አባጀበል መንግስት በርካታ ንፁሃን ኦሮሞዎችን እየገደለና እያሰረ የሚገኝበት ሰቆቃ እንዲያበቃ ፤ የፖለቲካ እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈቱና ገዢው መንግስት ከተቃዋሚ ኃይሎች ጋር አስቸኳይ ውይይት በማካሄድ በሰላማዊ መንገድ ስልጣኑን እንዲለቅ ለመጠየቅ ሰልፉ መጠራቱን ለዶይቼ ቨለ "DW" ገልፀዋል:: ሌላዋ ሰልፈኛ ቀነኒት አብዲም በኦሮሞዎች ላይ የሚፈፀመው ግድያና እስራት በአስቸኳይ ይቁም ከተቃዋሚ ኃይሎች ጋር መንግሥት ሰላማዊ ውይይትና ድርድር ይጀምር ብለዋል::
እኛ ኢትዮጵያን የመገንባት እንጂ የማፍረስ ዓላማ የለንም ያሉት ሰልፈኞቹ ፤ ጥያቄያቸው ምላሽ እስኪያገኝ በአገር ውስጥም ሆነ በዲያስፖራ ጠንካራ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን እንደሚያካሂዱ አስታውቀዋል:: ቄሮ የታገለው ኢትዮጵያን ከመፍረስ ለማዳን ነው ያሉት በሰልፉ ላይ ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎች ያም ቢሆን ጥያቄያችን የማይመለስ ከሆነ የማይቀረውን አማራጭ ለመግፋት እንገደዳለን ሲሉም ተናግረዋል::መላው የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችም ሰላማዊ ትግላቸውን እንዲደግፉ ጥሪ አስተላልፈዋል:: በድርጊቱ የተቆጡ አንዳንድ ሰልፈኞች በስፍራው በስራ ላይ በነበርንበት ወቅት "የመንግስት ወኪል ነው" በማለት ለመተናኮል ቢሞክሩም ፤በርካታ የጀርመን የፖሊስ ኃይል በቦታው በመኖሩ ከጥቃት ለመትረፍ ችለናል :: የሰልፉ አስተባባሪ አቶ አብዶቃዲ አባጀበል ካለመግባባት ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ ጠይቀዋል::
እንዳልካቸው ፈቃደ
እሸቴ በቀለ