1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደን ምንጣሮን ለመከላከል ያለመው የአውሮጳ ኅብረት ሕግ

ሐሙስ፣ ኅዳር 29 2015

የአውሮጳ ኅብረት ከሌሎች ሃገራት ወደ አባል ሃገራት የሚገቡ የተለያዩ የእርሻ ውጤቶችን የሚመለከት ደንብን ለማጽደቅ ተስማማ። ከመጪው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ጀምሮ በሕግ መልክ ይፋ የሚሆነው ደንብ በሌሎች ሃገራት የደን ጭፍጨፋን ለመከላከል እንደሚረዳ ነው የሚታሰበው።

https://p.dw.com/p/4KgHG
Abholzung des Amazonas
ምስል Tarso Sarraf/AFP/Getty Images

የአውሮጳ ገበያ


ከረዥም ጊዜያት ድርድር እና ውይይት በኋላ የአውሮጳ ኅብረት ፖለቲከኞች የተስማሙበት ይህ ውሳኔ በዓለም ደረጃ የደንን መራቆትን ለመግታት የተደነገገ የመጀመሪያው ደንብ ነው። አዲሱ ሕግ እንደቡና፣ ካካኦ፣ አኩሪ አተር፣ ጣውላ፣ ቆዳና መሰል የእርሻ ውጤቶች ወደ አውሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት መግባት የሚችሉት በደን ምንጣሮ ሂደት እንዳልተመረቱ የሚያሳይ ማረጋገጫ ካላቸው ብቻ እንደሆነ ይደነግጋል። የኅብረቱ ሃገራት በዚህ ደንብ ላይ ስምምነታቸውን ካረጋገጡ በኋላ የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑዌል ማክሮ «የአየር ንብረት እና ብዝሃሕይወትን ለመጠበቅ የሚደረገው ፍልሚያ እየተፋጠነ» ነው ብለዋል። የኅብረቱ ሃገራት በምክር ቤታቸው የተስማሙበት ደንብ ከጎርጎሪዮሳዊው 2003 ዓ,ም አንስቶ በሕግ ደረጃ እንደነበር እና አሁን ግን ዘላቂነትን አካትቶ መደንገጉን ነው አውሮጳ የደን ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ እና የዓለም አቀፍ የደን አስተዳደር ቡድን ሰብሳቢ ዶክተር ይታገሱ ተክሌ የገለጹልን። ተመራማሪው ሕጉ፤ አንድ ምርት በደን ምንጣሮ ያስከተለ ከሆነ በአውሮጳ ገበያ ላይ እንዳይሸጥ እንደሚያግድ ነው የገለጹልን። አያይዘውም። «የደን ምንጣሮን ያስከትላሉ ተብለው የሚታወቁ የግብርና እና የደን ምርቶች ቡና፣ ቸኮሌት፣ ሥጋ እና ጣውላ ሲመረቱ የደን ምንጣሮን ሳያስከትሉ መመረታቸውን የሚያረጋግጥ ይዘት ያለው ሕግ ነው።» በማለት አብራርተዋል። 
የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት FAO ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በመላው ዓለም 420 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የነበረ የደን ሀብት መጨፍጨፉን ያመለክታል። የደን ምንጣሮም ሆነ ጭፍጨፋው የሚካሄደው ደግሞ በተለይ ለውጪ ገበያ የሚሆኑ የተለያዩ ምርቶችን ለማብቀል በሚል ነው። በእንደዚህ መልኩ የሚመረተውን ደግሞ ከቻይና ቀጥሎ ለአውሮጳ ኅብረት ሃገራት ገበያ የሚቀርብ መሆኑ ነው የተገለጸው። አሁን የአውሮጳ ኅብረት ሃገራት ከተስማሙበት ደንብ በተቃራኒ በደን ምንጣሮ የተለያዩ ምርቶችን አብቅለው ለገበያ ከሚያቀርቡ ሃገራት መካከል ብራዚል፤ ኢንዶኔዢያ፣ ማሌዢያ፣ ናይጀሪያ፣ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ፣ ኢትዮጵያ፣ ሜክሲኮ እና ጓቲማላ እንደሚጠቀሱ የአዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘገባ ያመለክታል። ዶክተር ይታገሱ የተባለው ደንብ ለኢትዮጵያ የደን ሀብቷን ከመጠበቅ ጨምሮ በኤኮኖሚም ሆነ በማኅበራዊ ረገድ ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው ነው የሚሉት።
ለአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ የሚሟገተው ግሪን ፒስ የተሰኘው ተቋም በአውሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት እና የአውሮጳ ፓርላማ በረቂቅ ሕጉ ላይ መስማማታቸውን «ታላቅ ውጤት» ብሎታል። ሌሎችም የተፈጥሮ ጥበቃ ተሟጋቾች ስምምነቱን «ታሪካዊ» ነው ያሉት። የኅብረቱ ሃገራት የተስማሙበት ደንብ በ18 ወራት ውስጥ ነው ሥራ ላይ ይውላል የተባለው። ምንም እንኳን የደን ምንጣሮን በማስቆም ለአካባቢ ተፈጥሮ አስተዋጽኦ ያደርጋል በሚል ደንቡ ቢወደስም እንዲህ ያለ ሕግ ወደሌላቸው ሃገራት ገበያው ፊቱን ሊያዞር ይችላል የሚል ስጋት አለ። 
ሸዋዬ ለገሠ

Kolumbien| Entwaldung in Caqueta
የደን ጭፍጨፋ በኮሎምቢያምስል Juancho Torres/AA/picture alliance
Waldbrände in Brasilien I Amazonas
በቃጠሎ የተደረገፈው የደን ምንጣሮ በብራiዚልምስል Carl de Souza/AFP

አዜብ ታደሰ