1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«የደቡብ የሙዚቃ እና የስነጽሁፍ ሰው» ወንድሙ ከበደ

እሑድ፣ ሚያዝያ 24 2013

የደቡብ ክልል ካፈራቸው እና ስማቸው ጎልቶ ከሚነሳ የሙዚቃ እና ስነጽሁፍ ሰዎች አንዱ ነው ። ከሙዚቃ እና የስነጽሁፍ ስራዎቹ በተጨማሪ ጥሩ የባህል አምባሳደር ነው ይሉታል። «ዳውሮ ባና » የሚታወቅበት ነጠላ ዜማው ነው። ከተወለደበት ማሕበረሰብ አልፎ ስም እና ዝናን አትርፏል።

https://p.dw.com/p/3srZq
CD Schallplatten Musik Symbol
ምስል Gerd Gropp/Fotolia

ወንድሙ ከበደ «ዳውሮ ባና» እና የሙዚቃ ስራዎቹ

የደቡብ ክልል ካፈራቸው እና ስማቸው ጎልቶ ከሚነሳ የሙዚቃ እና ስነጽሁፍ ሰዎች አንዱ ነው ። ከሙዚቃ እና የስነጽሁፍ ስራዎቹ በተጨማሪ ጥሩ የባህል አምባሳደር ነው ይሉታል። ጤና ይስጥልን አድማጮች በዛሬው የመዝናኛ ዝግጅታችን ከተወለደበት ማሕበረሰብ አልፎ ስም እና ዝናን ከማትረፍ ባሻገር ሀገራዊ የባሕል ተልዕኮን ማሳካት ከቻለው ድምጻዊ እና ደራሲ ወንድሙ ከበደ ወይም ዳውሮ ባና ጋር ያደረግነውን ቆይታ ይዘን ቀርበናል። መልካም ቆይታ 
ትውልድ እና እድገቱ በልምላሜዋ በምትታወቀው የደቡቧ የዳውሮ ዞን ሲሆን ለጋ የወጣትነት ዕድሜውን በውትድርና ለማገልገል ተሰልፏል። በደርግ ዘመነ መንግስት በኤርትራ አስመራ ቆይቷል። ልክ እንደ አብዛኞቹ አንጋፋ ድምጻውያን እርሱም የሙዚቃ ስራውን በወታደር ቤት እንደጀመረ ይናገራል። ምናልባት የእርሱ የተለየ የሚያደርገው ሁለቱንም ማለትም ስነጽሁፉንም ሙዚቃውንም ጎን ለጎን ማስኬዱ ነው።  የሙዚቃ ስራውንም አንድ ብሎ የጀመረው በአስመራ ቆይታው በ1979 ዓመተ ምህረት እንደሆነ ይገልጻል።
የደረግ ስርዓት ከወደቀ በኋላ ወንድሙ መጀመርያ ወደ ሱዳን ከዚያም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ መኖርያውን የጅማ ከተማ በማድረግ «ሰላም» የተባለ ባንድ በከተማዋ በማቋቋም ለአሁኑ የሙዚቃ ጉዞው ሁኔታዎችን እንዳመቻቸለት ይናገራል። ከዳውሮ ብሔረሰብ ውጭ በብዙኃኑ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈለት «ዳውሮ ባና» የሚል መጠርያ የሰጠው ነጠላ ዜማው ቀደም ሲል ከነበሩት የሙዚቃ ስራዎቹ ወደ አዲስ ምዕራፍ ስለመሸጋገሩ አብሳሪ እንደነበር ይነገራል። የዳውሮ ብሔረሰብ ማንነት እና የተፈጥሮ ጸጋንም ለማስተዋወቅ መጥቀሙን ወንድሙ ከበደ ይናገራል።
ወንድሙ አንድ አልበምን ጨምሮ ከሰላሳ እስከ አርባ የሚደርሱ የሙዚቃ ስራዎችን መስራቱን ይናገራል። ይኼ ደ,ግሞ አሁንም ገና በርካታ የሙዚቃ ስራዎችን ሊሰራ እንደሚችል ያሳያል። 
የዳውሮ ዞን ካሉት ተፈጥሯዊ እና ባህላዊ ቅርሶች ውስጥ በ17 ኛው ክፍለዘመን በንጉስ ሃላላ እንደተገነባ የሚነገርለት የሃላላ ግንብን ጨምሮ የጨበራ ጩርጩራ ፓርክ ከፊል የሚገኝበት እንዲሁም በቅርቡ ግንባታው የሚጀመረው የኮይሻ ፓርክ ከፊል የሚገኝበት እንደ መሆኑ የብሔረሰብ ዞኑ ባህላዊ እና መልክዓ ምድራዊ ሀብቱ ከምንጊዜውም ይልቅ የሚተዋወቅበት እና  ህዝቡም የሚጠቀምበት እንደሆነ የሚገልጸው ወንድሙ ሙዚቃውም አብሮ እንዲያድግ የተሻለ ዕድል እንደሚያገኝ ያምናል።
ወንድሙ ከበደ እና ሌሎች በደቡብ ክልል ውስጥ ስም እና ዝናን ካተረፉ ድምጻውያን ጋር በጋራ የመሰረቱት ማሕበር ደግሞ የሙዚቃ ስራቸውን በሕብረት ለመስራት ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ባሻገር በ2012 ዓ/ም ናይጄሪያ አዘጋጅታ በነበረው የአፍሪካ የባህል ፌስቲቫል ላይ ተሳትፈው ኢትዮጵያን ወክለው አንደኛ  ወጥተው መመለስ የቻለ የባህል ቡድን አባል እንደነበር ነው ወንድሙ የሚገልጸው።
ወንድሙ ከበደ በሁለት ትዳር 7 ልጆችን አፍርቷል። ከሙዚቃ እና የስነጽሁፍ ስራው ጎን ለጎን ደግሞ የዳዉሮ የባህል ምግብ በማዘጋጀት እና በዚያም እውቅና እያተረፈ መምጣቱንም ያስረዳል።
 እግዲህ አድማጮቻችን ከድምጻዊ እና ደራሲ ወንድሙ ከበደ ጋር ያደረግነው የዛሬው የመዝናኛ ዝግጅታችን ይህንን ይመስል ነበር ለወንድሙ ከበደ የበለጠ ስኬትን እየተመኘን የዛሬውን በዚሁ አበቃን ጤና ይስጥልን!

ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ