1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ክ/ም/ት ጉባኤ በጸጥታ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 4 2012

የደቡብ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ማካሄድ ጀመረ። በቅርቡ ወደ ስልጣን የመጡት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው ለምክር ቤቱ ባቀረቡት የስራ ሪፖርት "በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ለሰው ህይወት መጥፋት ፣ ለንብረት ውድመትና ለበርካቶች መፈናቀል ምክንያት ሆነዋል" ብለዋል።

https://p.dw.com/p/3RLiM
Die Mitglieder haben die kritischen Fragen angesprochen
ምስል DW/S. Wegayehu

የደቡብ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ በሀዋሳ እየተካሄደ ነው

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው የክልሉ ምክር ቤት አምስተኛ ዙር አምስተኛ ዓመት አስረኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ሲጀመር የክልሉን መንግስት የ2011 ዓ.ም. የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል። በደቡብ ክልል ቀደም ሲል ጀምሮ ሲንከባለሉ ከመጡ የመዋቅር፣ የአከላለል፣ የማንነት፣  የወሰን እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ለታየው አለመረጋጋት በዋነኛ መንስኤነት እንደሚጠቀሱ አቶ እርስቱ በሪፖርታቸው ገልጸዋል።

አገራዊ ለውጡን የሚቃወሙ ግለሰቦች እና ቡድኖች የተዛቡ መረጃዎችን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ማሰራጨታቸውና አንዳንድ ወገኖች ለውጡን ከራሳቸው የግል ፍላጎትና ስሜት አንፃር ብቻ መተርጎማቸው በክልሉ ለታየው አለመረጋጋት ተጨማሪ ምክንያት መሆኑንም ዘርዝረዋል ። በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተስተዋሉት አለመረጋጋት እና የፀጥታ መደፍረሶችን በበጀት ዓመቱ በክልሉ መደበኛ የዕቅድ አፈፃጸም ሊተገበሩ በተያዙ የሰራ ዘርፎች ላይ አሉታዊ ተፅኖ አሳድሮ መቆየቱንም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

in neuer Regionalpräsident sollte sein Kabinett und verschiedener Ämter neu ordnen
ምስል DW/S. Wegayehu

የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮችን በመፍታተ ክልሉን ወደ ሰላማዊ ሁኔታ የመመለስ ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ የጠቀሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይም በየአካባቢው የኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ወደ ተግባር ከተገባ ወዲህ አንፃራዊ መረጋጋት መስፈኑን አስረድተዋል። "በአሁኑወቅት የክልሉ መንግስት በየደረጃው ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በሰላም ዙሪያ እያካሄደ ከሚገኘው ውይይት ጎን ለጎን የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል" ብለዋል። 

ዝርዝር ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ሸዋንግዛው ወጋየሁ 

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ