1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ኢትዮጵያ ዞኖች ክልል የመሆን ውሳኔ 

ማክሰኞ፣ ኅዳር 18 2011

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል መስተዳድር ውስጥ ወደ ክልል እንደግ የሚሉ ዞኖች ቁጥር ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ ከፍ እያለ መጥቷል። ለምሳሌ ይህ ጥያቄው ትናንት በዞን ምክር ቤት የጸደቀለት የጉራጌ ዞን ይገኝበታል።

https://p.dw.com/p/38zqL
Süd Äthiopien, Hawassa See
ምስል DW/S. Wegayehu

«የዞኖቹ ውሳኔ በከፍተኛ ጥንቃቄ ካልተያዘ ለሌላ ብጥብጥ በር ይከፍታል።»

ይሁንና፣ የዚሁ ውሳኔ አፈጻጸም በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያዝ እንደሚገባ አንድ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ስጋታቸውን ገልጸዋል። ይሁንና፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ በምህጻሩ ደኢህዴን ውሳኔውን ማስፈጸም አዳጋች እንደሆነ ከወዲሁ አስታውቋል።                   
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ውስጥ የሚገኙ የተለያዩት ዞኖች ራሳቸውን ችለው ክልል ለመሆን በየምክር ቤቶቻቸው ጥያቄ ሲያቀርቡ ሰንበት ብሏል።ረቡ ይገኛሉ። ባለፉት ጥቂት ጊዚያት የሲዳማ፣ የወላይታ፣  የከምባታ፣ እና የጋሞ ዞኖች፣ ትናንት ደግሞ የጉራጌ ዞን ይኸው ጥያቄአቸው ጸድቆላቸዋል። የጉራጌ  ዞን ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔ ክልል የመሆን ጥያቄን ከመረመረ በኋላ ምልዓተ ጉባዔው እንዳጸደቀው የጉራጌ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና መንግሥት ኮሙኒኬሼን መመሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት አመልጋ ለ DW አስታውቀዋል። የማረቆ፣ የቀቤና እና የጉራጌ ብሔረሰቦች የተጠቃለሉበት ከአምስት ሚልዮን ህዝብ በላይ ያለው የጉራጌ ዞን፣ ክልል ለመሆን ልምዱ ያለው እና የሚያስፈልገውንም መስፈርት ማሟላቱን የገለጹት ወይዘሮ መሰረት፣ ወቅቱ የዞኑ ህዝብ ራሱን በራሱ በክልል የማስተዳደር ጥያቄ እንዲያቀርብ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮለታል ብለዋል። 
እስካሁን በክልሉ ከሚገኙት ዞኖች መካከል ብዙዎቹ በክልል የእንደራጅ ጥያቄ ማቅረባቸው፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል  አሁን ባለበት ሁኔታ መቀጠሉን አጠያያቂ እንዳደረገው በወልቅጤ ዩኒቬርስቲ የፖለቲካ ሳይንስና የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ ዳንኤል መኮንን ለDW ተናግረዋል። እንደ አቶ ዳንኤል፣ ዞኖቹ ከበፊቱም በክልሉ የተጠቃለሉት በፍላጎታቸው አልነበረም።
በዚህም የተነሳ ከደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ በምህጻሩ ደኢህዴን ጋር ያላቸው ግንኙነት እጅግ ደካማ እንደሆን አቶ ዳንኤል ቢያስታዉቁም፣ በፍላጎት ላይ ተመስርተው  ጠንካራ ክልል ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ገልጸዋል፣ ግን፣ ይህ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚጠይቅ የወልቂጤው ዩኒቨርሲቲ መምህር አመልክተዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ፣  የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንዳመለከቱት፣ ክልሉን የሚያስተዳድረው ፣ ደኢህዴን፣ የዞኖቹ ምክር ቤቶች የደረሱበት በክልል የመደራጀት ውሳኔ ምንም እንኳን ሕገ መንግሥታዊ ቢሆንም ደኢህዴን ካስቀመጠው አቅጣጫ ውጭ  በመሆናቸው  ለማስፈፀም አዳጋች እንደሚሆን ገልጿል።  

Wasserreinigung Pflanze aus Süd-Äthiopien Omo Zone
ምስል DW

አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ