1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ዉሳኔ የመጀመሪያ ዉጤት

ማክሰኞ፣ ጥር 30 2015

የትናንቱ የድምፅ አሰጣጥ ሒደት በተወሰኑ አካባቢዎች ካጋጠሙ መለስተኛ ችግሮች በስተቀር በታቀደው መሠረት መደረጉን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡

https://p.dw.com/p/4NCEi
Äthiopien Referendum Arbaminch
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የድምፁ ዉጤት በየምርጫ ጣቢያዎች እየተነገረ ነዉ

 በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በስድስት ዞኖችና በአምስት ልዩ ወረዳዎች ትናነት የተደረገዉ ህዝበ ውሳኔ ውጤት ዛሬ በየምርጫ ጣቢያዉ ይፋ ተደርጓል፡፡የትናንቱ የድምፅ አሰጣጥ ሒደት በተወሰኑ አካባቢዎች ካጋጠሙ መለስተኛ ችግሮች በስተቀር በታቀደው መሠረት መደረጉን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ እንዳሉት አጠቃላዩ የህዝበ ውሳኔ ውጤት ከአምስት ቀናት በኋላ በይፋ ይነገራል።

የህዝበ ውሳኔ ቆጠራ ውጤት ይፋ አየተደረገ ነው

ትናንት በደቡብ ክልል ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች የተካሄደው የሕዝበ ውሳኔ የድምፅ ቆጠራ ውጤት ዛሬ ይፋ ተደርጓል ፡፡ መራጮች ድምፅ በሰጡባቸው የምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት የድምፅ ቆጠራ ውጤቶችን ሲመለከቱ ውለዋል ፡፡ ህዝበ ውሳኔው ከተካሄደባቸው መካከል አንዱ በሆነው የጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ከተማ የምርጫ ጣቢያ ውጤት ለማየት የተገኙ መራጮች በየጣቢያዎቹ  የተለጠፉ  ውጤቶችን ሰብሰብ ብለው ሲመለከቱ ፣በውጤቱ ዙሪያም ሀሳብ ሲለዋወጡ መመልከቱን በሥፍራው የተገኘው የዶቼ ቬለ ዜና አቀባይ ሸዋንግዛው ወጋየሁ ዘግቧል ፡፡

Äthiopien Referendum Arbaminch
ህዝበ ውሳኔ በአርባ ምንጭምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ትዕግስት ይፍሩ በከተማው አሻም ምርጫ ክልል ትናንት ድምፅ የተሰጠበትን ውጤት ለማየት መገኘቷን ትናገራለች ፡፡ በውጤቱም ድምፅ በሰጠችበት ጣቢያ አሷ የደገፈችው አማራጭ ከፍተኛ ውጤት እንዳገኘ መመልከቷንና በዚህም መደሰቷን ተናግሯል፡፡

በክልሉ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ትናንት ድምፅ የተሰጠበት ህዝበ ውሳኔ ሰላማዊና በተያዘለት ዕቅድ መሠረት መከናወኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡

ያም ሆኖ በተወሰኑ የምርቻ ጣቢያዎች መለስተኛ ችግሮች አጋጥመው እንደነበር የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል ፡፡

Äthiopien Referendum Arbaminch
በአርባ ምንጭ በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ ተሳታፊዎች ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በድምፅ አሰጣጥ ሂደት ካጋጠሙ የአሰራር ግድፈቶች መካከልም ለአካለ መጠን ያልደረሱ 18 አመት ያልሞላቸው ዜጎች በመራጭነት ተመዝግበው መገኘታቸው እንዱ መሆኑን የጠቆሙት ሰብሳቢዋ «በዎላይታ ዞን አስተዳደር  በበሌ ማእከል በሶርቶ ምርጫ ጣቢያ የመታወቂያ ወረቀት የማደል የተፈፀመ የህግ ጥሰቶችንም አጋጥመዋል  ፡፡ ነገር ግን ሁሉንም የህግ ጥሰቶች  ወዲያው ማረምና ሂደቱን ለመቀጠል  ተችሏል ፡፡ በአሁኑ ወቅት በእብዛኛው ምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ ቆጠራ ተጠናቆ በዛሬው ዕለት በምርጫ ጣቢያዎች ደረጃ የቆጠራ ውጤቶች ይፋ ተደርጓዋል ፡፡ አጠቃላይ የህዝበ ውሳኔው  ውጤትም ከአንድ ሳምንት በኋላ ይገለጻል»ብለዋል፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ 

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ