1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ህዝበ ውሳኔ ዝግጅት

ማክሰኞ፣ ጥር 23 2015

በደቡብ ክልል በመጪው ሳምንት መጀመሪያ ለሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ አሥፈላጊውን መሰናዶ በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጲያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ገለፀ፡፡ በአሁኑወቅት በህዝበ ውሳኔው ድምፅ ለመስጠት የሚያገለግሉ የምርጫ ቁሳቁሶች ወደ የምርጫ ጣቢያዎች እየደረሱ ሲሆን ለምርጫ አስፈጻሚዎችም በድምፅ አሰጣት ዙሪያ ገለጻ እየተደረገ ይገኛል ተብሏል።፡

https://p.dw.com/p/4Mv7C
Äthiopien Birtukan Midekssa
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የምርጫ ቁሳቁሶች ወደ ምርጫ ማዕከላቱ በመጓጓዝ ላይ ነዉ

በደቡብ ክልል በመጪው ሳምንት መጀመሪያ ለሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ አሥፈላጊውን መሰናዶ በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ገለፁ፡፡ ዋና ሰብሳቢዋ ከዶቼ ቬለ DW ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ በአሁኑወቅት በህዝበ ውሳኔው ድምፅ ለመስጠት የሚያገለግሉ የምርጫ ቁሳቁሶች ወደ የምርጫ ጣቢያዎች እየደረሱ ሲሆን ለምርጫ አስፈጻሚዎችም በድምፅ አሰጣት ዙሪያ ገለጻ እየተደረገ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በህዝበ ውሳኔው 3 ሚሊዮን 28 ሺህ 770 መራጮች መመዝገባቸውን የጠቀሱት ዋና ሰብሳቢዋ 3 ሺህ 769 የምርጫ ጣቢያዎችም በሥራ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ አሁን ላይ ቦርዱ ድምፅ ለመስጠት የሚያገለግሉ የምርጫ ቁሳቁሶች ወደ ምርጫ ማዕከላቱ በመጓጓዝ ላይ እንደሚገኙና በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ሙሉ በሙሉ በጣቢያዎቹ ይደርሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል ፡፡

በወላይታ ዞን የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የማህበረሰብ አንቂዎች ሕዝበ ውሳኔው የራስን ክልል የማደራጀት ዕድልን የነፈገ ነው ይላሉ ፡፡ በጋራ ክልል ከመደራጀት ጎን ለጎን የራሳቸውን ተናጠላዊ ክልል ለመመሥረት ለሚፈልጉ አካላት በህዝበ ውሳኔው ውስጥ እንደ አንድ አማራጭ ለምን አልተካተተም በሚል ዶቼ ቬለ DW ዋና ሰብሳቢዋን ጠይቋል፡፡

ቦርዱ ቁጭ ብሎ ይኼኛው አማራጭ ይካተት ያኛው አይካተት የማለት የህግ ሥልጣን እንደሌለው የጠቀሱት ሰብሳቢዋ “ ህዝበ ውሳኔው በክልሉ  6 ዞኖችና 5 ልዩ ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች የጋራ ክልል ለመመሥራት የሚደረገው ሂደት በህዝቡ መደገፍና አለመደገፉ እንዲለካ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት እየተከናወነ የሚገኝ ነው ፡፡  ይህ ማለት ግን ያለቀ ጉዳይ ነው ማለት አይደለም ፡፡ ዛሬ በዚህ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ተሰጠ ማለት ነገ በሌላ ጉዳይ ህዝበ ውሳኔ አይካሄድም ማለት አይደለም ፡፡  የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የወላይታ ህዝብ ራሱን በቻለ ክልል እንዲደራጅ ፍላጎት ካላችው አሁንም በራሳቸው መስመር ተጉዘው ወደ እኛ እንዲመጣ የማድረግ መብት አላቸው “ ብለዋል ፡፡

Äthiopien Birtukan Midekssa
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በመራጭነት የተመዘገበው ነዋሪ ውሳኔ በሚሰጥባቸው አማራጮች ላይ ግንዛቤ ኖሮት እንዲመርጥ ምን ያህል  ዝግጅት ተደርጓል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ሰብሳቢዋ ሲመልሱ “ህዝቡ ሁለቱንም ምልክቶች ለይቶ እንዲያውቅና ሀሳቡን በትክክል እንዲገልፅ ለማድረግ የመገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች መረጃዎችን እየተሰጡ ይገኛሉ ፡፡ ይህ በቀሪ ቀናትም የሚቀጥል ይሆናል ፡፡ አደረጃጀቱን ባለመደገፍ የሚከራከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይህንኑ አቋማቸውን ለደጋፊዎቻቸውና ለመራጮች  እንዲያስረዱ ቦርዱ ጥሪውን ያቀርባል “ በማለት ገልጸዋል፡፡

በደቡብ ክልል የፊታችን ጥር 29 2015 ዓም በሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ በክልሉ 6 ዞኖችና 5 ልዩ ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች የጋራ ክልል እንዲመሠረት “ እደግፋለው“ ወይም “ አልደግፍም “ በሚሉ አማራጮች  ድምፃቸውን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ፡፡ ህዝበ ውሳኔው የመራጮችን ይሁንታ ካገኘ የወላይታ ፣ የጋሞ ፣ ጎፋ ፣ የኮንሶ ፣ የደቡብ ኦሞ ፣ የጌዴኦ ዞኖችና እንዲሁም የአማሮ ፣ የቡርጂ ፣ የደራሼ ፣ የአሌ እና የባስኬቶ ልዩ ወዳዎች የፌዴራል ሪፐብሊኩ 12ኛ ክልላዊ መንግሥት በመሆን የሚደራጁ ይሆናል ፡፡

ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ 

አዜብ ታደሰ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ