1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ሥራ አለመጀመር

ማክሰኞ፣ ጥር 14 2011

የረጲ የኃይል ማመንጫ ዛሬም  ወደ ሥራ አልተመለሰም። በ2.6 ቢሊዮን ብር የተገነባው እና ደረቅ ቆሻሻን ወደ ኃይል በመቀየር ለከተማዋ ችግር መፍትሔ ይሰጣል ተብሎ ነበር።

https://p.dw.com/p/3Bv6I
Mülltrennung in Indien
ምስል picture-alliance/Zumapress/S. Thakur

የረጲ የኃይል ማመንጫ ዛሬም  ወደ ሥራ አልተመለሰም

ከተመረቀ ከሁለት ሳምንታት በኋላ የቆመው የረጲ የኃይል ማመንጫ ዛሬም ወደ ሥራ አልተመለሰም። በ2.6 ቢሊዮን ብር የተገነባው እና ደረቅ ቆሻሻን ወደ ኃይል በመቀየር ለከተማዋ ችግር መፍትሔ ይሰጣል ተብሎ ነበር።  የከተማውን 50 በመቶ ቆሻሻ ወደ ሀይል የሚለውጠው ይሄው ፕሮጀክት ከሁለት ሳምንታት የሙከራ ስራ በሃላ ተቋርጧል። ባሳለፍነው ነሐሴ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. የተመረቀው የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ሃይል ማመንጫ ዛሬም ስራውን አልጀመረም።  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅ ዶ/ር እሸቱ ለማ ኃይል ማመንጫው ቆሻሻ መቀበል ማቆሙን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እንደተነገራቸው ለ«DW» አረጋግጠዋል። ይኸ ከሆነ አራት ወራት ገደማ አልፈዋል። ለሁለት ሳምንታት ቆሻሻ ም ለኃይል ማመንጫው ስናቀርብ ቆይተን ከኢትዮጵያ መብራት ሀይል ኮርፖሬሽን ስራውን እንድናቆም ተነገረን ይላሉ። «በከተማው ያለውን ቆሻሻ ሰብስበን እያቀረብን ነበርን በድንገት አቆሙ። ስንጠይቅ አጣርተን ከሁለት ሳምንት በሃላ እንነግራችሃለን አሉን። እስካሁን ድረስ ሳይጀምር ቆይቷል። በቀን 3000 ቶን ቆሻሻ ይመረታል። 47 በመቶ የሚሆን ቆሻሻ እያስወገዱልን ነበር።» የአዲስ አበባ ከተማ ደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ ኃላፊነት የከተማዋን ቆሻሻ ሰብስቦ በተገቢው መንገድ ለሃይል ማመንጫው ማቅረብ እንደሆነ ዶ/ር እሸቱ ይገልጻሉ።  «የኛ ድርሻ ቆሻሻ ሰብስበን በተገቢው መንገድ ለሀይል ማመንጫው ማቅረብ ነው። ሲቋቋም 50 በመቶ የከተማዋን ደረቅ ቆሻሻ ያስወግዳል ተብሎ ነበር። ሁለት ሳምንት አካባቢ እንደሰራ ነው የቆመው።» ዶ/ር እሸቱ ስለፕሮጀክቱ አስፈላጊነት ሲገልጹም፤ ትልቅ ፋይዳ አለው ይላሉ። « 50 በመቶ ቆሻሻ ወደ ሃይል ማመንጫው እንወስዳለን። ፕሮጀክቱ ስራ ቢጀምር ትልቅ ፋይዳ አለው። የሚመለከተው አካል ተረባርቦ ወደ ስራ እንዲገባ ቢደረግ መልካም ነው።» ወደ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ዋና ስራ አስፈጻሚ ቢሮ  በተደጋጋሚ ጊዜ ስልክ ብንደውልም የኮርፖሬሽኑን ኃላፊ ልናገኛቸው አልቻልንም። የሚስተካከሉ ቴክኒካል ስራዎች ስላላለቁ የሙከራ ስራ እንጂ ይፋዊ የሆነ ርክክብ እንዳልተፈጸመ ከኮሙኒኬሽን ቢሮ ለማወቅ ችለናል። 
 

ነጃት ኢብራሂም

እሸቴ በቀለ